ዕረቡ ሰኔ 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ መዓዛ መሐመድ እና ሰለሞን ሹምዬ ላይ የቀረበውን ይግባኝ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ሐሙስ ሰኔ 2 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በዛሬው ችሎት፤ ለሦስቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በስር ፍርድ ቤት የተፈቀደው ዋስትና ውድቅ እንዲደረግ እና 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የፖሊስ ኮሚሽኑ መርማሪዎች በዛሬው ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተጠረጠረበት “ሁከት እና ብጥብጥ ማነሳሳት” ወንጀል ወደ “ሽብር ወንጀል” ሊቀየር እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። መርማሪዎቹ ይህን ያሉት ተመስገን የተጠረጠረበት ወንጀል ውስብስብ መሆኑን ለፍርድ ቤት ባስረዱበት ወቅት ነው።
መርማሪ ፖሊሶቹ ተመስገንም ሆነ ሌሎቹ ኹለት ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል “ውስብስብ፣ በአገር ላይ እና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ ነው” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ባስገቡት ማመልከቻ ጠቅሰዋል። ከዚህ አንጻር ምርመራው “ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ” በመሆኑ እና ምርመራውን በስፋት እስኪያጣሩ ድረስ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው የስር ፍርድ ቤት መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።
ሆኖም የስር ፍርድ ቤቱ ትላንት ማክሰኞ ግንቦት 30 ቀን 2014 በዋለው ችሎት ለእያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች የ10 ሺህ ብር ዋስትና መፍቀዱን እንደሚቃወሙ መርማሪዎቹ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ገልጸዋል። መርማሪ ፖሊሶቹ የምርመራ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ይረዳቸው ዘንድ ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን መጠየቃቸውን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።
የፖሊስን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄ አጥብቀው የተቃወሙት የተጠርጣሪ ጠበቆች፤ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የስር ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን የዋስትና ትዕዛዝ እንዲያጸና ጥያቄ አቅርበዋል።
ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ይግባኝ እና የጠበቆችን ምላሽ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ሐሙስ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ ማጠናቀቁም ታውቋል።



