ከማንነት ጥያቄዎች በስተጀርባ ኢሕአዴግ . ሕገ መንግሥት . ብሔርተኝነት

0
1042

የማንነት ጥያቄ በኢትዮጵያ ካሉ የፖለቲካ አጀንዳዎች ሁሉ ቁንጮ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለመሆኑ የማንነት ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? ለጥያቄዎቹ መልስ የሚሆን መፍትሔስ እንዴትና ከወዴት ማግኘት ይቻላል? እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ስንታየሁ አባተ የተለያዩ ማሳያዎችን በማቅረብ እንዲሁም ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞችን በማነጋገር ርዕሰ ጉዳዩን በሐተታ ዘ ማለዳ እንደሚከተለው ቃኝቶታል።

አረጋሽ ሽግሬ የ67 ዓመት አዛውንት ናቸው፤ መስከረም 5/2011 ከሰዓት በኋላ ከስድስት ዓመት በፊት ገዝተው ኑሯቸውን በመሠረቱበትና ቡራዩ በሚገኘው ቤታቸው አገር አማን ብለው ከጎረቤቶቻቸው ጋር ቡና እየጠጡ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዕለቱ ባለቤታቸው ከቤት ወጣ ካሉ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በአቅራቢያው የተሰማ ኡኡታ የቡና ወጋቸውን ያቋረጣቸው አዛውንት ወደ ውጭ ብቅ ሲሉ ባለቤታቸውን በግምት 20 የሚሆኑ ወጣቶች እየተፈራረቁ እጅና እግራቸውን ሲደበድቧቸው አስተዋሉ። የባለቤታቸውን ሞት አፋፍ ላይ መሆን የተረዱት አዛውንት በድንጋጤ ሩጫ ወደ ቤት ውስጥ ገቡ። በመሐልም እግራቸውን በተወረወረ ድንጋይ ተመተው በሰዎች አጋዥነት ወደ አዲስ አበባ ሸሽተው መምጣታቸውን ይናገራሉ። ባለቤታቸው ደግሞ ወደ ሆስፒታል ስለመወሰዳቸው ሰምተዋል። የጋሞ ተወላጅ መሆናቸውን የሚናገሩት አዛውንቷ ጥቃቱ የተፈፀመው ዘርን ወይም የብሔር ማንነትን መሠረት አድርጎ እንደሆነ ነው የሚያምኑት፤ ምክንያታቸው ደግሞ የድብደባና ግድያ ጥቃቱ የተፈፀመው ቤት እየተመረጠ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
በቡራዩው ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች እንደሞቱ መንግሥት ሲያምን፣ የአካል ጉዳት፣ ንብረት ውድመት የደረሰባቸውና የተፈናቀሉ ሰዎች በርካታ እንደነበሩም ይታወሳል። በኢትዮጵያ ማንነትን መሠረት ባደረጉ ግጭቶች ካጋጠሙ የዜጎች ሞት በተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺሕ (ግማሾቹ ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለሳቸውን መንግሥት አስታወቋል) ኢትዮጵያዊያን መፈናቀላቸውን የመንግሥትና የዓለም ዐቀፍ ተቋማት ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ግጭቶችና መፈናቀሎቹ የሚደርሱትም አንድም ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ካሉበት ሥፍራ ለቀው እንዲወጡ በተለያዩ ወገኖች በሚደረግ ግፊትና ጥቃት፣ በክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በሚነሳ የመሬት ባለቤትነት ይገባኛል ውዝግብ እና የማንነት ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖች የአደባባይ ሰልፍ የክልል መንግሥታት የሚወስዱት እርምጃ እንደሆነ ነው የሚገለጸው።
ማንነት ምንድን ነው?
