የአገር ሕልውና መጠበቅ፥ ሕግም መከበር አለበት

0
578

በኢትዮጵያ በፖለቲካ ፓርቲ በኅቡም ሆነ በይፋ ተደራጅቶ ይሆነኛል፤ ለአገር ይበጃል ተብሎ መታገል ከተጀመረ ከአምስት ዐሥርት ዓመታት አይዘልም።
የፖለቲካ ፓርቲ መኖር በተደራጀ መልኩ የሕዝብን ንቃተ ሕሊና ለማዳበርና ለማደራጀት ጠቃሚና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ መንግሥት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ብሎም ምርጫን መሰረት አድረጎ የመንግሥት ሥልጣን ለመጨበጥ የሚያግዝ ትልቅ መሣሪያ ነው ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ኀይሎች መስተጋብር በውጣ ውረድ የተሞላ፣ ለአጭር ወይም ረጅም ጊዜ ግብ ሲባል ብዙም መተባበር የማይታይበት፣ የመጠላለፍ አንዳንዶች እንደሚገልጹት ደግሞ “የመበላላት” አሳዛኝ ታሪክ ባለቤት ነው። በ1960ዎቹ እንዲሁም 1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበሩት መኢሶንም ሆነ ኢሕአፓ በከተማ ትግል ወይም ነፍጥ አንስተው ሲታገሉ የነበሩትም እንደእነ ሕወሓት፣ ሻዕቢያ፣ ኦነግ የመሳሰሉት ፓርቲች ወይም ስብስቦች ይህ ነው የሚባል የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ባይኖራቸውም የመተባበርና አብሮ የመሥራት መንፈስ አልነበራቸውም ማለት ይቻላል፤ ግንኙነት እንኳን ቢፈጥሩ በአጭር የተቀጩ ግንኙነቶች ነበሩ። ሁሉም ግን ማለት ይቻላል ግራ ዘመም ሶሻሊስታዊ ርዕዮተ ዓለም እንዲሁም ለሕዝቦች ነፃነት እንታገላለን እንደሚሉ እንደነበሩ/እንደሆኑ ይታወቃል።

በብዛትና በንጽጽር በተጠናከረ መልኩ የፖለቲካ ኀይሎች መፈጠር የጀመሩት ከ1983 የመንግሥት ለውጥ በኋላ ቢሆንም ከመንጋጋት ውጪ አብዛኞቹ ይሔ ነው የሚባል የፖለቲካ መርሃ ግብር ያልቀረጹ፤ ቢቀርጹም ነባራዊውን ሁኔታ ከግምት ያላስገቡና ከሆነ ቦታ ላይ የተገለበጡ የሚመስሉ፤ ሕዝባዊ መሠረት የሌላቸው፤ የፓርቲ ተልዕኮን ከግል ፍላጎት ያሳከሩ፤ ሕዝብ የማንቃት፣ የማደራጀት ሥራቸውን የዘነጉ፤ በምርጫ ወቅት ብቻ “አለን አለን” የሚሉ፣ ቁርጠኝት መገለጫቸው ያልሆኑ ነበሩ/ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በተጨማሪም ውህደት፣ ኅብረት፣ ቅንጅት፣ ግንባር የመሳሰሉ አብሮ የመሥራት ዕድሎች በግለሰቦች የግል ፍላጎት፣ በርዕይ አለመኖር እና በብቃት ማነስ የተተበተቡ በመሆናቸው የተጀመሩ ትብብሮች በመለያየት፣ ኅብረታቶች በጸብ ብዙም ሳይቆዩ መቋጨታቸው ዓይነተኛ መለያ ናቸው። ትብብራቸው እንኳን ቢቀጥል ያን ያክል ፋይዳ ያለው፣ ውጤታማና ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን የቻሉበት አጋጣሚ ሲፈጥሩ እምብዛም አይታዩም።

