የውጭ ምንዛሬ እጥረት አሳሳቢው ሌላ ትኩሳት

0
1335

በተለያየ አቅጣጫ በተለያዩ ጉዳዮች ተወጥራ ያለችው ኢትዮጵያ፣ የምጣኔ ሀብቱ ነገርም ፈተና ሆኖ በሯን እያንኳኳና የዜጎቿን ኑሮም በእጅጉ እየፈተነ ይገኛል። ይልቁንም የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ዛሬን ብቻ ሳይሆን መጪውም በስጋት ዐይን እንዲታይ የሚገፋፋ ሆኗል። በሰሜኑ ክፍል የተነሳውን ጦርነት ጨምሮ፣ ለምንዛሬ እጥረቱ ምክንያት ተብለው በምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች የሚጠቀሱት ብዙ ናቸው።

የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ መንስኤዎች ምን ምን ናቸው፣ እጥረቱስ ምን አስከተለ እንዲሁም ወደፊት ምን ይበጃል የሚለውን ጥያቄ በማንሳት፣ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎችን በማነጋገር፣ የቀደሙ ዘገባዎችን እንዲሁም ጥናቶችን በማጣቀስ፤ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ነገር አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ራሱን ችሎ የቆመ አለመሆኑን ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ተጽዕኖ የማያጣው መሆኑን ከምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጀምሮ በመንግሥት የሚነሳ ጉዳይ ነው። አሁን አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተፈተነ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎች ይወጣሉ። ከመንግሥት ተቋማት እስከ ግሉ ዘርፍም ቀዳሚ ችግር መሆኑም መነገር ከጀመረ ሰነባብቷል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን የሚያመላክቱ መረጃዎች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ይወጣሉ። ችግሩ በመንግሥት ከሚሠሩ የልማት ሥራዎች እስከ ግል ሥራዎች እንዲስተጓጎሉ ምክንያት እየሆነ ነው።

የመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የ2014 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ ዕቅዳቸውን በአግባቡ ለመፈጸም እንደ እንቅፋት ካነሷቸው ችግሮች መካከል የውጭ ምንዛሬ እጥረት ዋነኛው ሆኗል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ በተጨማሪ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት መፈጸም የሚገባቸው ፕሮጀክቶች መፈጸም አለመቻላቸውን አብራርተዋል።

ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ በተጨማሪ፣ በርካታ የመንግሥት ተቋማትና የግል ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ባለመቻላቸው፣ በበጀት ዓመቱ የያዙትን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ እንዳይፈጽሙ እስከማድረግ የደረሰ ጉዳት እያስከተለ ነው። አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ሌሎች የመንግሥት ተቋማትን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የተመለከተች ሲሆን፣ መሥሪያ ቤቶቹ ካስቀመጧቸው ዋና ተግዳሮቶች መካከል የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቀዳሚውን ደረጃ ይዟል።

በተለይ ተጠቃሽ ከሆኑት ዘርፎች መካከል ግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማጋጠሙ የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር በግብርናው ዘርፍ፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በዕቅዳቸው ልክ እንዳይፈጽሙ እንቅፋት እንደሆነባቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት አስታውቀዋል።

ለአብነትም፣ ግብርና ሚኒስቴር የቆላ ዝንብ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚያደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ለኬሚካል ግዥ የሚውል ዶላር ጠይቆ ማግኘት አለመቻሉን ጠቁሟል። በዚህም በወቅቱ የኬሚካል ርጭት ማካሄድና የቆላ ዝንብ ጉዳትን ማስቀረት እንዳልቻለ ነው የጠቆመው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሌሎችንም የውጭ ምንዛሬ የሚስፈልጋቸውን ግዥዎች ለመግዛት መቸገሩን ለምክር ቤቱ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በበኩሉ፣ የዘጠኝ ወር ዕቅዱን በሙሉ አቅሙ እንዳይፈጽም የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ቀዳሚ እንቅፋት እንደሆነበት ለምክር ቤቱ አሳውቋል። ኮሚሽኑ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለማቃለል በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ትርፋቸውን ወደ ውጭ እንዳይወስዱ ጥረት እያደረገ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው። ኮሚሽኑ፣ ባለሀብቶቹ በተጨማሪ ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው የውጭ ምንዛሬው አገር ውስጥ ለማቆየት ጥረት እያደረገ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው የጸጥታ ችግርና አለመረጋጋት ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን ወደ ውጭ እንዲወስዱ ገፊ ምክንያት መሆኑ እንደቀጠለ ነው።

