- ከመደበኛ መምህራን 2 ሺሕ 200 ብር ጭማሬ ያገኛሉ
በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የተመደቡ የኦሮምኛ ቋንቋ አስተማሪዎች ከመደበኛው ክፍያ በተለየ ልዩ ጥቅማ ጥቅምና ደሞዝ እያገኙ መሆኑን ተከትሎ በአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ቅሬታቸውን አቀረቡ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለእነዚህ መምህራን 3 ሺሕ ብር እየተከፈለ ለመደበኛ መምህራን ግን 800 መከፈሉ ተገቢ እንዳልሆነ ብንጠይቅም ምላሽ አልተሰጠንም ብለዋል።
በአዲስ አበባ ንፋስ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በአንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ በታሪክ መምህርነት በማገልገል ላይ የሚገኙ፣ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ መምህር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በተመሳሳይ የሙያ ዘርፍ ውስጥ እያለን የኹለት ሺሕ ኹለት መቶ ብር ልዩነት ሊኖር የቻለበት ምክንያት አልገባንም። የተሻለ የሥራ ልምድ ያላቸው መምህራን እንኳን በዚህ ደረጃ ተጠቃሚ አልሆኑም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የትምህርት ቤታችንን አስተዳደር ብንጠይቅም ለሁኔታው እርሳቸውም እንግዳ መሆናቸውን ነግረውናልም ብለዋል። ከትምህርት ቢሮ ለመጡ ባለሙያዎችና ኀላፊዎች ጥያቄውን ቢያቀርቡም “አርፋችሁ ሥሩ” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በሌላ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህር ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፣ የዓበሉን ልዩነት ስንሰማ በጊዜው ደንግጠን ነበር ይላሉ። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ፈልገን የትምህርት ቢሮ ሰዎችን ስንጠይቅ ከኦሮሚያ ለመጡ መምህራን የሚከፈለው ክፍያ ከትምህርት ቢሮ አለመሆኑን ሲነግሩን ይበልጥ ግራ ተጋብተናል። በአንድ ተቋም እየሠራን በተለያየ አካል ለምን ደሞዝ ይከፈላል የሚል ጥያቄ ብንጠይቅም አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም ብለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አበበ ቸርነት፣ ትምህርት ቢሮው የመምህራኑን ቅሬታ እንደሚያውቁት ገልጸው፣ ነገር ግን በሒደት ምላሽ የሚያገኝ ጉዳይ መሆኑን አስታውቀዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራን የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አዲሱ ሻንቆ፣ ቅሬታዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ በአዲስ አበባ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ በሚሰጥባችው አራት ትምህርት ቤቶች በ2010 ከኦሮሚያ ክልል መጥተው ለሚያስተምሩ መምህራን በኦሮሚያ ክልል መንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆነ “አልመቱማ” በተባለ ድርጅት ድጋፍ ተጨማሪ 2 ሺሕ 200 ብር የቤት ኪራይ አበል እየተከፈላቸው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በሌሎች ትምህርት ቤቶች በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራን በመደበኛ ደሞዝና አበል እንዲያስተምሩ ውል ገብተው ከክልሉ መምጣታቸውን የሚያወሱት አዲሱ፣ ከአራት ትምህርት ቤቶች ውጪ የተለየ ክፍያ የሚከፈላቸው የኦሮሚያ መምህራን አለመኖራችውን አስታውቀዋል።
ከዓመት በፊት ከኦሮሚያ ዙሪያ እየመጡ ለሚማሩ ተማሪዎች ይከፈል የነበረው የትራንስፖርት አበል መቋረጡን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በአሁኑ ሰዓት ተማሪዎቹ በራሳቸው ወጪ እየተመላለሱ እየተማሩ ነው ብለዋል።
ከመምህራን በርካታ የቤትና የአበል ጥያቄዎች በመነሳት ላይ መሆናቸውን ያሳወቁት አዲሱ፣ ይህንን ለመፍታት ከፌደራል መንግሥት ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ የመምህራኑ ብቻ ሳይሆን የሌላውም መንግሥት ሠራተኛ በመሆኑ፣ ለሁሉም ጥያቄያቸውን በአንድ ጊዜ ማሟላት ስለማይቻል በሒደት መንግሥት ለችግሮቹ እልባት ያበጃል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012