በርግጥ አብሮ መሥራቱ፣ ተጠናክሮ አንድ ሆኖ መውጣቱ የፖለቲካ ኀይሎቹ ውስጣዊ ድክመት በዋናነት የሚጠቀስ ቢሆንም ውጫዊ ጫና የለባቸውም ማለት እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። የመንግሥት ሥልጣኑን የተቆጣጠሩ ኀይሎች ብርቱ ክንድም ለደካማነታቸው ተጠቃሽ ነው። መሰረታዊ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበር እንዲሁም አምባገነንት የራሳቸውን የሆኑ አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል። ሕዝቡንም ፈሪ ወይም “ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ” የሚያስብል መንፈስ ውስጥ ከትተውታል።

በ1997 ክልላዊና አገር ዐቀፍ ምርጫ ብቅ ያለው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ በአጭር በተቀጨ የሕይወት ታሪኩ አብሮ የመሥራትን ፋይዳ፣ የመተባበርን ትሩፋት እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪነትን በጥቂቱም ያጣጣመ ቢሆንም አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና ኅብረት ወይም ቅንጅት ታሪከ የመሰነጣጠቅ፣ የመለያየት እና የሴራ ጉንጎና ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ በተቃራኒው ግን ኢሕአዴግ በግንባርነት በተሳካ መልኩ የዘለቀ ብቸኛው የፖለቲካ ኀይል ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፤ ምንም እንኳን እስካሁን ከግንባርነት መዝለል ባይችልም።

ኢሕአዴግ ከልብም ይሁን ካንገት በላይ ባይታወቅም የውሕደት ሐሳቡን ካነሳ ኹለት ዐሥርት ዓመታት መቆጠራቸው ይነገራል። ይሁንና ከ2008 ጀምሮ የተጠናከረው ሕዝባዊ አመጽ ገዢውን ግንባር ፈተና ላይ የጣለ ብቻ ሳይሆን በውስጡም አዲስ የለውጥ ኀይል ወደ ፊት እንዲወጣ ያስገደደበትን አጋጣሚ ፈጥሯል።
በጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጥ ኀይል ኢሕአዴግን እስከ ዛሬ በተጓዘበት መንገድ ማስቀጠል እንደማይቻል በመገንዘብ ከግንባርነት ወጥ ወደ ሆነ አንድ ፓርቲነት ራሱን ለመለወጥ በተጨባጭ ሒደት ላይ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል።

የግንባሩ ሊቀ መንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡም ከሸገር ሬድዮ ጋር ባደረጉት ይቆታ የኢሕአዴግን ከግንባርነት ወደ ወጥ ፓርቲነት መለወጥ በአጭር ጊዜ እውን እንደሚሆን አረጋግጠዋል። አዲስ ማለዳም ቅርብ ከሆኑ ምንጮቿ ባገኘችው መረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ (አብፓ) እንደሚተካ እንዲሁም ከሕወሓት በስቀተር ሌሎች የግንባሩ አባል ድርጅቶች እና አጋር ፓርቲዎችን ያካተተ እንደሚሆን አረጋግጣለች።

