ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰላም አሰከባሪ ኃይል በደቡብ ሱዳን ምዕራብ ኢኳቶሪያ ግዛት ለሰላም መረጋገጥ እየከፈለ ያለው ዋጋ የሚደነቅ ነው ሲሉ የግዛቱ ዋና አስተዳዳሪ አልፎርድ ፋቱዩ ገለፁ።
ዋና አስተዳዳሪው በየዓመቱ የሚከበረውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀን ምክንያት በማድረግ በተከናወነው የመታሠቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ለዓለም ሠላም መከበር ሲሉ ህይወታቸውን ለገበሩ ሠማዕታት የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።
“ለህዝቦች ሠላምና ዕድገት” በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ዋና አሰተዳዳሪው አልፎርድ ፋቱዬ ባደረጉት ንግግር፤ ማንኛውም በዓለም ላይ ያለ ዜጋ ሰላምን የማምጣት ኃላፊነት አለበትና ህዝብ ለህዝብ እንዲሁም አገራት ከአገራት በመምከር ስለ ሰላም በበለጠ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በግዛታችን ስለ ሰላም መረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰሩ ያሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እየከፈሉት ላለው ውድ ዋጋ ትልቅ ክብር አለን በማለትም ምስጋና አቅርበዋል።
በምዕራብ ኢኳቶሪያ ስቴት የዩናሚስ ፊልድ ኦፊሰር ኃላፊ ክርስቶፎር ምቹሪ ሞሪንጋ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ከተመሰረተበት እ.ኤ.አ 1946 አንስቶ በተለያዩ አገራት ለሰው ልጅ ሰላም መረጋገጥና በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ተሰማርቶ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመው በእስካሁን የሰላም ማሰከበር ግዳጅ ሂደት ላይም ከ4 ሺህ 300 በላይ የተለያዩ አገር ዜጎች ውድ ህይወታቸውን ለዚሁ ዓላማ መገበራቸውን አስታውሰዋል።
በዚሁ ዓለም አቀፍ የሰላም ማሰከበር ቀን የሰማዕታት መታሠቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ የ15ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ አመራር እና አባላት፣ የዩናሚስ ወታደራዊ ታዛቢዎች፣ የግብረ ሰናይ ድርጅት ተወካዮች፣ የምዕራብ አኳቶሪያ ግዛት ከፍተኛ አመራሮች፣ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መታደማቸውን ከኢፌዴሪ መከላያ ሰራዊት ያገኘኘው መረጃ አመላክቷል።








