ሲቄሽን አንሺ!

0
879

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የኢትዮጵያዊት ኦሮሞ ሴት ኃይል፣ ሥልጣኗና ድምጿ በዚህች ቀጭን በትር ተመስሎ ተቀምጧል፤ በሲቄ/ሲንቄ። ያቺ ሴት ሲቄዋን ካነሳች በእርሷ ላይ ዱላ የሚያሳርፍ የለም። ክፉ ቃልም ማንም አይናገራትም።

የጥበብ ሰዎች የሲቄን ነገር በጥበብ ሲገልጹ ሲቄ አንዴት ቀጭን በትር ብቻ እንደሆነች፣ ነገር ግን የተመሰለችበትን ኃይል ያስረዳሉ። በሲቄ ውስጥ፣ በሲቄ ላይ የሰዎች እምነትና ስምምነት አለ። ሰዎች የሠሩት ስርኣትና ሕግ አለ። የዱላዋ መጠንና ቅርጽ ሳይሆን የወከለችው እምነት፣ ሕግና ስርዓት ትልቅ ስለሆነ፣ ሲቄ ትከበራለች። ባለሲቄዋ ሴት ደግሞ ክብሯ ከዛ ቢልቅ እንጂ አያንስም።

የተጣሉ፣ ጦር የተማዘዙ ሰዎች መካከላቸው ባለሲቄ ስትገባ መሣሪያቸውን ያስቀምጣሉ። ዱላዋ እንዳታርፍባቸው ፈርተው አይደለም፤ የሰላም መልዕክተኛ መሆኗን ስለሚያውቁ ነው። ሰላምን ደግሞ ሁሉም ያከብሯታል።

መከበር ኃይል ነው፡፡ ከኃይል ይልቅ ፍቅር አሸናፊ ያደርጋል፡፡ በፍቅርና በሰላም እኩልነት እንጂ መበላለጥና መፈራራት የለም፡፡ በኃይል ግን መሸናነፍ የለም፤ እኩልነትም የለም፡፡ ሴት ልጅ አንድም ኃይሏ ክብሯ ነው፡፡ ክብሯ ቁሳዊ ወይም አካላዊ አኳኋን ላይ አይመሠረትም፤ ሰው ከመሆኗ ላይ በሚታከል ሴትነቷ ብቻ እንጂ፡፡ ይህ አያሳንሳትም፡፡ መከበር ከፍ ያደርጋል እንጂ ዝቅ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ባይሆን እሱን መጠቀም ነው፤ ለተሻለ ውጤት ማዋል፡፡

እንዴት? በኹለት መንገድ፡፡ ወዲህ የሴቶች የመብት ጥያቄ ዛሬም አለ። ዛሬም በጾታዊ ጥቃት ሕይወታቸው የሚጎሳቆልና የሚነጠቅ እህቶች አሉን። ሊደርሱ ከሚችሉበት ከፍታ የተገቱ፣ በአጉል ባህል ዝም እንዲሉና በደረሰባቸው በደል መልሰው እንዲሳቀቁ የተገደዱ ጥቂት አይደሉም።
ወዲያ ደግሞ አገር ሰላም በማጣት ውስጥ ናት። መረጋጋት ርቆናል። እንደው በአካል ብንረጋጋ እንኳ መንፈሳችን በብዙ ቆሻሻ ሐሳቦች ተበክሎ ኮሽታው ሁሉ የጸብ መነሻ እየሆነብን ነው። እናም አሁን ባለሲቄዋ የምታስፈልግበት ጊዜ ነው።

ጥሪውም ይህ ነው፤ ባለሲቄዋ ተነሽ! ስለራስሽ ደግሞም ስለአገርሽ ዝም አትበይ። መብትሽ ሲነጠቅ፣ እህትሽ ሰውነት መብቷ ተነፍጎ ስታይ ዝም ብለሽ አትመልከቺ፡፡ በተማርሽው፣ በምትሠሪው፣ ባለሽ አቅም ሁሉ ለለውጥ ትጊ፡፡ የአንድ ሰውን አመለካከት መቀየር ተራ ጉዳይ አይምሰልሽ፡፡ ሰው ይሁነኝ ብሎ ሳይሆን የለመደው ስርዓት ተዋህዶት ሊሆን ይችላልና የእህትሽን መብት የሚጋፋ፣ ልብ እንዲል ቀስቅሺው፡፡

ተነሺ! በትርሽን…ሲቄሽን አንሺ። ኃይልና አቅሙ ከእጅሽ ነው። ልጆችሽን፣ ባልሽን፣ ወንድምሽን ከጥፋት መልሺ፡፡ በአንቺ የተነሳ ለነፍሱ እንደማይሳሳ ሁሉ ስለአንቺ የማይተወዉ አይኖር ከሆነ ተመልከቺ፤ ተው በይ! ተዉ በይ! የራስሽን ሰብአዊ መብት እንድታስከብሪ፣ የአገርሽ ሰላም እንዲከበር እንድታደርጊ ሐሳብሽን አሰሚ፣ አውዶቹን ተጠቀሚ፣ ስለደኅንነትና ሰላም ቁሚ፣ ሲቄሽን አንሺ።
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here