መነሻ ገጽአንደበት“ለነበሩብን ችግሮችና ድክመቶችም ኃላፊነቱን የምንወስደው እንደአመራር በጋራ ነው”

“ለነበሩብን ችግሮችና ድክመቶችም ኃላፊነቱን የምንወስደው እንደአመራር በጋራ ነው”

ዮሐንስ መኮንን
በኢዜማ ፓርቲ የትይዩ ካቢኔ የከተማና የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ትይዩ

ዮሐንስ መኮንን ይባላሉ። በሙያቸው አርክቴክት ናቸው። አሁን ላይ በኢዜማ ፓርቲ የትይዩ ካቢኔ የከተማና የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ትይዩ ሆነው ያገለግላሉ። አሁን ደግሞ ኢዜማ ባዘጋጀው በመላው አገሪቱ የሚገኙ አባላቱ በሚሳተፉበት ምርጫ ለምክትል መሪነት ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር እየተወዳደሩ ነው።

ከተማሪነት ጊዜያቸው ጀምሮ ለፖለቲካ ዝንባሌ እንደነበራቸው ይናገራሉ። በተደራጀ ሁኔታ ወደ ፖለቲካው ዓለም እንዲገቡ ተጽዕኖ ያደረጉባቸው ግን ፕሮፌሰር ብርሃኑ መሆናቸው ተናግረዋል። በአርክቴክት ሙያ ተመርቀው ወደ ሥራ ዓለም በተቀላቀሉበት ዘመን የቅንጅት አባል ሆነው ተመዝግበው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ቅንጅት ፓርቲ ከፈረሰና ከተበተነ በኋላ እርሳቸውም የፖለቲካ ተሳትፏቸው ገታ ብሎ ነበር። ለኹለተኛ ጊዜ ወደ ፖለቲካው የተመለስኩት እስር ቤት የነበሩት የቅንጅት ሰዎች ተፈትተው ፓርቲ ሲመሠርቱ ነው ብለዋል። ይህን ተከትሎ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባል ነበሩ። ከዛም በመቀጠል ነው አሁን ያሉበትን የኢዜማ የፖለቲካ ፓርቲ የተቀላቀሉት።

ኢዜማ ፓርቲ መሪውን ለመምረጥ እየተደረገ ያለውን ምርጫና ሂደቱን እንዲሁም ፓርቲውን በተመለከተ ጠቅለል ያሉ ጉዳዮችን በሚመለከት የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ከዩሐንስ መኮንን ጋር ተከታዩን ቆየታ አድርጓል።

የፓርቲያችሁን የመሪና የምክትል መሪ ምርጫ ፉክክር እንዴት ያዩታል?
እንደዚህ ዓይነት የዴሞክራሲ ልምምድ ወይም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጅምሮች እንዲኖሩ፣ ላለፉት 50ና ከዛ በላይ ዓመታት ለሚሆን ጊዜ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲያነሷቸው፣ ለዴሞክራሲና ለዜጎች መብት እንታገላለን የሚሉ በርካታ ቡድኖች ይህን የመሰሉ ሐሳቦች ሲያንሸራሽሩ ቆይተዋል። ብዙ መጽሐፍትም ተጽፈዋል።

ግን መሬት ላይ አውርዶ ለመተግበር እድል ያገኘው የኔ ትውልድ ነው ብዬ ነው የማስበው። ወይም በኢዜማ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ በርካቶች ሲቪል ማኅበረሰቦች፣ በርካታ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ በርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎች በፕሮግራማቸው የጻፉትን፣ የሚምሉለት፣ የሚገዘቱለት፣ የታሰሩለትን ሐሳብ ወደ መሬት አውርደን ለመለማመድ እኛ እድል አግኝተናል።

ስለዚህ ይህ ከግለሰብ በላይ ነው። እኔና ብርሃኑን ከማስመረጥ ወይም እንዳልኩት እጩዎችን ከማወዳደር በላይ አድርገን ነው የምንወስደው። በመደበኛነትም ሦስት መሠረታዊ ገዳዮችን እናሳካለን ብዬ አስባለሁ፤ ከግለሰቦች ምርጫ በላይ።