ኢትዮጵያ ወትሮውንም የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚያጣት ባትሆንም፣ ባለፉት ተከታታይ አራት ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል። የኢትዮጵያ ገበያ በውጭ ምንዛሬ ሁኔታ በቀጥታ የሚዘወር እየሆነ መጥቷል። ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ወይም ጥሬ ዕቃቸው ከውጭ የሚገባ ምርቶች በቀጥታ ከውጭ ምንዛሬ ጋር የተገናኙ መሆኑን ተከትሎ የሚፈጠረው ተለዋዋጭ የገበያ ሁኔታ፣ አጠቃላይ የገበያ ሁኔታውን መረበሽ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።

የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት መከሰት ኢትዮጵያ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ በጥቁር ገበያ ወይም ከባንክ ውጪ በሰፊ የምንዛሬ ልዩነት እንዲንሸራሸር እድል መክፈቱን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም ለዘፈቀደ አሰራሮች የተጋለጠና በሙስና የተዘፈቀ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ተንታኝና የፖሊሲ አማካሪው ቆንጠንጢኖስ በርሄ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

የውጭ ምንዛሬ ዝውውሩ በባንኮች በኩል መሆን ሲገባው ለጥቁር ገበያ የተጋለጠ መሆኑን ተከትሎ፣ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ከጥቁር ገበያ ጋር ሲነጻጸር፣ በአንድ ዶላር ከ20 ብር በላይ ልዩነት አለው። የጥቁር ገበያና የባንኮች ምንዛሬ ሰፊ ልዩነት ማሳየቱ ወደ ኢትዮጵያ እንደ አገር የሚገባውን የውጭ ምንዛሬ በአግባቡ እንዳትጠቀምና ዘርፉ ለሕገ ወጥ ዝውውር እንዲጋለጥ ምክንያት መሆኑን ቆስጠንጢኖስ ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬን ዝውውር በቁጥጥር ስር ለማዋል በየጊዜው የተለያዩ መመሪያዎችን ደንግጎ ተግባራዊ ቢያደርግም፣ ለውጥ አለማምጣቱን ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ብሔራዊ ባንክ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የኢትዮጵያ ባንኮች ከሸቀጦች እና አገልግሎቶች የወጪ ንግድ እንዲሁም ከሓዋላ ከሚሰበስቡት የውጭ ምንዛሬ 70 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስረክቡ መመሪያ መስጠቱ አንዱ ነው።

ባንኮች የሚሰበስቡትን የውጭ ምንዛሬ ለብሔራዊ ባንክ የሚያስገቡት ምጣኔ ከ30 ወደ 50 እያለ አሁን ላይ 70 ደርሷል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥር 2/2014 ይፋ የተደረገው መመሪያ፣ ከአራት ወራት ገደማ በፊት የነበረውን አሰራር የሻረ ነው። ባንኮች እጃቸው ከሚገባው የውጭ ምንዛሬ እስከ ነሐሴ 2013 ድረስ 30 በመቶውን ብቻ ለብሔራዊ ባንክ ሲያስረክቡ ቆይተዋል። በነሐሴ ወር ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መጠኑን ወደ 50 በመቶ ከፍ አድርጎት ነበር።

የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ምን አመጣው?
የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶ አሁን ላይ እንደ አገር የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ክምችት ከኹለት ወር በላይ እንደማያወላዳ መገለጹ የሚታወስ ነው። የውጪ ምንዛሬ እጥረቱ የውጭ ጥሬ ዕቃ የሚያስፈልጋቸውና አገር ውስጥ የሚመረቱ የኢንዱስትሪ ውጤቶች ምርት እንዲቀንስ፣ አለፍ ሲልም በመንግሥት የተያዙ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ ምክንያት ሆኗል።

የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች እንደሚያስረዱት፣ የውጭ ምንዛሬ ወይም የዶላር እጥረት የሚከሰተው አንድ አገር ከውጭ ምርቶች ከምታገኘው ገቢ የበለጠ ዶላር ስታወጣ ነው። ትኩረቱን የኢንቨስትመንት ጥናቶች ላይ አድርጎ የሚሠራው ኢንቨስቶፒዲያ የተባለ ተቋም፣ ከአንድ ዓመት በፊት ስለ ውጪ ምንዛሬ እጥረት ባስነበበው ጽሑፍ፣ “የአሜሪካ ዶላር በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ብዙ ሸቀጦችን ለመሸጫነት የሚውል በመሆኑ እና በብዙ ዓለም ዐቀፍ የንግድ ልውውጦች ላይ የሚውል በመሆኑ፣ የዶላር እጥረት የአንድን አገር እድገት እና የንግድ ልውውጥ አቅም ይገድባል” ይላል።

