ጅማ ዩኒቨርሲቲ የተመረተው አፈር መመርመሪያ መሣሪያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አገኘ

0
1008

ዕረቡ ሰኔ 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተማሪዎች የተሠራውና አፈር መርምሮ ምን ቢዘራ አዋጭ እንደሆነ የሚለው መሣሪያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቷል።

መሣሪያው ከሌሎች በጅምር ላይ ካሉ ኩባንያዎች ጋር በኡጋንዳ፣ ካምፓላ ተወዳድሮ አንደኛ ደረጃን በመያዝ የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት ማግኘቱም ነው የተገለፀው።

ይህ በዓለም አቀፍ መድረክ ዕውቅና ያገኘው ‘ኦሚሽቱ-ጆይ’ ተብሎ የተሰየመው አፈር መመርመሪያ መሣሪያ ከጥቂት ዓመታት በፊት በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተማሪዎች የተሠራው ነው።

አነስተኛ መጠን ያለው መሣሪያው፣ በአፈር ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮች በመመርመር በዛ አፈር ውስጥ የትኛው ተክል ቢተከል ወይም የትኛው ዘር ቢዘራ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ይለያል ተብሏል።

ኦሚሽቱ-ጆይ በዓለም ባንክ በሚደገፈው ‘Africa Start Up Award’ ውድድር ከ23 አገራት ከተወጣጡ ሥራዎች ጋር ተወዳድሮ ነው በአንደኛነት በማጠናቀቁ ሽልማቱን የተረከበው።

መሣሪያው የአፈርን የንጥረ ነገር ይዘት፣ የሙቀት መጠን (ቴምፕሬቸር) እና እርጥባማነት ለይቶ ውጤቱን ወደ ስማርት ስልኮች ይልካል።

2013 ላይ ተማሪዎች ለመመረቂያ ፕሮጀክት ያነሱት ጽንሰ ሐሳብ በመምህራን ተደግፎ ከዚህ መድረሱን በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩተር ሳይንስ መምህር ጃርሚያ ባይሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአንድ አካባቢ ዘር ከመዘራቱ በፊት አፈሩ ለየትኛው የዘር ዓይነት ምቹ እንደሆነ መለየት መቻል የምርት ውጤትን ከፍ ያደርጋልም ተብሏል።

መምህር ጃርሚያ ‘ኦሚሽቱ-ጆይ’ ሲል የሰየመው መሣሪያ፣ የአፈር ናሙና ከወሰደ በኋላ በአፈሩ ላይ ምርመራ አካሂዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአፈሩ ውስጥ ያለውን አሲድ፣ ንጥረ ነገሮች እና እርጥበት በመለየት ውጤቱን ወደ ሞባይል ስልክ ይልካል በማለት አስረድተዋል።

መሣሪያው የረቀቀውን ሰው ሠራሽ ልኅቀት ቴክኖሎጂ (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) ከመጠቀሙም በላይ መጠኑ አስተኛ በመሆኑ ሰዎች በቀላሉ ከቦታ ቦታ ይዘውት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ጃርሚያ ገልፀዋል።

ማንበብ እና መጻፍ የማይችሉ ሰዎችም መሣሪያውን በቀላሉ መጠቀም እንዲችሉ ጆይ-ኦሚሽቱ ትዕዛዝ በድምጽ ተቀብሎ የምርመራ ውጤቱን በድምጽ መግለጽ እንዲችል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንንም ተናግረዋል።

“አንድ አርሶ አደር ስማርት ስልክ ካለው በድምጹ አዝዞ ውጤቱንም እንዲሰማ ለማድረግ እየሠራን ነው” ሲሉም መምህሩ ገልፀዋል።

“ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ሶማሊኛ እና ትግርኛ በአጠቃላይ በአምስት ቋንቋዎች እየሠራን ነው። በደቡብ ክልል ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል ኹለት ቋንቋዎችን ለመጨመርም አስበናል” ሲሉም ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የአርሶ አደሩን የግብርና ምርታማነት ለመጨመር ኦሚሽቱ-ጆይ መሣሪያን በብዛት ለማምረት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ መሣሪያውን ለማምረት የሚረዱ ኮምፒዩተሮች እና ግብዓቶችን ከውጪ ማስመጣት ግን እንቅፋት እንደሆነባቸው ይገልጻሉ።

“መሣሪያውን ለማምረት የሚያገለግሉ ግብዓቶች በውጪ አገራት በቀላሉ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እነዚህን እቃዎች ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አስቸጋሪ ሆኗል” ሲሉም አስረድተዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here