በኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች አቅራቢያ የህገ-ወጥ ቤቶች ግንባታ እየተበራከተ ነው ተባለ

0
1082

ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ምሰሶዎች አቅራቢያ የህገ-ወጥ ቤቶች ግንባታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ኮንቨርተር ጣቢያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የፕሮጀክቱ ሳይት ሥራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ አያሌው እንደገለፁት፤ ካለፉት ኹለት ዓመታት ወዲህ በአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢው የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን ተከትሎ በርካታ ህገ-ወጥ ቤቶች እየተገነቡ ነው፡፡

በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ምሰሶዎቹ አቅራቢያ እየተከናወኑ የሚገኙትን ህገ-ወጥ የቤቶች ግንባታ እና የመሬት ወረራ ለማስቆም ከከተማው አስተዳደር እና ከዞን ጽ/ቤት አመራሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ቢደረጉም ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ነው ቴዎድሮስ የገለፁት፡፡

ተቋሙ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለሚመለከታቸው የክልል እና የፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ማሳወቁንም አብራርተዋል፡፡

የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታው ከመጀመሩ በፊት በአካባቢው ምንም ዓይነት ግንባታም ሆነ የመሬት ወረራ አልነበረም ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ የፍተሻ ሥራ እየተከናወነ ባለበት ወቅት ከ300 በላይ የህገ-ወጥ ቤቶች ግንባታ መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን ደህንነት ለመፈተሸ ህገ-ወጥ ቤቶቹ ወደ ተሰሩበት አካባቢ መግባት ከፀጥታ አኳያ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ተቋሙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ በሚያልፍባቸው ቦታዎች ሁሉ ተገቢውን የካሳ ክፍያ ከወረዳ አስተባባሪዎች ጋር በመሆን ፈፅሟል ያሉት ቴዎድሮስ፤ ይሁን እንጂ በአርባ ምንጭ ከተማ እና በምዕራብ አባያ አንዳንድ አካባቢዎች የወሰን ማስከበር ሥራው አደጋ ላይ መውደቁን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ዲዛይን ሲደረግ ከምሶሶው 32 ነጥብ 5 ሜትር ርቀት ምንም ዓይነት የቤቶች ግንባታ ማካሄድ እንዲሁም ከ30 ሜትር ወዲህ ማናቸውንም አዳጊ ዕፅዋቶች መትከል የማይፈቀድ መሆኑ በህግ ቢደነገግም፤ በተጠቀሱት አካባቢዎች ግን ህጉን ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ አመላክቷል፡፡

በተያያዘ ዜናም በያቤሎ ከተማ የኃይል ማስተላለፊያ ምሶሶዎቹ አቅራቢያ የአራት ቤቶች ግንባታ ቢከናወንም ከከተማው አስተዳደር ጋር በተደረገ ውይይት ህገ-ወጥ ቤቶቹን የማፍረስና ተጨማሪ ግንባታዎችና የመሬት ወረራዎች እንዳይፈፀሙ ለመከላከል ሥምምነት ላይ መደረሱን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የግንባታ ሥራው በ2008 የተጀመረው የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ከ183 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ መጠናቀቁን ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here