አንደኛው የውስጥ ፓርቲ ዴሞክራሲያችንን እናጎለብትበታለን። እንደሚታወቀው ፓርተዎች ሥልጣን አልያዙም እንጂ ቢይዙ ራሳቸው አምባገን ናቸው እየተባሉ ይታማሉ። በውስጣቸው ያልተለማመዱትን ዴሞክራሲ፣ ፍትህ እና ስርዓት ማክበር እንዴት ለአገር፣ ለዜጎች ሊያደርሱ ይችላሉ እየተባሉ ይወቀሳሉ። ይህን ወቀሳ በታሪክም የሻረ የመጀመሪያ እርምጃ አድርጌ እወስደዋለሁ። እና አንደኛው የውስጥ የዴሞክራሲ ባህላችንን ማዳበር ነው።

ኹለተኛ የዴሞክራሲ አሻራዎችን ጥለን የምናልፍበት ይመስለኛል። ከአሁን በኋላ በኢዜማ ቤትም ሆነ በሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎችም ምሳሌ ሆኖ የሚጠቀስ ስለሚሆን፣ ይህ የዴሞክረሲ አሻራ የሚቀጥል ይመስለኛል።

ከአሁን በኋላ በሌሎቹ ቢቀር ቢያንስ በኢዜማ ቤት የሚደረጉ የአመራር ምርጫዎች ከዚህ ሊያንሱና ሊወርዱ አይችሉም። ከዚህ በላይ ከፍ ብለው ነው የሚሄዱት።

ሦስተኛው ለተገዳዳሪዎቻችን፣ ለተፎካካሪዎች ወይም በትብብር አብረውን ለሚሠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብነት የሚሆን፤ እኛ ሞክረነው አሳይተናል። እንደሚታወቀው እኛ አገር ብዙዎች ሥልጣን ይፈልጋሉ። ይህም ሥልጣን ከመውደድ ላይሆን ይችላል፤ ሌሎች ቢይዙት ያበላሹታል፣ እኔ ካልመራሁ መንገድ ይስታል ብሎ ራስን አድራጊ ፋጣሪ ወይም ደግሞ ብቸኛ ጠባቂ ወይም ሌሎች እንደሚገልጹት በውጪ ቋንቋ አባታዊ ስርዓት፣ እኔ ብቻ ነኝ ተከላካይ ጠባቂ፣ የዚህ ተቆርቋሪ ብሎ ከማሰብና ሌሎችን ካለማመን የሚመነጭ ሊሆን ይችላል። እንደሱ ዓይነት ልምድ አለ።

አሁን እኛ ሞክረን አሳየን። የድርጅቱ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ ምክትል መሪ አንዱዓለም፣ ታች ያለ ማንም የማያውቀው አንድ አርሲ ያለ አንድ የኢዜማ አባል ለመሪነት እንወዳደራለን። ስለዚህ ለማንም እድሉ ክፍት መሆኑና ይህን ለማረጋገጥ እድሉን አግኝተናል።

ይህን ማሳካት በራሱ ትልቅ ስኬት ይመስለኛል። ከዚህ ባለፈ ግን ኢዜማ ቤት መሄድ የምንፈልገውን የአካሄድ ስልት የምንመርጥበት አጋጣሚም አድርጌ እወስደዋለሁ። በጣም ጥሩ ጅምር ነው።

ለኢዜማ መሪና ምክትል መሪ በሚደረገው ምርጫ የእናንተ ቡድን ካሸነፈ የኢዜማና የመንግሥት ግንኙነት በምን ሁኔታ የተቃኘ ይሆናል?
ይህ የሚመነጨው እኔና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከመመረጣችን አይደለም። ይህ የሚመነጨው ኢዜማ ካለው ስልታዊ ግቦች ነው። ኢዜማ አራት መሠረታዊ ሥልታዊ ግቦች አሉት። እነዚህ ሥልታዊ ግቦች በአንድ ምርጫ ዘመን ወይም በአንድ አመራር የሚተገበሩ አይደሉም። በረዥም ጊዜ ሂደት ውስጥ ከግብ የምንደርስባቸው ናቸው።

እንዳልኩት ለመኖራችን፣ ለመመሥረታችን፣ እንደ ፓርቲም ለመቆማችን ምክንያት የሆኑን አራት ሥልታዊ ግቦች አሉን። ከአራቱ ኹለቱ የትብብር ናቸው፤ ሁለቱ ደግሞ የፉክክር ናቸው።

- ይከተሉን -Social Media

የትብብር የምንላቸው የአገር ሰላም፣ አንድነት እና ሉዓላዊነት ነው። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ፣ በአገር ሰላም፣ በአገር ሉዓላዊነት ላይ ከማንም ጋር አንፎካከርም። ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር፣ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ከሁሉም የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ጋር በትብብር እንሠራለን። ይህ በሰነድ የተቀመጠ ሥልታዊ ግባችን ነው።