በተለያየ አጋጣሚ ሰዎች ‹በማንነታችን ምክንያት ተጨቁነናል፣ ጥቃት ደርሶብናል፤ ማንነታችን አልተከበረልንም› ይበሉ እንጂ ‹ማንነት ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ከአገራዊ ማንነት የተለየ የብሔር ማንነት አለ ወይስ የለም?› የሚሉ መከራከሪያዎች አሉ።
ማንነት በግለሰብ ደረጃ ሲታይ ማን ፈጠረኝ? ለምንስ ተፈጠርኩ? ወዴትስ እሔዳለሁ? ወዘተ… ለሚሉ የተዛነቁ ጥያቄዎች በእምነት፣ በባሕል፣ ወይም በሌላ መንገድ መልስ ሲበጅለት የሚፈጠር እሳቤ እንደሆነ የሚገልጹ ወገኖች አሉ። ማንነት ከትንሽ ቡድን እስከ አገር በለው እርከን ውስጥ ደግሞ እነዚህን ግለሰባዊ የማንነት እሳቤዎች አሳልፎ ምን አንድ አደረገን? ምን ያመሳስለናል? ልዩነታችንስ ምንድነው? ምን የጋራ የሆኑ እሴቶችና መልኮች (ከአካላዊ ገጽታው የሚሻገር) አለን? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ተመልሰው የሚገነባ የወል እሳቤ ወይም ጋርዮሽ ነውም የሚሉ አሉ። ማንነት ዓይነተ ብዙ ነው።
የማንነት ጥያቄዎችን በተመለከተ ፍራንሲስ ፉኩያማ እ.አ.አ. በ2018 ባሳተሙት ‹Identity: the demand for dignity and the politics of resentiment› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው የማንነት ጥያቄን በሦስት መደብ ሊያስቀምጡት ይሞክራሉ። የመጀመሪያው ‹ታይሞስ› በማለት የጠሩት ሲሆን፣ ሰብአዊ ክብራቸው ዕውቅና እንዲያገኝላቸው የሚፈልጉ የማንነት ቡድኖችን የለዩበት ነው። ሁለተኛው፣ ‹አይሶታይሚያ› ያሉት ሲሆን፣ ከሌሎች ጋር በእኩል ደረጃ መታየት የሚፈልጉ የማንነት ቡድኖችን የለዩበት ነው። ሦስተኛው ‹ሜጋሎታይሚያ› ያሉት ሲሆን፣ የሌሎች ሁሉ የበላይ ሆነው መታየት የሚፈልጉ የማንነት ቡድኖችን የለዩበት ሥያሜ ነው።
በኢትዮጵያ በርካታ የማንነት ጥያቄ ናቸው በሚል የሕዝባዊ አመፅ እንዲሁም የግጭት መንስዔ የሆኑ ንቅናቄዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ “የማንት ጥያቄ አለን” በሚል የሚንቀሳቀሱ የራያ ተወላጆች ይገኙበታል። የራያ ሕዝብ ማንነትን የሚመለከተው “ባሕልን፣ ታሪክን እና እሴትን ማሳደግና በዚያም መኩራት ብቻ አይደለም፤ ማንነትን፣ ታሪክንና ባሕልን ከምትጋራው ሰው ጋር መኖርና ከሚመስልህ ጋር እጣ ፈንታን ማስተሳሰርም ጭምር” አድርጎ እንደሆነ የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢው አግዘው አዳሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ማንነት በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት
ኅዳር 29/1987 የፀደቀው ሕገ መንግሥት ከአገራዊ ማንነት ባሻገር የብሔር ማንነት እንዳለ የሚጠቁም ቢሆንም ብሔር በራሱ ምንድነው? ከብሔረሰብና ሕዝብ ጋር ያለው ተመሳስሎና ልዩነትስ? ጎሳ? ነገድ? ዘውግ ከሚሉት ጋርስ እንዴት ይታረቃል? ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች ስናነሳ በቃላቱ ላይም መግባባት አለመደረሱን ያመለክታል።
የሕገ መንግሥቱ መገቢያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ኢትዮጵያን ተሳስረው የሚኖሩባት እንሆነች በመጥቀስ መጪው የጋራ ዕድላቸው መመሥረት ያለበትም ከታሪክ የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆን እንዳለበት አምነው ሕገ መንግሥቱን ስለማፅደቃቸው ያትታል።
