በአዲስ አበባ ከታሰሩት እስካሁን ያልተፈቱ አሉ

0
481

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ወደ አገር መመለሱን ተከትሎ መስከረም 5/2011 ከተደረገው የአቀባበል ሥነ ስርዓት ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ በተነሳው ሁከት ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ ያልተፈቱ ግለሰቦች ይገኛሉ ተባለ።
በኦነግ አቀባበል ወቅት በተቀሰቀሰ ሁከት በመዲናችን አዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ግጭቶች መከሰታቸው እና የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ መውደቁ ይታወሳል። ከተከሰተው ሁከት ጋር ተያይዞ ከአዲስ አበባና በዙሪያዋ ከሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር ይታወሳል። ከእነዚህም ውስጥ 1,174 የሚሆኑ የአዲስ አበባ ወጣቶች በጦላይ ማሠልጠኛ ትምህርት ከተሰጣቸው በኋላ መለቀቃቸው ይታወሳል። ነገር ግን በዚሁ ጉዳይ ተጠርጥረው እስከ አሁን ድረስ ካለመፈታታቸው በላይ፥ መደበኛ ክስ ያልተመሠረተባቸው ስምንት ግለሰቦች እንዳሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አዲስ አበባ ከተማ ፒያሳ አካባቢ በቁጥጥር ሥር የዋሉት መርጋ ፍቃዱ እና ግርማ ፍቃዱ የተባሉ የዪኒቨርሲቲ መምህራን እንደሚገኙበት ምንጮቻችን ገልጸዋል። ግለሰቦቹ መስከረም 10 ቀን በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን መስከረም 14 ቀን ፍርድቤት ቀርበዋል።
ግለሰቦቹ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀርበው ለፖሊስ 28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን፥ ከ28 ቀን በኋላ በድጋሜ ሲቀርቡም ተጨማሪ 28 ቀን ተጠይቆባቸው ፍርድ ቤቱም ይህንኑ ቀን መፍቀዱን የተጠርጣሪዎቹ የቅርብ ወዳጆች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እነኚህ ግለሰቦች የተጠረጠሩበት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ በመሻሻል ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ሥር የተመለከቱትን የወንጀል ድንጋጌዎች የሚተላለፉ ድርጊቶችን ፈፅሟል በሚል ተጠርጥሮ ለሚፈለግ፣ በምርመራ ላይ ላለ፣ የወንጀል ክስ ለተመሠረተበት ወይም የጥፋተኝነት ፍርድ ውሳኔ ለተላለፈበት ሰው ምሕረት የሚሰጥ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል። ይህ የምሕረት አዋጅ ተፈፃሚ የሚሆነው ከግንቦት 30/2010 በፊት በሕጉ በተዘረዘሩ የተለያዩ ወንጀሎች በሚጠየቁ ግለሰቦች ላይ ብቻ መሆኑ ታውቋል።
መርጋ ፍቃዱ እና ግርማ ፈቃዱ ታኅሣሥ 1/2011 ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here