ኹለተኛ ሥልታዊ ግባችን የዴሞክራሲ መሠረት መጣል ነው። የዴሞክራሲ መሠረት አንድ ትውልድ ስለፈለገ ወይም አንድ አመራር ስለፈለገ በአንድ ጀንበር የምናሳከው አይደለም። ባህል መሆን አለበት። ከታች ጀምሮ የሚያድግ ነው። የመጣንበት የሀምሳ ዓመት የአፈና፣ የመገዳደል የመበሻሸቅ ባህል በአንድ ትውልድ የምርጫ ሥራ የሚስተካከል ወይም በአንድ ዘመን ባሉ መሪዎች በጎ ፈቃድ የሚለወጥ አይደለም።

ባህል ስለሆነ ይህን ባህል መሠረት ማስያዝና መገንባት ያስፈልጋል። ይህም በአንድ ተቋም የሚገነባ፣ የሚሠራ አይደለም። ስለዚህ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር ሁሉ በትብብር እንሠራለን። ይህ የፉክክር ጉዳይ አይደለም።

ኹለት የሚቀሩት ሥልታዊ ግቦች ደግሞ የፉክክር ናቸው። ከሌሎች አቻ ፓርቲዎች ወይም ከሌሎች እኛን ከመሰሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተፎካክረን፣ የተሻለ ሐሳብ አለን የምንለውን ለሕዝብ አቅርበን የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የምንሠራባቸው ናቸው። አንደኛው የውስጥ ዴሞክራሲን በመገንባት ጠንካራ መዋቅር ያለው ተፎካካሪ ፓርቲ መገንባት ነው። ሦስተኛ ሥልታዊ እቅዳችን ማለት ነው፤ ይህኛው እንደ ፓርቲ የምንቆምበት የራሳችን ጉዳይ ነው።

አራተኛና የመጨረሻው እነዚህ ሲሳኩ የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዘ መፎካከር ነው። የመንግሥት ሥልጣንም ሆነ ፓርቲ የሚኖረን፣ ቅድም ያልኳቸው ኹለቱ ሥልታዊ ግቦች ሲኖሩ ነው። አገር ስትኖርና የዴሞክራሲ ስርዓት መደላድል ሲኖር ነው።

ስለዚህ ጥያቄውን ከዚህ አንጻር ነው የምመልሰው። የእኛና የገዢው ፓርቲም ሆነ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ከዚህ መሠረታዊ የፖለቲካ ገባችንና መርሃችን ይመነጫል። ስለዚህ በአጭር ቃል በትብብር መሥራታችን ይቀጠጥላል። ከመንግሥትም ጋር ከሌሎችም ባለድርሻዎች ጋር፣ በአገር ሉዓላዊነትና የዴሞክራሲ መርሆዎችና መሠረት ለመጣል በሚደረጉ ሥራዎች ሁሉ በመፎካከር ሳይሆን በመተባበር፣ ለዛውም ከግማሽ መንገድ በላይ ሄደን እንሠራለን።

እንዲህ የመሰሉ ውሳኔዎች እንደ ፓርቲ ሊጎዳን እንደሚችል እናውቃለን። ግን ከመጣንበት የፖለቲካ ስርዓት ወይም ከነባሩ የፖለቲካ ባህል የተነሳ፤ ሁሉን ነገር በጩኸት አንፈታም። አንዳንድ ጉዳዮች ሰከን ብሎ በእውቀት፣ ሥልታዊ ግብ አስቀምጦ በመሥራት ነው የሚፈቱት።
እና እኔና ፕሮፌሰር የምንመረጥ ከሆነ፤ በዋነኛነት የኢዜማን ሥልታዊ ግቦች ለማሳካት እንሠራለን። እነዚህ ግቦች አንደኛውና ዋናው ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ከባለድርሻዎች ጋር በትብብር በሚያሠሩ አገራዊና ዴሞክራሲ መሠረታዊ ግንባታ ላይ አብረን እንሠራለን።