ከእኔ በፊት በነበሩ መንግሥታት የብሔር ጭቆና ነበር፣ ሰዎች በብሔራቸው እንዲሸማቀቁ ሲደረግም ነበር የሚለው የኢሕአዴግ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ እነዚህ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ይላል። እንዲያውም ኢትጵያዊያን በብሔራቸው እንዲኮሩ ከማድረግ ባለፈ በአንቀጽ 39 የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር እስከመገንጠል የደረሰ ነጻ መብት የተሰጣቸው መሆኑንም ይጠቅሳል፤ ምንም እንኳን ይህ አንቀፅ እስካሁን መግባባት ላይ ባይደረስበትና የውዝግብ መነሻ ቢሆንም።
በሕገ መንግሥቱ በታሪክ የተወረሰው የተዛባ ግንኙነት ታርሞ የጋራ ጥቅም ማሳደግ ላይ ይሠራል ይባል እንጂ፣ ዛሬም ኢትዮጵያ የልዩነት ጥያቄዎች የከረሩባት፣ ብሔር ወይም ሞት እሰከማለት የተደረሰባት ነች የሚሉ አሉ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ በኢትዮጵያ ከአገራዊ ማንነት ይልቅ የብሔር ማንነት መገንገኑ የግጭት መንስዔ መሆኑን ሲገልጹ ይደመጣል። ከዚህ ቀደም የነበሩ የኢሕአዴግ መሥራቾች “ኩሩ ኦሮሞ ሆኖ ኩሩ ኢትዮጵያዊ፣ ኩሩ አማራ ሆኖ ኩሩ ኢትዮጵያዊ፣ ወዘተ. መሆን ይቻላል” በማለት የብሔር ማንነት ለኢትዮጵያዊያን ኩራት እንጂ የግጭት መንስዔ ሊሆን እንደማይችል በተደጋጋሚ ሲያነሱ ነበር። ለግጭት መንስዔ የሚሆነው የብሔሮች ጥያቄ ከታፈነ ነው በሚልም ሲከራከሩ ይስተዋላል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊው አንዳርጋቸው ጽጌ “ኩሩ ትግሬ ሆኖ ኩሩ አትዮጵያዊ መሆን ይቻለል” የሚለው አባባል የሚሠራው ብሔራዊ ዕድገታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰ፣ የበሰለና በምክንያት የቆመ የሕዝብ ዕውቀት ባለበት፣ ብሔራዊ ክልሎቻቸው በግልጽ የታወቁና አንዱ በሌላው ላይ የይገባኛል ጥያቄ የማያነሳባቸው ድንበሮች ባሉበት፣ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ምጣኔ ሀብት የተሻገሩ እንዲሁም ለሁሉም በእኩል የሚሠሩ ነጻ የፍትሕ፣ የጦር፣ የፖሊስ፣ የስለላና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ባሉበት አገር እንደሆነ ያሠምሩበታል። በዚህ መመዘኛ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱም የለም ብለው የሚያምኑት አንዳርጋቸው የኢሕአዴግ ፖለቲካ ድርጅቶችም በደምና ዘር ጥራት ላይ ያተኮሩ ዘውጌ ድርጅቶች እንጂ የብሔር ድርጅቶች አይደሉም ይላሉ። ለዚህም ነው ስለ ብሔራዊ ክልል ሲወራ ከዘውጌ ማኅበረሰብ አባላት ውጪ ያሉትን ቢቻል ከከልሉ ለማፅዳት ካልሆነም ከክልሉ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ሲያገልሉ የሚስተዋለውም ይላሉ።
ግንቦት 9/2010 በሸራተን አዲስ ሆቴል “ብሔራዊ ማንነትና አገራዊ አንድነት፣ ሕዝባዊ ምክክር መድረክ” በሚል ተዘጋጅቶ በነበረው ሁነት አብዛኖቹ ተሳታፊዎች ሲያነሱት የነበረውም በኢሕአዴግ ዘመን ከኢትጵያዊነት ይልቅ የብሔር ማንነት የበለጠ አጀንዳ ሆኖ ስለተሠራበት አሁን አገሪቱ ችግር ውስጥ ገብታለች የሚል ነበር። በተለይም የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር የሽዋስ አሰፋ የክልል ሕገ መንግሥታት ‹ክልሉ የእነ እከሌ ብሔሮች ነው፤ ከዚህ ውጭ ያሉት ግን መኖር ይችላሉ› ማለታቸው ዛሬ ላይ ለሰዎች በማንነታቸው መፈናቀልና የብሔር ተኮር ግጭቶች መብዛት ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ። ይህን ሐሳብ የሚደግፉ የፖለቲካ ፓርቲ የበላዮችም በኢትዮጵያ ከግለሰብ ይልቅ ለቡድን መብት ቅድሚያ በመሰጠቱ ችግሮች በርክተዋል ሲሉ ተደምጠዋል።