አብዛኞቹ አገሮች የውጭ ዕቃዎችን ለመግዛት፣ የአገሪቱን የምንዛሬ ተመን ለመቆጣጠር፣ ዓለም ዐቀፍ ዕዳ ለመክፈል ወይም ዓለም ዐቀፍ ግብይቶችን ወይም ኢንቨስትመንቶችን የሚያደርጉት በውጭ ምንዛሬ ተጠቅመው መሆኑን የኢንቨስቶፒዲያ ጽሑፍ ያመላክታል።
የምጣኔ ሀብት ተንታኙ ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት፣ መንግሥት ኤክስፖርትን አበረታታለሁ ብሎ የሚያደርጋቸው ነገሮች፣ የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀሙን ያለአግባብ እንዲወጣ እያደረገው ነው ይላሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ዶላር ያስገኛሉ ተብለው የሚታሰቡት እንደ ቡና እና ጫት የመሳሰሉ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች፣ የሚያገኙትን ዶላር ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ ስለሚጠቀሙበት እንደሆነ ያነሳሉ። ይህም እንደ አገር የውጭ ምንዛሬ እጥረት ላይ ከሚጥሉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው ይላሉ።

በሌላ በኩል የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ያስከተለው ብርቱ ቀውስ የውጭ ንግድን ጨምሮ በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ማሳደሩን ቆስጠንጢኖስ ያነሳሉ። በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ የሚያገኛቸውን ድጋፎችና ብድሮችን እስከማቋረጥና እስከማዘግየት የደረሰ በመሆኑ፣ ለውጭ ምንዛሬ እጥረት አንዱ ምክንያት እንደሆነ ያነሳሉ።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት፣ ኢትዮጵያ እንደ አጎዋ የመሳሰሉ ነጻ ገበያዎችን እንድታጣና ከአበዳሪ አካላት ብድር የማግኘት እድሏን ያጠበበ እክል ፈጥሯል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ አገራት የውጭ ንግዳቸው ሲስተጓጎልና ማዕቀቦችን ሲያስተናግዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይፈትናቸዋል። ኢትዮጵያም በዚህ መስመር ውስጥ እያለፈች መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በዋናነት የውጭ ምንዛሬ የምታገኘው ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች፣ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ ከዓለም ዐቀፍ ድጋፎችና ብድሮች እንዲሁም በውጭ ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች መሆኑን የባንክ ባለሙያው ዳንኤል ሽፈራው ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ከዓለም ዐቀፍ አበዳሪ አካላት የምታገኘው ብድርና ድጋፍ እንዲሁም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበት አመርቂ ባለመሆኑ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንድትፈተን ምክንያት ሆኗል ይላሉ።
የኢንቨስቶፒዲያ ጽሑፍ እንደሚያብራራው፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚከሰተው አንድ አገር ዓለም ዐቀፍ ንግዷን በብቃት ለመምራት የሚያስችል በቂ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ማግኘት ሳትችል ስትቀር ነው።

