የኦሞ ኩራዝ የስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች በሥራ ላይ እያሉ ተገደሉ

0
739

በኦሞ ሸለቆ ተፋሰስ ላይ በተገነቡ ኹለት የስኳር ፋብሪካዎች በማገልገል ላይ የሚገኙ አራት ሠራተኞች በሥራ ላይ እያሉ መገደላቸውና ሠራተኞች የጸጥታ ሥጋት ላይ በመወደቃቸው ፋብሪካው ሥራ እንዳቆመ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሠራተኞች ማኅበር አስታወቀ።

በአካባቢው ላይ ያለው የእርስ በእርስ ግጭትም በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በደረሰ ጥቃት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉንም የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጋሻው አይችሉህም ተናግረዋል።

የስኳር ኮርፖሬሽን መሰረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ሊቀ መንበር ጋዲሳ ደሳለኝ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በፋብሪካዎቹ ሠራተኞች ላይ የሚፈጽሙት የግድያ ጥቃት እየተበራከተ መጥቷል። አንደ ሊቀ መንበሩ ገለጻ ታጣቂዎቹ ሰሞኑን ብቻ በተከታታይ በፈጸሙት ጥቃት የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ሾፌርን ጨምሮ በሸንኮራ ማሳ ላይ የተሰማሩ በርካታ ወዛደሮች ለሞትና ለጉዳት ተዳርገዋል። ለዚህም ግጭት መነሻ የሆነው የአካባቢው አርብቶ አደሮች እርስ በእርስ በመጋጨታቸው ነው።

በወቅቱም በፋብሪካው ለሚሠሩ ሠራተኞች ምግብ የሚመጣው ከጂንካ ከተማ ቢሆንም በአካባቢው ባለው አለመረጋጋት የተነሳ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ብዙ ሠራተኞች ሥራቸውን ለቀዋል። ምን ያህል የሚለውን እርግጠኛ ባልሆንም እስካሁን ግን በትንሹ ከ10 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በጉዳቱ ሰለባ ሆነው ሕይወታቸውን አጥተዋል ብለዋል። ፋብሪካውም ከዚህ ግርግር ባለፈ በክረምቱ ምክንያት ሥራ አቁሟል።

ሆኖም ግን በአካባቢው የመከላከያ ኀይሎች በቦታው ገብተው ሰላሙን ለማረጋጋት እየሞከሩ ሲሆን እስከ ጥቅምት 19/2012 ድረስ ሁሉም ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ይገባሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር ደንበሩ ታደሰ ለአዲስ ማለዳ እንደንደገለጹት፤ ባለፉት ሦስት ሳምንታት በአካባቢው ከባድ ጊዜ እያሳለፍን ነበር፤ ከሰኔ 2011 ጀምሮ አንድ የፌደራል ፖሊስ እና አንድ የጥበቃ ሠራተኛ ተገድለው መገኘታቸው እና የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል። እንዲሁም አንድ የማኅበሩ ጥበቃ ሠራተኛ መገደሉ የፋብሪካውን ሠራኞች ሥጋት ላይ ጥሏል ብለዋል።

ድንበሩ፤ ይህን ተገቢ ያልሆነ ግፍ የፈፀሙት ግለሰቦች እስካሁን አልተያዙም፤ ድርጊቱን ፈጻሚዎች ግን የክልሉ አርብቶ አደሮች መሆናቸውን እናውቃለን ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

የሠራተኛ ማኅበሩ ችግር በተፈጠሩባቸው ወቅቶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ቢያደርጉም ሁኔታው የተሻሻለበት ጊዜ የለም ብሏል። በመሆኑም የፋብሪካው ሠራተኞች “እኛ እየሞትን ልማት አይቀጥልም” በማለት አብዛኞቹ ሥራቸውን አቁመዋል፤ የደኅንነት ሥጋት የተሰማቸው ሠራተኞችም የሥራ መልቀቂያ እያቀረቡ እንደሆነ ተገልጿል።

የፋብሪካው ሥራ የቆመበትም ምክንያት ግን ከክረምቱ መግባት ጋርም ተያይዞ ነው ይላሉ። ሆኖም ግን ባሳለፍነው ሳምንት መከላከያ ሠራዊት ገብቶ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም ሠራተኞቹ ወደ ፋብሪካው ለመምጣት በመከላከያ ታጅበው እየሔዱ ነው ብለዋል።

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የሰላማጎና እና የኛንጋቶም ወረዳዎችን፣ በቤንች ማጂ ዞን የሱርማና የሚኤኒት ሻሻ ወረዳዎችን እንዲሁም በከፋ ዞን የዴቻ ወረዳ አንዳንድ የተመረጡ ቦታዎችን ያካተተ ሲሆን በተከለሰው የስኳር ልማት ዘርፍ ዕቅድ መሰረት፣ በቀን እያንዳንዳቸው 12 ሺሕ ቶን አገዳ መፍጨት የሚችሉ ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች እና በቀን 24 ሺሕ ቶን አገዳ መፍጨት የሚችል አንድ ስኳር ፋብሪካ እየተገነባበት የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት፤ ለአራቱም ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚውል የሸንኮራ አገዳ በ100 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ እየለማ እንደሚገኝ ከስኳር ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ረቡዕ፣ መስከረም 14 ባወጣው ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በተፈጠሩት ግጭቶች የተነሳ ከ1 ሺሕ 229 ሰዎች ሕይወት አልፏል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረቶች መውደማቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here