ለኢዜማ መሪነት በምትፎካከሩበት በዚህ ጊዜ፤ ኢዜማ ከመንግሥት ሥልጣን መጋራቱ ፓርቲውን ደካማ እንዳደረገው ተፎካካሪዎቻችሁ እየገለጹ ነው። በእናንት በኩል የኢዜማ ሥልጣን መጋራት ፓርቲውን አልጎዳውም ማለት ይቻላል?
በዚህ ጉዳይ ላይ ዘርዘር ያለ ጥናት ማዘጋጀት ያስፈልጋል። እንደው በ‹ኮመን ሴንስ› ወይም በግለሰብ ሐሳብና አስተያየት ላይ ተመሥርቶ ብያኔ መስጠት የሚያስቸግር ይመስለኛል። ዋነኛው ግን ቅድም ካልኩት ኢዜማ ማሳካት ከሚፈልጋቸው ሥልታዊ ግቦቹ አንጻር፣ የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከዛም ባለፈ ደግሞ ዴሞክራሲ መሠረትን ለመጣል ከገዢ መንግሥት ጋር ሥልጣን ተጋርተን አብረን መሥራታችን ኢዜማንም አገርንም ጠቅሟል ብዬ ነው የማስበው።

- ይከተሉን -Social Media

ዝርዝር ገዳዮን ማንሳት ይቻላል፤ በአጭሩ ግን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚወሰኑ ውሳኔዎች፤ ከላይኛው ከመጨረሻው ሥራ አስፈጻሚ የመንግሥት የሚኒስቴሮች ካቢኔ ጀምሮ መኖራችን ድምጻችን እንዲሰማ፣ እኛ ሐሳብ ወደፊት እንዲመጣ እድል ያስገኛል። አጀንዳዎችን በስሚ ስሚ ወይም ከዚህ በፊት እንደነበረው በስማ በለው እየሰማን፣ በጭምጭታ መስማታችን ቀርቶ ትክክለኛውን ከምንጩ እየሰማን ለመታገል እድል ይሰጠናል።

ከዛ ውጪ ነገ ሕዝብ መርጦን የመንግሥት ሥልጣን ስንይዝ፣ የመንግሥት መዋቅር እንዴት እንደሚሠራ ለማየት እድል አግኝተናል፤ በቅርብ በመሥራታችን።

ሦስተኛ እንደ ፓርቲ አባሎቻችን በተመደቡበት የመንግሥት መዋቅር ውስጥ፤ ባላቸው አበርክቶና ሐሳብ፣ በሥራ ትጋታቸው የተመሰከረላቸው የተመሰገኑ እንዲሆኑና ነገ በሚኖረው የምርጫ ውድድር እድል ብናገኝ አገርን በምን ዓይነት የጠራ ሐሳብ እና እንዴት ባለ ትጋት ማገልገል እንደምንችል ማሳያ እድል አድርገን እንወስደዋለን።

ለምሳሌ አዲስ አበባ ያሉትን ተመራጮቻችን ብቻ በምሳሌ ብናነሳ፣ ከውሰር ኢድሪስ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ተመራጭ ነች፤ ክፍለ ከተማ ካቢኔ አባል ነች። በአፈጻጸም ምርጥ ተብላ የዋንጫ ተሸላሚ ናት። በአዲስ አበባ ካቢኔ ግርማ ሰይፉ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍን በካቢኔነት ይመራሉ። የገዢው ፓርቲ አማካሪ ቀጥሮ ባስጠናው ጥናት፤ በጣም ምርጥ አፈጻጸም ካሳዩ፣ በትጋታቸው ከተመሰገኑት አንዱ እሱ ነው።

ፕሮፌሰር እየሠራ ያለው ይታያል። በአገር ዐቀፍ ደረጃ የወደቀውን የትምህርት ስርዓት ለማንሳት እየሠራ ነው። አንዳንዶቹን በልመና ጭምር፣ ለምሳሌ ከፖለቲካ ውጪ አባል በሆንኩበት አርክቴክቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች፣ ሲቪል መሀንዲሶች ማኅበር ጭምር የዜግነት ትብብር እንዲያደርጉ እየለመነ፣ በጦርነት የወደሙትን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመሥራት፣ ስርዓተ ትምህርቱን ከወደቀበት ለማንሳት የሚያደርገውን ድካምና ውጣ ውረድ እየተጠቀምንበት ነው። ኢዜማ ተጠቀመ የምልህ አገር ስትጠቀም ነው።