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው መንገዶች መካከል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አንዱ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በገጠማት ጦርነት የውጭ ባለሀብቶች ፍላጎት በእጅጉ ማሽቆልቆሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የማዕድን ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ሌላኛው ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበት መንገድ ከውጭ አበዳሪና ደጋፊ አካላት ቢሆንም፣ በሚፈለገው ልክ ላይገኝ እንደሚችል መንግሥት እየገለጸ ነው። በአንዳንድ ዘርፎች ላይ ደግሞ ከመደበኛ በጀት ላይ እስከ 40 በመቶ የሚሆን ቅናሽ እንደሚደረግ አብራርተዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የፖሊሲ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ዝግጅትን አስመለክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ የበጀት ጉድለትን ለመሙላት ከውጭ የሚገኘው ሀብት በታሰበው መጠን ላይገኝ ስለሚችል መንግሥት ከአገር ውስጥ ከሚመነጨው ሀብት ማለትም ከግምጃ ቤት ሰነድና ከሌሎች የአገር ውስጥ ምንጮች ለማሟላት የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነድፎ ተግባራዊ በማድረጉና በዛም አበረታች ውጤት በመገኘቱ፣ የበጀት ጉድለቱ የዋጋ ግሽበትን በማያባበስ ሁኔታ ለማሟላት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከውጭ በብድርና በድጋፍ የምታገኘው ሀብት ላይኖር እንደሚችል የሚያመላክቱ ምልክቶች በግልጽ መታየታቸው ትልቅ ስጋት መሆኑን የሚገልጹት የባንክ ባለሙያው ዳንኤል፣ ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ወደፊትም ሊቀጥል እንደሚችል አመላካች መሆኑን ይገልጻሉ።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚከሰተው አገራት በቂ የውጭ ምንዛሬ ሳያከማቹ ሲቀሩና የውጭ ምርት ሸማች ብቻ (Net Importer) ሊሆኑ እንደሚችሉ የኢንቨስቶፒዲያ ጽሑፍ ያብራራል። የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ በጣም ከከፋ፣ አንድ አገር የገንዘብ አቅሟን ለመጠበቅ እና ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል ከሌሎች አገራት ወይም ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች እርዳታ ልትጠይቅ ትችላለች።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ እንደሚደመጡት፣ የሰሜኑ ጦርነት ኢትዮጵያ ያላት የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን ነው። በዚህም የውጭ ንግድ መዳከም፣ በዕርዳታ እና በድጎማ ወይም በብድር የሚገኝ ውጭ ምንዛሬ መቋረጥና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበት መቀዛቀዝ ተጠቃሽ ናቸው።

ምን ያስከትላል?
የውጭ ምንዛሬ እጥረት በተለይ ሸማች ወይም የውጭ ምርት ተጠቃሚ ለሆኑ አገራት አጠቃላይ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብት ተንታኙና የፖሊሲ አማካሪው ቆስጠንጢኖስ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በዚሁ ከቀጠለ፣ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ። መንግሥት የውጭ ምንዛሬ አጥረቱን መፍትሔ ካልፈለገለት “መመለሻው ከባድ ነው” የሚሉት ባለሙያው፣ የውጭ ምንዛሬ ከሌለ ምንም ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ይገልጻሉ።

“ዕርዳታ ይመጣል አይመጣም ጥያቄ ውስጥ ነው” የሚሉት ቆስጠንጢኖስ፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ነዳጅ፣ ማዳበሪያና የምግብ ፍጆታዎችና የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎችን መግዛት የምትችልበት የውጭ ምንዛሬ የማታገኝ ከሆነ ችግሩ የከፋ ነው ይላሉ።
ቆስጠንጢኖስ የገለጹት ስጋት አስቀድሞ መከሰቱን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ለ2014/2015 የምርት ዘመን 20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት አቅዶ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መግዛት የቻለው 12 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ብቻ ነው። የተገዛው አፈር ማዳበሪያ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር የስምንት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ቅናሽ ያለው ሲሆን፣ በ2013/2014 የምርት ዘመን ከተገዛው ጋር ሲነጻጸር የአምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ቅናሽ አለው። ግብርና ሚኒስቴር በ2013/2014 ምርት ዘመን 17 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ ነበር።

የባንክ ባለሙያው ዳንኤል በበኩላቸው፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የአገር ውስጥ ገበያ እንዳይረጋጋና የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የምርት አቅርቦት ከተከሰተ በቀጥታ ወደ ዋጋ ግሽበት እንደሚሸጋገር በማንሳት ነው።

“ዞሮ ዞሮ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አጠቃላይ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይና በሕዝቡ ኑሮ ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል የሚባል አይሆንም” የሚሉት የባንክ ባለሙያው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው የዋጋ ግሽበት አባባሽ ምክንያት ሆኖ እንደሚቀጥል ይገልጻሉ።
ኢንቨስቶፒዲያ በጽሑፉ ላይ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የተከሰተባቸው አገራትን በምሳሌነት ይጠቅሳል። በምሳሌነት ከተጠቀሱ አገራት መካከል፣ እ.ኤ.አ. በ2017 መጨረሻ እስከ 2018 መጀመሪያ ድረስ፣ በሱዳን ያለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሱዳን ገንዘብ እንዲዳከም ማድረጉን ተከትሎ፣ የዋጋ ግሽበት በፍጥነት እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን ያወሳል።