በረከት ስምዖን “ትንሳኤ ዘ ኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 86 ላይ ሕገ መንግሥቱ “የዜጎች መብት ካልተከበረ የማኅበረሰቦች መብት ሊከበር፣ የማኅበረሰቦች መብት ባልተከበረበትም የግለሰብ መብት ሊከበር አይችልም በሚል አስተሳሰብ፣ ሁለቱንም ሳይነጣጥልና በምሉዕነት በማክበር መርሕ ላይ የተዋቀረ ነው” ሲሉ አስፍረዋል። እንደ በረከት እምነት በኢትዮጵያ የተገነባው ሕገ መንግሥታዊ ዴሞከራሲም በሌሎች አገራት ባልተለመደ መልኩ ለቡድን መብቶች በተለይም ለብሔር ብሔረሰብ መብቶች የተሟላ ዕውቅና የሰጠ በመሆኑ አቃቂር የሚወጣለት አይደለም።
በረከት ሕገ መንግሥቱ ከመፅደቁ በፊት በረቂቁ ላይ በተደረገ ውይይት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ከ16 ሚሊዮን ያላነሱ ኢትጵያዊያን እንደዘከሩና መከሩበት፣ በአፅዳቂ ጉባኤው ላይም ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች ከወር በላይ ተከራክረው እንዳሳለፉት ይገልጸሉ። ይሁንና ዛሬም ድረስ ‹ሕገ መንግሥቱ እኔን አይወክልም፣ ሲፀድቅም አልተሳተፍኩም› የሚለው ወገን ድምፅ በጉልህ እና በብዛት አየተሰማ ነወ።
በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የቀድሞው ፕሬዘዳንት ነጋሶ ጊዳዳ በግንቦት 9/2010 ውይይት ላይ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሚባለው ሕዝባዊ ውይይት በወጉ ስላለመደረጉና ሕዝቡም እንዲጠይቅ ዕድል እንዳላገኘ በማስተወስ አንቀጽ 39ኝን ጨምሮ “ብዙ ያልተግባባንባቸው አንቀጾች አሉ” ሲሉ ተደምጠዋል። አንዳርጋቸው በበኩላቸው አንቀጽ 39ኝን በኢትዮጵያ በሠላማዊ መንገድ መተገበር እንደማይቻል በማንሳት “ከቅዥት” ያለፈ ትርጉም እንደማይሰጣቸው ይጠቅሳሉ።
ከ1966ቱ አብዮት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን የግራ ርዕዮት ምሁራን ከስታሊን የወረሱት “የብሔር ብሔረሰቦች” ትርጉም ከጅምሩ ያልተጠናና ከአገሪቱ እውነታ ጋር የማይጣጣም እንደሆነ የሚገልጹት አንዳርጋቸው፣ ለብሔር ብሔረሰቦች ከስታሊን የተወሰደው ትርጉም “የጋራ ቋንቋ፣ ታሪክ ባሕልን፣ ሥነ ልቡና፣ መልዕክ ምድርን እና የተዋሐደ ኢኮኖሚን በጋራ ለሚጋሩ ሕዝቦች የተሰጠ ስያሜ ነው” ይላሉ። በዚህም በቋንቋቸው ዙሪያ በርከት ብለው በአንድ መልክዓ ምድር ላይ የተሰባሰቡ ሕዝቦች ብሔር ብሔረሰብ የሚል ሥያሜ ሊሰጣቸው እንደሚችል ቆጥሮ መነሳቱ ከጅምሩ ችግር ነበረበት ይላሉ – አንዳርጋቸው።
አንዳርጋቸው “ነፃነት የማያውቅ ነፃ አውጭ” በሚል ባሳተሙት መጽሐፋቸው “በአገራችን ዘውገኛነት፣ ቋንቋን እና ባሕልን ከመሳሰሉ ማኅበራዊ እውነታዎች ጋር ካለው ትስስር በታች ወርዶ፣ በዋነኛነት ደምን፣ ዘርን እና መወለድን ከሚያጣቅሱ እንስሳዊ የሰው ባሕርዮች ጋር የተሳሰረ” እንደሆነ በገጽ 133 ላይ አስፍረዋል። ጸሐፊው ኢትዮጵያዊነትን መሰባሰቢያው አድርጎ የተጀመረ አገር ግንበታ በጠንካራ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ባለመታገዙ ምክንያት ዛሬ በአገሪቱ ለተስፋፋው የዘውጌ ፖለቲካ አሰተዋፅዖ ማድረጉን ሲገልጹም፣ “የጎሳ/ዘውጌ ፖለቲካ ዘመናዊ የአገርና መንግሥት ግንባታ በሚገባው ደረጃ እውን ባለመሆኑ የተከተለ ውርጃ ነው” ይላሉ። ኢሕአዴግ ብሔርተኝንት የሚለው በዘርና ደም መቋጠር ላይ የተመሠረተን ዘውጌነት ስለመሆኑም ይከራከራሉ።
