ፕሮጀክቱ በቀጣይ በአፋር እና ትግራይ ክልሎች እንደሚተገበርም ተገልጿል
ዕረቡ ሰኔ 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ የሚውል የ145 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል።
ፕሮጀክቱ በቀጣይ ኹለት ዓመታት ውስጥ የሚተገበር ሲሆን፤ ኸርማን ገማንደር ፈንድ ደችላንድ ከተሰኘና በጀርመን አገር ከሚገኝ የኤስ ኦስ ኤስ ድርጅት በተገኘ የ4 ሚየሊን ዩሮ ድጋፍ እንደሚተገበር በኢትዮጵያ የኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሳህለማርያም አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት ከሆነ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ኤስ ኦ ኤስ ድርጅቶች የ6 ነጥብ 72 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የተጠየቀ ቢሆንም፤ ለጊዜው ከኸርማን ገማንደር ፈንድ ደችላንድ በተገኘው የ4 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ዕቅድ ተይዟል።
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል በሚደረግ የ145 ሚሊየን ብር ወይንም የ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ይጀመር እንጂ፤ በቀጣይ በትግራይ እና አፋር ክልሎች ለሚገኙ እና በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ቀሪው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ተደራሽ እንደሚሆን ሳህለማርያም ጨምረው አስረድተዋል።
በዚህም መሰረት በሰሜን ሸዋ፣ በሰሜን ወሎ፣ አድዋ፣ መቀሌ እና ምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች አስተባባሪ የሆኑት ቢኒያም አስፋው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በክልሎቹ በተሰራ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ላይ ተመስርቶ መቀረፁን የተናገሩት ቢኒያም፤ ድጋፉም በክልሎቹ ለሚገኙና አስቸኳይ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው የተመረጡ ወረዳዎች ለሚገኙ ሰዎች፤ የምግብ እርዳታ፣ የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ፣ የትምህርት መገልገያ መሳሪያዎች ድጋፍ እንዲሁም ለገበሬዎች ዘር እና ለእርሻ የሚውሉ በሬዎች ማቅረብን እንደሚያካትት ገልፀዋል።
በፕሮጀክቱ በአማራ ክልል ለሚገኙ ከ231 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የገለፁት ቢኒያም፤ በክልሉ በተመረጡት አካባቢዎች ላይ የሚሰሩት ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኃላ በሚገኙ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፎች በአፋር እና ትግራይ ክልሎች ላይ ድጋፍ የማድረሱ ሥራ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዳሬክተር ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው፣ የሲቨል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገራችን ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ከኹሉም በመቅደም የማህበረሰቡን ጥቅምና ፍላጎት ለሟሟላት የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ፤ ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር በኢትዮጵያ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚያደርገው ጥረት እጅግ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ፋሲካው አክለውም በአትዮጵያ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከ 2 ሺህ በላይ አዳዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸውን ገልፀው፤ ከዛ በፊት ከነበሩት 1 ሺህ 800 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ከ3 ሺህ 800 በላይ በጎ አድራጊ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገራችን እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
እነዚህም ድርጅቶች በአገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸውና በአፋር እና በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ባደረጉት ጥረት፤ ከ 440 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ድጋፍ በባለስልጣኑ በኩል አድርገዋል ሲሉም ፋሲካው ተናግረዋል፡፡
ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር በ1967 በኢትዮጵያ የተከሰተዉን ድርቅ ተከትሎ መንግስት ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ባደረገው ጥሪ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ደርጅት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በ7 የክልል ከተሞች ውስጥ 24 ያህል ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።



