የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እስከ ሁለት ዓመት የሚያከናውናቸውን ዕቅዶች በተመለከተ በሰጠው መግለጫ “የፀረ ጥላቻ ንግግር ሕግ” በዚህ ዓመት ሊያወጣ እንደሆነ ገለጸ።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመሻሻል ላይ ካሉ እና አዲስ ከሚዘጋጁ የሕግ ማዕቀፎች መካከል በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች እና በሌሎችም ስልቶች የሚሰራጩ ብሔር፣ ሃይማኖት እና ማንነት ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ንግግሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሕግ እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡
በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እየተሰራጩ ግጭትን የሚቀሰቅሱ አካሔዶች በአገሪቱ እየሰፉ መምጣታቸውን የጠቀሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መንግሥት ምን አንዳሰበ ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩም “በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ ግጭት ቀስቃሽ አካሔዶች ከኢትዮጵያ ባሻገር ዓለም ዐቀፋዊ ፈተና ነው” በማለት፤ መንግሥታቸው የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያወጣ ተናግረውም ነበር፡፡
ሰሞኑን በአገሪቱ ዩኒርሲቲዎች እየተከሰቱ ካሉ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ጋር በተያያዘም በዩኒቨርሲቲዎቹ ሁከት እንዲፈጠር እየተደረገ ያለው በዋናነት በማኅበራዊ ድረ ገጾች በሚሰራጩ “ሐሰተኛ ወሬዎች” መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚንስትሯ ሒሩት ወ/ማሪያም (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል፡፡
ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡት የጋዜጠኝነት መምህሩ ወልደጊዮርጊስ ገብረሕይወት እንዳሉት የጥላቻ ንግግሮች በግልጽ በስድብ መልክ ብቻ የሚቀርቡ ሳይሆኑ፣ በውስጣቸው አሉታዊ ፍረጃን የያዙ መደበኛ የቃላት አጠቃቀሞችንም ይጨምራሉ፡፡ እነዚህን የጥላቻ ንግግሮች ለይቶ ተናጋሪዎቹን ለሕግ ለማቅረብ ከባድ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት ወልደጊዮረጊስ፣ ሕጉ ዘርዘር ያሉ መለያዎችን እስካስቀመጠ ድረስ የጥላቻ ንግግሮችን ለይቶ መከላከሉ ተገቢ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ የጥላቻ ንግግሮች ምን እንደሆኑ ከመለየት ባለፈም በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች መሰል ንግግሮችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ወልደጊዮርጊስ ያምናሉ፡፡
ስለጥላቻ ንግግር ሲነሳ ከጉዳዩ ጋር ተያይዘው ከሚነሱ ነገሮች መካከል ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አንዱ ነው። በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች የፈለጉትን ነገር መናገራቸውን እንደ መብት ሲያዩት ሌሎች ደግሞ በሌሎች ሰዎች ሥነ ልቡና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ንግግሮች ከነጻነት ይልቅ ወንጀል ናቸው ብለው ያምናሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ የሕግ ባለሞያው ደበበ ኃይለ ገብርኤል የጥላቻ ንግግር በመናገር ነጻነት ላይ የተቀመጠ አንድ ገደብ ነው ብለው ያምናሉ። “በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 29 መሠረት ማንኛውም ሰው ሐሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብት አለው፤ ነገር ግን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ፍፁማዊ መብት አይደለም” ብለዋል።
የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 (ንዑስ አንቀጽ 6) መሠረት የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ሥም ለመጠበቅ እንዲሁም የጦርነት ቅስቀሳዎችን እና ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከልከል ሲባል ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት በሕግ ሊገደብ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡
የሕግ ባለሙያው ደበበ አንደገለጹት አንድ ሰው የራሱን ሐሳብ በነጻነት ሲገልጽ የሌሎችን መብት ማክበር አለበት፡፡ ምክንያቱም ሐሳብ የሚሰነዝረው ግለሰብ ያለው መብት ሐሳብ የሚሰነዘርበት ግለሰብ ወይንም ቡድንም አለውና ነው። ሐሳብ በሚገለጽበት ጊዜ የሌሎችን ሰዎች ያለማዋረድና ክብራቸውን የመጠበቅ ግዴታ አለብን። ይህ ካልሆነ ግን የአንድን ሰው ሰብአዊ መብት ከመጣስ ባሻገር ወደ ግጭትና ብጥብጥ የሚያመራበትን ሁኔታ ሊፈጥር ይችላልም ብለዋል፡፡