ኢሕአዴግ በደምና ዘር ላይ የተመሠረተን የዘውግ ወይም የጎሳ ፖለቲካ የሥልጣን ማራዘሚያ አድርጎት ስለመቆየቱም ትችት ይሰነዘርበታል። በረከት ግን በመጽሐፋቸው ገጽ 88 ላይ ይህንን በመቃወም “የብሔር ብሔረሰቦችን መብት በማክበር ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ በጎሳ ፖለቲካ መልክ በመሰየም ዘርና ደም በመምረጥ ላይ የተመሠረተ ለማስመሰል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።: የጎሳ ፌደራሊዝም የሚባለው መነሻና መድረሻው ደምና ዘር ተኮር ነው። በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ዴሞክራሲም ሆነ አገራዊ አንድነት ግን መነሻና መድረሻው ዘርና ደም አይደለም” ይላሉ።
ፖለቲከኛው መረራ ጉዲና (ዶ/ር) በበኩላቸው ራሳቸውን የኢትዮጵያዊነት ሰርተፍኬት ሰጭና ተቀባይ አድርገው የሾሙ ሰዎች እንዳሉ በመጥቀስ እስካልታረሙ ድረስ በኢትጵያዊነት ላይ ችግር መሆኑን፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እኔ በምለው መልኩ ብቻ ትደራጅ ብለው ድርቅ የሚሉትም መስከን እንዳለባቸው ይመክራሉ።
የኢትዮጵያ ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ሊቀመንበሩ ይልቃል ጌትነት እንደሚሉት ሰው ብዙ ማንነቶች ያሉት ቢሆንም በኢትዮጵያ ማንነት ከብሔር ወይም ዘውግ ጋር ብቻ እንዲተሳሰር በመደረጉ ነገሮች ምስቅልቅላቸው እንዲወጣ አድርጓል። በአስተዳደር ወሰንና በታሪካዊ ባለቤትነት የሚነሱ ሕጋዊ ጥያቄዎች እንዳሉ የሚስማሙት ይልቃል ይሁን እንጂ፣ “ዳቦ ባነሰ ቁጥር የጎሳ ባንዲራውን እያውለበለበ የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳው እንደሚበዛ እርግጥ ነው” ይላሉ።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ገደይ ደገፉ የብሔር ማንነት በኢትዮጵያ ከ1970ዎቹ ‹ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት› የሚል የግራ ዘመም ፖለተከኞች የጀመረ መሆኑን ይገልጻሉ። ከደርግ ውድቀት በኋላም ኢትዮጵያን ከክፍለ አገር ወደ ዘውግ ማካለል ሲገባም ሕዝቡ አለመሳተፉን ይልቁንም ሕዝቡን ወክለናል ያሉና የብሔር ጥያቄን ያነገቡ የግራ ፖለቲካ ኃይሎች (በተለይም ኢሕአዴግ፣ ኦነግና የኤርትራ ነጻነት ግንባር) ፍላጎታቸውን እንዳስፈፀሙበት ያስረዳሉ። በሕገ መንግሥቱም ከመግቢያው (እኛ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚል ሐረግ) ጀምሮ በአንቀጽ 39ና 40 የተንፀባረቀው የግራ ፖለቲከኞች ሐሳብ እንደሆነ በመጥቀሰ እፎይታን እንጂ ዘላቂ መፍትሔን እንዳላመጣም ያክላሉ።
ራያ እንደ ማሳያ
ኢትዮጵያዊያን ከተጣባቸው ድህነትና የመልካም አስተዳደር እጦት የመፋታት እንጂ የማንነት ጥያቄ የላቸውም የሚሉ ወገኖች በአንድ በኩል፣ የማንነት ጥያቄ አለን የሚሉ ደግሞ በሌላ በኩል አሉ። አሁን ላይ የማንነት ጥያቄ ጎልቶ ከሚነሳባቸው ራያና ወልቃይት ጋር በተያያዘ የትግራይ ክልል በተደጋጋሚ ባወጣው መግለጫ በአካባቢዎቹ የመልካም አስተዳደር እንጂ የማንነት ጥያቄ የለም ብሏል። የአማራ ክልል በበኩሉ በአዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ለክልሉ የፀጥታ ስጋት እንደሆኑበት ጠቅሶ የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱና በዚህም ትግይራን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን የሚጠቅስ መግለጫ በማውጣቱ የትግራይ ክልል በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ ገብቷል በማለት ክልሉንና የትግራይን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚያሳስብ መገለጫን ማውጣቱ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) “የራያና ወልቃይት ጥያቄ የማንነት ነው” ሲል፣ ዓረና ትግራይ በበኩሉ “የማንነት ጥያቄ የለም” በሚል ሙግት ውስጥ ገብተዋል።
የኮሚቴ ሰብሳቢው አግዘው “የትግራይ ክልል መንግሥት መሬቱን እንጂ የራያን ሕዝብ አይደለም የሚፈልገው” ሲሉ ይወቅሳሉ። ትግራይ ክልል በበኩሉ በጥቅምት 27/2011 መግለጫው በአማራ ክልል ከ2008 ጀምሮ በማንነታቸው ምክንያት የትግራይ ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ የሕይወትና ንብረት ጉዳት እንደደረሰ በመግለጽ ወቀሳ ያቀርባል።
ጥቅምት 26 “በመተማና ሌሎች አከባቢዎች ተመሳሳይ ግፍ ተፈፅሟል” ካለ በኋላም ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች አንዳንድ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ግፍ እንዲፈፀም አመራር ስለመስጠታቸውም ያክላል።
በዚህ መነሻነትም በተለያዩ ጉዳዮች መስማማት ያቃታቸው የክልል ባለሥልጣናት የሚነሱትን የማንነት ጥያቄዎችን እንደመጠቃቂያ ስልት እየተጠቀሙባቸው ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።
መረራ ጉዲና (ዶ/ር) በበኩላቸው “ብሔረሰቦቸ እርስ በእርሳቸው የማይተማመኑባት ኢትዮጵያ ተፈጥራለች” ይላሉ። “ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠርባቸው መሥራት ከሚያስፈልጉት ጉዳዮች አንዱም ይኸው ነው የሚሉት” መረራ ልኂቃኑ በፈለጉት መንገድ የሚጋጩ ሕልሞችን ይዘው መኳተናቸው ለዚህ ፈተና መሆኑን ያስረዳሉ። በሌላ በኩል ኢሕአዴግ በሚወስዳቸው ማሻሻያዎች “ከዚህ ቀደም የበላይ የነበረ የበላይነቴ ይቀጥል አለበለዚያ እጎዳለሁ ሲል፣ ተገዥ የነበረው እስከመቼ እገዛለሁ በሚል የሚፈጥሩት ውዝግብ ነው” ብለውም ያምናሉ።
“ጥያቄው የመልካም አስተዳደር ነው” የሚለውን ሐሳብ በጥብቅ የሚቃወሙት የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢው አግዘው የራያ ጥያቄ የማንነት እንደሆነ በመግለጽ “ሰው ሠላማዊ ሰልፍ እየወጣ የተገደለውና የተፈናቀለው የማንነት ጥያቄ ስላለው ነው” በማለት ይሞግታሉ። የራያ ሕዝብ በትግራይ ክልል በኩል ለዓመታት በደል ሲደርስበትና የራሱን ማንነት እንዲያጣ ጫና ሲደረግበት እንደኖረ በመጥቀስ ጥያቄው ማንነቱ እንዲከበርለትና ወደ አማራ ክልል እንዲካለል መሆኑን ያክላሉ።