በመንግሥትነት እያስተዳደረ ያለው ኢሕአዴግ ውሕድ ሆኖ መውጣት እንደ ቀደምቶቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኀይሎች ተጽዕኖው ቀላል እንደማይሆን አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። በተለይ አባል ድርጅቶቹ ሙሉ ስምምነት ላይ ደርሰውም ይሁን ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ውሕደቱ ቢፈጸም የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል። ምክንያቱም የግንባሩ ስኬት ወይም ውድቀት፤ ድኅነት ወይም ቅጽፈት ከራሱ አልፎ በሌሎች ኀይሎች እንዲሁም በአገር ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ የማሳደር ዕድሉ ከፍተኛ ነው ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ለአብነት የግንባሩ ወጥ ፓርቲ ሆኖ መውጣት ተጽዕኖው አብረውት በሚሠሩት እንዲሁም ተፎካካሪ ከሆኑ በብሔር ለተደራጁትም ሆነ ሕብረ ብሔራዊ ወይም ዜግነትን መሠረት ባደረጉት የፖለቲካ ኀይሎች ላይ የአሰላለፍ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የፖለቲካ ኀይሎች በጠቅላላው በኹለት ዋና ዋና ምድብ ሊካተቱ ይችላሉ፤ ሕብረ ብሔራዊ እና ብሔር ተኮር። የአራት የብሔር ድርጅቶች ግንባር የሆነውን ኢሕአዴግ ጨምሮ ሌሎች ኀይሎች የቆምኩላቸው፣ ድምጻቸውን የማሰማላቸው የሚሏቸው ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ አንድነት፣ በብሔር እኩልነት ቢያምኑም ኅብረ ብሔራዊነትን ወይም ዜግነትን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኀይሎች እንዲሁ። አዲስ ማለዳ ይህ ነባራዊ ሐቅ ፈጽሞ ችላ ሊባል አይገባም የሚል ጽኑ አቋም አላት።

የኢሕአዴግ ወጥ ፓርቲ ሆኖ መምጣት በሁለቱም የፖለቲካ ኀይሎች የአሰላለፍ ምድቦች ላይ የራሱ የሆነ ጠንካራ ተጽዕኖ የማሳደር፤ አንዱን የማጠናከር፥ ሌላውን የማዳከም ጫና ሊፈጥር ይችላል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በመሆኑም ነባራዊው እውነትን መካድ ሳያስፈልግ ሁሉም የፖለቲካ ኀይሎች ሰላማዊ እና ሕጋዊ ፉክክር የሚያደርጉበት ዓውድ መፍጠር የመፍትሔው አካል ሊሆን ይገባል። ይህም የሚሆነው ዴሞክራሲያዊ ልምምዶች በተግባር ላይ ሲውሉ፣ ሕዝብን የማንቃት የማደራጀት ነፃ እንቅስቃሴዎች ሲተገበሩና ሕግና ስርዓት ሲከበሩ ብቻ ነው ብላ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

በእርግጥ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፉክክሩ በሐሳብ ላይ ካተኮረ ፈራጁና የመጨረሻውን ውሳኔ ሰጪ ሕዝብ ነውና ለሕዝቡ አማራጮች መቅረባቸው ጥሩ ዕድል ይፈጥራል። ሁሉም የፖለቲካ ኀይሎች ይህንን ከግምት ማስገባት፣ ሕግን ማክበር፣ ሰላማዊ አካሔዶችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሌላው በኢትዮጵያ ውስጥ በተካሔዱ አብዮቶች ወይም ለውጦች ሥልጣነ መንበሩን የያዙትን መሪዎች ወይም ቡድኖች ብቻ በማውረድ ሳይመለስ የአገረ መንግሥቱን ሕልውና አሳጥተዋል። ለዚህ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሣዊ አገዛዝ እና የደርግ ውድቀት ተጠቃሽ ማስረጃዎች የሚሆኑ ናቸው።

በመሆኑም የኢሕአዴግ ወደ ወጥ ፓርቲነት ጉዞ አገረ መንግሥቱን አደጋ ላይ እንዳይጥል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። መንበረ መንግሥቱን እንደያዘ ግንባር ውሕደቱ ሕገ መንግሥታዊ አንድምታውም ምን ሊሆን ይችላል የሚለውም በጥንቃቄ ሊጤን ይገባዋል።

በአጠቃላይ የኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ወጥ ፓርቲነት መለወጥ ያለውን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊና አገራዊ አንድምታዎች በጥንቃቄ መያዝ አለባቸው። አዲስ ማለዳ ከምንም ነገር በላይ የአገር ሕልውና ሊጠበቅ፣ ሕግም ሊከበር ይገባል ስትል ያላትን ጽኑ አቋም ትገልጻለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here