ሦስተኛው ዙር የህዳሴው ግድብ ሙሌት በሐምሌ ወር እንደሚጀመር ተገለጸ

0
1659

የኹለተኛው ተርባይን ፍተሻም ተጀምሯል ተብሏል

ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ለመጀመሪያ ጊዜ ኃይል ማመንጨት ከጀመረ ሦስት ወራት ያለፉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት፣ ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ መከናወን እንደሚጀምር ታዉቋል፡፡

ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ ወደ ግድቡ የሚፈሰው የውኃ መጠን፣ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ከፍ እያለ ከሄደ በኋላ ወደ ግድቡ የሚገባውን ውኃ በመያዝ፣ በሐምሌ ወር ሙሌቱ እንደሚጀመር ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመት ወደ ግድቡ እንዲገባ የሚጠበቀውን የውኃ መጠን ለመያዝ የግድቡን ቁመት የመጨመር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ የውኃ ሙሌቱ ሲጀመር የግድቡ ቁመት በሚፈለገው መጠን እንደሚደርስ አስረድተዋል፡፡

ከክረምቱ መግባት በኋላ ባሉት ወራት የሚኖረው የውኃ መጠን የሚለያይና እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ፣ ከፍተኛው የውኃ መጠን የሚታየው በነሐሴ ወር ነው ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከሐምሌ ጀምሮ የሚፈለገው የውኃ መጠን ተይዞ፣ በነሐሴ ወር ውኃው በግድቡ ላይ ይፈሳል ሲሉ ያላቸዉን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ኹለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በሰኔ ወር መጨረሻ ሲጀመር፤ በነሐሴ ወር አጋማሽ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፣ በዓመቱ በነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ፍሰት የተነሳ መጠናቀቁ የተበሰረው ሐምሌ 12 ቀን 2013 ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው የ2014 የክረምት ወር ትንበያ፣ አብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር አሳይቷል፡፡

በዚህ ዓመት ምን ያህል የውኃ መጠን ለመያዝ እንደታቀደ ባይገለጽም፣ መንግሥት ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ምን ያህል ውኃ ለመያዝ ማቀዱን አስታውቆ ነበር፡፡

ሙሌቱ በተጀመረበት 2012 የግድቡ ቁመት 565 ሜትር ሆኖ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውኃ መያዙ መገለጽ የሚታወስ ሲሆን፣ በቀጣዩ ዓመት የግድቡን ቁመት 595 ሜትር በማድረስ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ለመሙላት ታቅዶ ነበር፡፡ ይህም ሙሌቱ በተጀመረ በኹለተኛው ዓመት ግድቡ የሚይዘውን የውኃ መጠን 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚያደርስ ነው፡፡

በሦስተኛው ዓመት ላይ የግድቡን ቁመት 608 ሜትር ከፍታ ላይ በማድረስ 10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመሙላት፣ አጠቃላዩን የውኃ መጠን 28 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የማድረስ ውጥን እንዳለ ዕቅዱ ያመላክታል፡፡ የህዳሴው ግድብ አጠቃላይ ውኃ የመያዝ አቅም 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደሆነ በተደጋጋሚ መገለጹ አይዘነጋም፡፡

ባለፈው ዓመት የተደረገው የውኃ ሙሌት መጠናቀቅ ሲበሰር የውኃው መጠን ሁለት ተርባይኖችን ማንቀሳቀስ የሚችል እንደሆነ ተገልጾ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል አንዱ የካቲት 13 ቀን 2014 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል፡፡

የህዳሴው ግድብ ኹለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት እንዲጀምር የፍተሻ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከፍተኛ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

ከአንድ ወር ከግማሽ እስከ ኹለት ወራት ባለ ጊዜ ውስጥ ኹሉንም የፍተሻ ሥራዎች አጠናቆ ኃይል ማመንጨት ማስጀመር እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

ኃይል ማመንጨት የጀመረው አንዱ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተነግሮ የነበረ ሲሆን፣ ኹለተኛውም ተርባይን ተመሳሳይ የማመንጨት አቅም እንዳለው ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here