“የዳቦ ዋጋ በአንድ ሳምንት ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል” የሚለው ጽሑፉ፣ ኢኮኖሚዋ ቀድሞውንም በአዲስ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎች ላይ በነበረችው ሱዳን ተቃውሞና ብጥብጥ ማስነሳቱን ያትታል። ሁኔታው ከአንድ ዓመት በኋላም መሻሻል አለማሳየቱን ተከትሎ የሱዳን ፓውንድ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዲወድቅ አድርጎት እንደነበር ያስታውሳል።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ኹለቱም ባለሙያዎች የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ የኢትዮጵያ የብር ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲወርድ እያደረገው መሆኑን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ብር ደረጃ ዝቅ እንዲል ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዘፈቀደ አሰራር ነው የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ ሁኔታው ብርን ዋጋ አሳጥቶታል ይላሉ። የብር ዋጋ ማጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ዋጋ ግሽበት እንዲቀጣጠል ምክንያት እንደሚሆን የባንክ ባለሙያው ዳንኤል ይገልጻሉ።

ችግሩ ምን ይሻል?
የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚያስከትላቸው ጫናዎች አሳሳቢ መሆናቸውን የሚገልጹት ቆስጠንጢኖስ፣ መንግሥት የውጭ ምንዛሬን ጉዳይ ችግር አባባሽ በሆነ መንገድ ሳይሆን ችግር ፈቺ በሆነ መንገድ ማስተካከል እንዳለበት ይመክራሉ። የውጭ ምንዛሬ አሰራር በዘፈቀደ የሚሠራ አይደለም የሚሉት ቆስጠንጢኖስ፣ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ምን ይደረግ? በሚለው ጉዳይ ላይ የሚነጋገርበት ጊዜ አሁን ነው ይላሉ።

ለውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የሆነውን ችግር ለይቶ “መንግሥት አንድ ሥርዓት ማስያዝ አለበት” የሚሉት ቆስጠንጢኖስ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት አድርጎ የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ እንዳለበት ይመክራሉ። የውጭ ምንዛሬ ዝውውሩና ስርዓቱ በሙስና የተዘፈቀ መሆኑንም ባለሙያው ያነሳሉ። በመሆኑም በሕገ ወጥ መንገድና በዘፈቀደ እየባከነ ያለውን የውጭ ምንዛሬ በአግባቡ ለመጠቀም የመንግሥት ጥብቅ ቁጥጥርና ስርዓት ያስፈልጋል ብለዋል።

የባንክ ባለሙያው ዳንኤል በበኩላቸው፣ የተፈጠረውን የውጭ ምንዛሬ ችግር ለማረጋጋት በቅድሚያ ኢኮኖሚውን የተጫነውን ፖሊቲካዊ ችግር እልባት መስጠት እንደሚገባ ይገልጻሉ። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ እንደ የውጭ ንግድን ለማጠናከር፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የውጭ ብድርና ድጋፍ ለማግኘትና ዳያስፖራው ገንዘቡን በባንክ ወደ ኢትዮጵያ እንዲልክ ለማድረግ እንቅፋት የሆነው ጦርነት እልባት ማግኘት አለበት ባይ ናቸው።

ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። በመንግሥት በኩል የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ባንኮች ክፍት ለማድረግና የካፒታል ማርኬት ለመጀመር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ያግዛሉ ይላሉ። ኢትዮጵያ ለውጭ ባንኮች በሯን ከከፈተች በኋላ የጎረቤት አገር ባንኮች ቢገቡ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ እምብዛም ለውጥ እንደማያመጡ የሚገልጹት ቆስጠንጢኖስ፣ አቅም ያላቸው ባንኮችን መሳብ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀምን በጥብቅ ቁጥጥርና ስርዓት ላይ የተመሠረተ አሰራር በመዘርጋት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ፕሮጀክቶችና ግዢዎች ትኩረት በመስጠት አባካኝነትን መቀነስ እንደሚገባ ቆስጠንጢኖስ ይገልጻሉ። እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ካልሆኑ በስተቀር፣ ለፕሮጀክቶች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ መቆጠብ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የ2015 በጀት ዓመት በጀትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ በ2015 በጀት ዓመት አዳዲስ ካፒታል ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደማይደረጉ አስታውቀዋል። በጅምር የሚገኙ የካፒታል ፕሮጀክቶች በአነስተኛ ወጪ እንዲጠናቅቁ የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የ2015 በጀታቸውን ባስገመገሙበት ወቅት ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here