ሜቴክ 11 ቢሊዮን ብር የግብር ዕዳውን በሰላሳ ዓመት ለመክፈል ጠየቀ

0
737
  • በአሁኑ ወቅት የኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ ዕዳ 70 ቢሊዮን ብር ደርሷል

የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) 11.3 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር አለመክፈሉን ተከትሎ ምሕረት እንዲያደረግለት ወይንም በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመክፈል ለገቢዎች ሚኒስቴር ጥያቄ አቀረበ።

ለውዝፍ ግብሩ መጠራቀም እንደዋነኛ ምክንያት የተጠቀሰው ላለፉት ስድስት ዓመታት ወደሀገር ውስጥ ላስገባቸው ዕቃዎች ለገቢዎች ሚኒስቴር መክፈል የሚጠበቅበትን ክፍያ ባለመፈጸሙ ነው።

የህዳሴው ግድብን ጨምሮ ለስኳር ኮርፖሬሽን እና ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ወደ ሀገር ውስጥ ላስገባቸው እቃዎች ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ለገቢዎች ሚኒስቴር ክፍያ ያልተፈፀመ ሲሆን ኮርፖሬሽኑ አሁን ካለበት ኪሳራ አንፃር እስከ 30 ዓመት በሚደርስ ረዥም ጊዜ ዕዳውን ለመክፈል ጥያቄ አቅርቧል።
ስለጉዳዩ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሜቴክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሕመድ ሃምዛ፣ ለዕዳው መጠራቀም ዋነኛ መንስኤው ድርጅቱ ለስድስት ዓመታት ኦዲት አለመደረጉና ከአቅሙ በላይ ፕሮጀክቶችን መያዙ ነው።

በህዳሴው ግድብ ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች፤ ደን ምንጠራ እና መሰል ሥራዎች ላይ የዋለውን እና ለሙስና የተጋለጠውን ገንዘብ በተመለከተ መንግሥት በወቅቱ ተገቢውን ቁጥጥር አላደረገም ነበር ያሉት አሕመድ፤ መንግሥት በወቅቱ ተገቢውን ክትትል ባለማድረጉ ዕዳ ስረዛ እንዲያደረግልን መጠየቃችን ተገቢ ነው ብለዋል።
ከዛሬ 10 ዓመት በፊት የተመሠረተው ሜቴክ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ልኅቀት ለማምጣትና ለተለያዩ የካፒታል ዕቃዎች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን ተቋቁሞ ቢሊዮን ብሮች የሚያወጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ፕሮጀክቶችን ቢይዝም፣ ብዙዎቹን ማሳካት አልቻለም። በተጨማሪ ተገቢውን ቁጥጥርና ኦዲት ባለመደረጉ ምክንያት ድርጅቱ ለሙስና እና ለብክነት ተጋልጦ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው እስከመታሰር ደርሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ድርጅቱ የተሰጠውን የመንግሥት ፕሮጀክቶችን የተቀማ ሲሆን አመራሮቹም ተቀይረዋል። ይህንንም ተከትሎ ድርጅቱ ላይ ማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቢሞከርም ተቋሙ ካለበት ዕዳ እና ቀሪ ፕሮጀክቶች አንጻር ተፈጻሚነቱን አዳጋች አድርጎታል።
“ካለንበት ሁኔታ አንጻር መንግሥት ያለብንን ዕዳ ሊራዘምልን ወይም ሊሰረዝልን ይገባል” ሲሉ የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አሕመድ ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ ባለሙያዎች በዚህ ሐሳብ አይስማሙም።

በፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ከ16 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው አብዱልመናን መሐመድ፤ የታክስ ባለሥልጣኑ በራሱ ለምን ይሔን ያህል ጊዜ የግብር ዕዳውን ሳያስከፍል ቆየ የሚለው በራሱ ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ይላሉ። የመንግሥት ተቋማት በመሆናቸው ብቻ ዝም ሊላቸው አይገባም ነበር ያሉት አብዱልመናን፣ ኮርፖሬሽኑ በ30 ዓመት ለመክፈል ያቀረበው ጥያቄ ረዥም በመሆኑና አዋጭ ባለመሆኑ ገቢዎች ሚኒስቴር ጉዳዩን በጥንቃቄ ማየት አለበት ብለዋል።

ዕዳ ስረዛው የሚደረግ ከሆነ ግን፣ ሌሎች ተመሳሳይ ውዝፍ ዕዳ ያለባቸው የግል እና የመንግሥት ድርጅቶች ተመሳሳይ ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ አስጠንቅቀው፣ ሚኒስቴሩ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በጥልቀት ድርድር ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ መምህር ታደለ ሌንጮ የገቢዎች ሚኒስትር እንደዚህ ዓይነት በቢሊዮን የሚቆጠር የግብር ዕዳ ምሕረት ማድረግ አይችልም ያሉ ሲሆን፣ ሥልጣኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ በአንቀጽ 9 በተደነገገው መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቂ ምክንያት መኖሩን ሲያምንበት ከሚኒስቴሩ ወይም ከፌዴራል መንግሥት የገቢዎች ቦርድ ሚኒስቴር በሚቀርብለት አስተያየት መሠረት ከማንኛውም ግብር፣ በዚሁ ላይ ከሚከፈል ወይም ከተከፈለ ወለድ ጭምር ምሕረት ሊያደርግ እንደሚችል የሚገልፅ ሲሆን የገቢዎች ሚኒስቴር ሥልጣን ሊሆን የሚችለው የሚኒስቴሩ ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በቂ ምክንያት መኖሩን ሲያምንበት በማንኛውም ግብር ላይ ከተጣለ መቀጫ በዚሁ ላይ የሚከፈልን ወይም የተከፈለን ወለድ ጭምር ምህረት ሊያደርግ ይችላል።
በአሁኑ ወቅት የኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ ዕዳ 70 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

አዲስ ማለዳ የግብር ዕዳ ክፍያ ማራዘም ጥያቄን በተመለከተ የገቢዎች ሚኒስቴርን በአካልም ሆነ በስልክ ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here