ጥያቄው የመልካም አስተዳደርና የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ነው የሚሉት ወገኖች እንደተሳሳቱ በማንሳትም ከሁሉም የሚቀድመው ቁሳዊ ልማቱ ሳይሆን መንፈሳዊው ጥያቄ (የማንነት) ነውም ባይ ናቸው። እንደ አግዘው ማብራሪያ የራያ ሕዝብ ከ1984 መጨረሻ ጀምሮ የማንነት ጥያቄን ሲያነሳ የኖረ ቢሆንም በሕወሓት በኩል አፈና ሲደረግበት ኖሯል። የፖለቲካ ለውጥ ታይቷል ተብሎ በሚገመትበት ጊዜ ሁሉ ጥያቄው ሲነሳ እንደነበር በመጠቀስ በአሁኑ ወቅት ገፍቶ አደባባይ ላይ መውጣቱን ያነሳሉ። በዚህም ራያ ላይ በነበሩ ሰልፎች 13 ሰዎች በክልሉ መንግሥት በጥይት እንደተገደሉ፣ እስካሁንም 500 ሰዎች መታሰራቸውንና ብዙዎች መፈናቀላቸውን ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ግን “ራያ ትግራይ ነው፣ የማንነት ጥያቄም የለንም” የሚል መፈክሮችን ያነገቡ ሰልፎች እየተካሔዱ ነው። ለአብነትም እሑድ ኅዳር 9/2011 የተካሔደውን ሰልፍ ማንሳት ይቻላል። ይህንን የሚያጣጥሉት አግዘው “ራያ ትግራይ ነው” የሚልና ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ የሚሆን ሰው አይጠፋም ይላሉ።
በመግቢያው እንደተነሳው ግን በተለያዩ ቦታዎች የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችም ሆኑ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ለበርካታ ሰዎች ሞት፣ አካል ጉዳትና እንግልት ምክንያት እየሆኑ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያዊያን በደቡብ ክልል እየተስተዋሉ የመጡት የክልል ልሁን ጥያቄዎች መነሻቸው “እኔ የተለየና የራሴ ማንነት ያለኝ መሆኔ በራሴ ልተዳደር” የሚል በመሆኑ ሔዶ ሔዶ ኢትዮጵያን የማሳሳትና የመበታተን አደጋ ላይ ይጥላት ይሆን የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።
ግደይ ግን እራሴን በራሴ ላስተዳድር የሚለው ጥያቄ ስጋት ሊሆን እንደማይገባ በመጥቀሰ ስጋት የሚሆነው ጥያቄውን መጨፍለቅ ውስጥ ከተገባ ነው ይላሉ። በሌሎችም አገራት ብሔርተኝነት የናረበት ዘመን ላይ መሆኑን በመጥቀስም ጥያቄው ከፖለቲካ ልኂቃኑ አልፎ የሕዝቡም ሆኗል ባይ ናቸው። ብሔርተኝነቱ አገራዊ አስተሳሰብን በማዳከም በኩል ተፅዕኖ እንደሚኖረው ግን ይጠቁማሉ።
መፍትሔው ከወዴት አለ?
የማንነት ጥያቄዎች ዓለምን እያተራመሱ እንደሆነ ዕውቁ የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያ ፍራንሲስ ፉኩያማ ቀድመን በጠቀስነው መጽሐፋቸው ላይ ያወሳሉ። ሶሪያን፣ ሊቢያን እና ሌሎችንም አገራት ለትርምስ የዳረጋቸው የማንነት ጥያቄ ገደብ አልባነት መሆኑን የጻፉት ፉኩያማ እንደመፍትሔ የሚጠቁሙት ማመሳሰልን (assimilation) ነው። እንደ ፉኩያማ አንድ አገር ውስጥ ዜጎችን የሚያስተሳስረው ማንነት ከአባል ማንነቶች የበለጠ መሆን አለበት፤ ይህ ማለት ግን የተለያዩ ማንነቶችን በመጨፍለቅ ሳይሆን አቃፊ ማንነቱን በማጎልበት ነው። ስለሆነም የተለያየ ማንነት ያላቸውን በአንድ የማንነት ማዕቀፍ ውስጥ ማኖሩ ችግሩ ሥር ሰዶ አገር ከማፈራረሱ በፊት ለመታደግ ያስችላል ባይ ናቸው። ዩሱፍ ያሲን የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ “ኢትዮጵያዊነት፤ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት” በሚል ርዕስ ጠቅልለው በገለጹበት እና በ2009 ባሳተሙት መጽሐፋቸው የደረሱበት ድምዳሜም ከፍራንሲስ ፉኩያማ ጋር ተመሳሳይ ነው። አቃፊ እና አገር ዐቀፍ ማንነት ያስፈልጋል የሚል።
