ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ኹለት መቶ ሺሕ ቶን ስንዴ ሊገዛ ነው

0
442

መንግሥት ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አገልግሎት የሚውል 2 መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ሊገዛ መሆኑን አስታወቀ።
ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚገዛው 2 መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ እና ችግረኛ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ የሚውል እንደሆነ በመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አሰፋ ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ሥር የወጣው ዓለም ዐቀፍ ጨረታ በአገልግሎቱ ሥር ግዢው የሚፈፀም ሲሆን በጨረታውም ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አገር ባለሀብቶች በቀጥታ መሳተፍ እንደሚችሉ የገለፁት አሰፋ፤ ጨረታው ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችም ከመስከረም 10 ጀምሮ ሰነዱን መግዛት የሚችሉ ሲሆን ጥቅምት 18 ጨረታው ክፍት ይሆናል ብለዋል።

በተመሳሳይም ባሳለፍነው ሳምንት በመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ሥር ለኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሚውል 4 መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ጨረታ መውጣቱ ይታወሳል። ለኮርፖሬሽኑም የሚገዛው ስንዴ ገቢያን ለማረጋጋት የታሰበ ሲሆን ለተለያዩ ዳቦ መጋገርያዎችና መሸጫዎች የሚከፋፈል ይሆናል ተብሏል። ጨረታውም ጥቅምት 12/2012 የሚከፈት ይሆናል።

ከዚህ ቀደም በግብርና ሚኒስቴር እንደተገለፀው ከሆነ በኢትዮጵያ በስንዴ ምርት የሚለማው መሬት ወደ 1.8 ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ ነው። ከዚህም የሚገኘው ምርት 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ሲሆን የምርት መጠኑም በሔክታር 27 ኩንታል ነው። ይህም አገሪቱን በአፍሪካ በስንዴ ምርት ልማት በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል ተብለዋል። ሆኖም ግን አገሪቱ ለነዋሪዎችዋ የዕለት ተዕለት ፍጆታ የሚውል ስንዴን ከውጭ በማስገባት ታቀርባለች። ይህም ከአገሪቱ አመታዊ የስንዴ ፍጆታ 25 በመቶ ያህሉን የሚሸፍን ሲሆን፣ በዓመት ስንዴ ከሌሎች አገራት ለመግዛት የምታወጣው ወጪ በአማካኝ 600 ሚሊዮን ዶላር ያህል ነው።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ባሳለፍነው የበጀት ዓመት ለኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን 1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ገደማ ወጪ የተደረገ ሲሆን ለግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አንድ መቶ 55 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ አንድ ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባቀረበው 6 መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ ማድረጉን አመላክቶ በአጠቃላይ አንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዢ የፈፀመ ሲሆን ለዚህም ግዢ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here