በኢትዮጵያ መድኀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ መድኀኒቶች ተበላሽተዋል

0
623
  • 23 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ መድኀኒቶች የአገልግሎት ጊዜያቸው ማለቂያ እየተቃረበ ነው

በኢትዮጵያ መድኀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በባሕር ዳር ቅርንጫፍ ውስጥ ብቻ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ መድኀኒቶች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።
አዲስ ማለዳ ከቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው በገንዘብ የተገዙ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ መድኀኒቶችና ከለጋሽ አገራት እና ድርጅቶች የተገኙ ደግሞ 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ መድኀኒቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ማለፉን ለማወቅ ተችሏል። ከዚሁ በተጨማሪ በአቀማመጥ ስህተትና በማጓጓዝ ሒደት ላይ ደግሞ በጥቅሉ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ መድኀኒቶች እንዲበላሹ ሆነዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በመንግሥት ወጪ ተገዝተው እና ከለጋሽ አገራት እና ድርጅቶች የተገኙ በጠቅላላ ዋጋቸው 23 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ መድኀኒቶች በጥቂት ወራት ውስጥ ለተጠቃሚዎች ሳይደርሱ የአገልግሎት ጊዜያቸው እንደሚያልፍ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በኤጀንሲው የአዲስ ማለዳ ምንጭ ከባሕር ዳር ቅርንጫፍ ተናግረዋል። በአካባቢው በተለይም ደግሞ በባሕር ዳርና ዙሪያዋ በርካታ ሴቶችና ሕፃናት ከመድኀኒት እጥረት ጋር በተያያዘ ለህልፈት በሚዳረጉበት በዚህ ሰዓት በርካታ መድኀኒቶች ግን በመጋዘን ተቀምጠው ያለምንም ግልጋሎት ለብልሽት እየተዳረጉ መሆኑንም ምንጮች አያይዘው ገልፀዋል።

በሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ የወጣባቸው መድኀኒቶች በአጭር ጊዜ የአገልግሎት ጊዜያቸው ማለፉ በርካታ ምክንያቶችን የሚገልፁት ምንጮች፤ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ በሙስና እና ብልሹ አሰራር የተጠላለፈ ግዢ ሒደት እንዲሁም ፍትሀዊ ያልሆነ የመድኀኒቶች ክፍፍል በዋናነት ይጠቀሳሉ። ምንጮች እንደሚገልፁት የዓለም የጤና ድርጅት መድኀኒቶች በሚገዙበት ወቅት የአገልግሎት መስጫ ጊዜያቸው ኹለት ዓመታትና ከዛ በላይ መሆን እንዳለበት ሕግ ቢኖርም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ግን ከኹለት ዓመታት በታች ዕድሜ የሚቀራቸው መድኀኒቶች እንደሆኑ አስታውቀዋል። መድኀኒቶች የሚገዙበት አገራት ለማስወገድ ብዙ ወጪ ስለሚጠበቅባቸው በቅናሽ ዋጋ የአገልግሎት ዘመናቸው እያለቁ የሚገኙ መድኀኒቶችን ለኢትዮጵያ በመሸጥ የመንግስት አካላትም በጥቅም ትስስር ካላቸው አስመጪዎች ጋር በመመሳጠር መድኀኒቶችን እንደሚረከቡ አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ከመጀመሪያው ጀምሮ ድርጅቶች ጨረታ አሸንፈው መድኀኒቶችን እንዲያስመጡ የሚደረጉ ድርጅቶች በትክክል ቅድመ ሁኔታዎችን የማያሟሉ መሆናቸው ከሚፈለገው ደረጃ በታች መድኀኒቶች እንዲገቡ ምክንያት እንደሆነም ታውቋል።

መንግሥት ገንዘብ አውጥቶ ከሚገዛቸው እና ለተጠቃሚዎችም በገንዘብ ከሚተላለፉ መድኀኒቶች በተጨማሪ ከለጋሾች የሚገኙት መድኀኒቶች በዋናነት ወባ፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስ እና ቲቢ መድኀኒቶች ናቸው። በአካባቢው በወባ በሽታ ኅብረተሰቡ በየቀኑ ኑሮው ፈተና ሆኖበት ባለበት ሁኔታ መድኀኒቶች ጥቅም ላይ ሳይውሉ በመንግሥት አካላት ድክመት አገልግሎት ጊዜያቸው ማለፉ እጅግ አገርን እና ወገንን የሚጎዳ ነው ሲሉ ምንጮች አስተያየታቸውን ያስቀምጣሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ካለፈው ዓመት በመነሳት ለመጭው ዓመት የሚደረጉ ግዥዎችን በትክክል አለመተንበይ እንደ ችግር የሚጠቀስ ነው። ይህ ደግሞ ትክክለኛ መግዛት የሚያስፈልገውን የመድኀኒት ብዛት እንዳይገዛና በተፈለገው ቦታ እንዳይደርስ የሚያደርግ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች 17 ቅርንጫፎችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የመድኀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በርካታ ክፍተቶችን እንደሚስተዋልበት የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል። የባሕር ዳሩን ቅርንጫፍ ጨምሮ በአማራ ክልል ጎንደር እና ደሴ ከተሞች ቅርንጫፎች እንዳሉትም ለማወቅ ተችሏል።

በተነሱት ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ መድኃኒቶች ወደ ቅርንጫፎች የሚላኩት ከቅርንጫፎች በሚመጣ ጥያቄ መሰረት እንጂ በዘፈቀደ የሚታደል ነገር እንዳልሆነ አስታውቋል። የኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አድና በሬ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት የአገልግሎት ጊዜያቸው ከኹለት ዓመት በታች የሆኑ መድኃኒቶች የሚገዙበት ልዩ አጋጣሚዎች እንዳሉም አስታውቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here