እንደ መረራ እምነት የማንነት ጥያቄው አንድም የበላይነትን ለማስቀጠል በመሻት፣ አልያም ተጨቁኛለሁ የሚለው ወገን ከጭቆናው ለመላቀቅ በሚያደርጉት ፍትጊያ ሊነሳ ቢችልም አንድ ሁለት ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነትም ይሁኑ ሌሎች የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የማኅበረሰብ ፍላጎቶች የማንነት ጥያቄን ሊያስነሱ እደሚችሉ ይጠቅሳሉ። ፍራንሲስ ፉኩያማም በዚህ ረገድ የማንነት ጥያቄዎች እና ብሶቶች “ምጣኔ ሀብታዊ ሥረ መሠረት አላቸው” ይላሉ። “ይሁን እንጂ በማንነት ሥም የሚደረጉ ሽኩቻዎች የችግሩን ምንጭ ለመቅረፍ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን መቅረፅ እንዳይቻል አጀንዳውን ይቀይሩታል።” ይህ የፍራንሲስ ፉኩያማ ድምዳሜ በተለይ እንደኢትዮጵያ ባሉ አገራት በማንነት ሥም የሚቀርበው ጥያቄ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በመሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ አንድምታ እንዳለው መረዳት አይቸግርም።
መረራ “መፍትሔው ለጊዜው ጥያቄው የሚነሳባቸውን አካባቢዎች ማረጋጋትና በዘላቂነት ቁጭ ብሎ በጋራ መምከር ነው” ይላሉ። በዚህም የማንነት ጥያቄው መቆሚያና መፍትሔው ብሔራዊ መግባትን መፍጠር ሲሆን አገርም ሁሉን አቃፊ እናት እንድትሆን እና እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መሥራት እንደሚያስፈልግም ያሠምሩበታል። ልኂቃኑም እውቀቱና ችሎታው ካላቸው እንዴት ተከባብረንና ተቻችለን አብረን እንኑር የሚለውን መፈለግ እንዳለባቸው ይመክራሉ። ይህ ካልሆነ በአንድ በኩል “ለማንነትህ ደምህን አፍስስ” እየተባለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “ሕዝቡን ክልልና ወሰን አያጥረውም፤ አንድ ነው” የሚለው መልዕክት ሕዝቡ ጋር ሲደርስ ችግር እንደሚፈጥርም ያስገነዝባሉ። የሚያለያይ ሳይሆን የሚያቀራርብ አካሔድን መከተልና ሕዝቡ እንዲወስን መፍቀድም የግድ ነው።
“ክልሎች የተካለሉት ሕገ መንግሥቱ ከመፅደቁ በፊት በተወሰደ የፖለቲካ ውሳኔ ነው” የሚሉ ወገኖች፣ “ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው መካለልን የሚጠይቁ የማንነት ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው በፖለቲካ ውሳኔ ነው” የሚል አቋም አላቸው። አግዘው ግን በዚህ መፍትሔ አይስማሙም። ይልቀንም ጊዜ ወስዶ መምከርና የጥያቄው ባለቤት በሕዝበ ውሳኔ ምርጫውን እንዲያሳውቅ በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ።
ይልቃል ጌትነት መፍትሔ የሚሉት ብሔርን እንደ ሃይማኖት ሁሉ ከፖለቲካ መለየት ነው። በጎሳ የፖለቲካ ማኅበርን መመሥረት ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ አገራት ክልክል ነው የሚሉት የኢሃን ሊቀመንበሩ “ፖለቲካ የሐሳብ ትግል በመሆኑ በብሔረሰብ እንዳይደራጅ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለው ያምናሉ። “መጀመሪያ የጋራ የዜግነት ማንነት ሊፈጠር ይገባል” በማለትም ሌሎቹ ማንነቶች ከዚህ ቀጥሎ ሊመጡ እንደሚችሉም ያነሳሉ።
የማንነት ጥያቄው ከዕድገት፣ ከቅኝ ግዛት እሳቤና የግራ ኃይሉ መዳከም ጋር እየተያያዘ ሊመጣ እንደሚችል የሚናገሩት የኮተቤው መምህር ግደይ፣ መጥፎው ነገር ማንነትህን ስትካድ ነው ይላሉ። ስለሆነም የሚነሱ ጥያቄዎችን ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ በሰከነ ውይይትና ድርድር ሕጋዊ እልባት እየሰጡ መሔድን ይመክራሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here