ስለዚህ ከመንግሥት ጋር ሥልጣን መጋራታችን፣ ምንም እንኳ በመንግሥት በጎ ፈቃድ ቢሆንም፣ አገር ተጠቅማለች። እንደ ፓርቲም ቅድም እንዳልኩት የመንግሥት መዋቅርን በቅርብ ለማየት፣ አጀንዳዎችን በቅርብ ለማግኘትለ ከዛም ደግሞ ነገ ብንመረጥና ብንሠራ እንዴት ዓይነት የማከናወን ብቃት እንዳለን ለማሳየት እድል ነበረን። ስለዚሀ ጎድቶናል ብለው ከሚመኑት ወግ አይደለሁም፤ አልጎዳንም ብዬ ነው የማምነው።

የመሪነት ምርጫ ፉክክሩ በፓርቲያችሁ ውስጥ ልዩነት እንደተፈጠረ ያሳብቃል የሚሉ ሐሳቦች ይነሳሉ። ልዩነት ከተፈጠረ ፓርቲው የመከፋፋል አደጋ አይገጥመውም ማለት ይቻላል?
ኹለት መሠረታዊ ጉዳዮችን በውል ካለመገንዘብ የሚመጣ ስጋት ይመስለኛል (ስጋቱን በመሠረቱ አልጋራም) አንደኛው የተለመደው አሮጌው የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው። አሮጌው የፖለቲካ አስተሳሰብ ማለት የፖለቲካ ልሂቃኑ ወይም መሪዎቹ በተኳረፉ ቁጥር፣ ታች ድረስ እየሄዱ የሚበተንበት ስርዓት ያከተመ ይመስለኛል። እንደሱ ዓይነት እድል ኢዜማ ውስጥ የለም።

እኛ በድሮው ፖለቲካና አስተሳሰብ የምንሄድ አይደለንም። ይህ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ኢዜማ የተመሠረተው በፖለቲካ ልሂቃን ስምምነት አይደለም። የኢዜማ የመጨረሻው ውሳኔ የሚሰጠው ወረዳ ላይ ያለው ነው። ስለዚህ ፕሮፌሰር ታች ወረዳ ሄዶ ለጉባኤ ካልተመረጠ መሪም አይሆንም፣ እንኳን መሪ የጉባኤ ተሳታፊ ሊሆን አይችልም።

- ይከተሉን -Social Media

ስለዚህ ከታች ወዳላይ የተገነባ፣ ምናልባትም በታሪክ የማውቀው የመጀመሪያው ፖለቲካ ፓርቲ ኢዜማ ነው። ሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ልሂቃን ይሰባሰባሉ፣ አባላት እየመለመሉ እያስገቡ ወደታች ነው መዋቅር የሚወርደው። የእኛ ግን ከታች ወደ ላይ ነው። ስለዚህ ብርሃኑና አንዱዓለም ቢጣሉ ወይም እኔና ሀብታሙ ኪታባ ብንቀያየም፤ እንደ ግለሰብ የኹለታችን ጉዳይ ነው የሚሆነው፤ ወይም በዙሪያችን ያሉ ጥቂት ጓደኞቻችን ጉዳይ ይሆናል። እንጂ ኢዜማን እስከ መሰንጠቅ እና መፍረስ ሊያደርስ የሚችል አጀንዳ በፍጹም ሊሆን አይችልም። አንደኛውና መሠረታዊው ጉዳይ ኢዜማ የተዋቀረበት የፖለቲካ አስተሳሰብና የተሠራበት ስሪት ፓርቲውን የመሰንጠቅ አደጋ ያመጣል የሚለው አያሳስበኝም።

ሁለተኛ ልዩነትን የምናይበት ባህል ይመስለኛል። እንዳልኩት ትንሽ መረርም ከረርም ያለ ይመስላል፤ ለውድድር የቀረቡት ተፎካካሪዎች በአደባባይ እያቀረቧቸው ያሉ ጽሑፎችና ንግግሮች ተራውን ሰው ወይም ለፖለቲካ ስስ ልብ ላለው ሰው የሚያስጨንቅና የሚስደነግጥ ሊሆን ይችላል። በመሠረቱ ልዩነትን የምናስተናግድበት ስርዓት እስካበጀን ድረስ፣ ዓላማችን ልዩነትን አጥፍቶ መጠርነፍ አይደለም። ከዚህ በፊት የነበሩ ገዢ ፓርቲችን የምንወቅስበት አንዱ ጉዳይ፣ ዜጎች በነጻነት ሐሳብ እንዳያራምዱ በጥቅማ ጥቅም ወይም በማስፈራት ይጠረንፏቸዋል የምንለውን፣ እኛም መልሰን ካደረግን ስህተት ነው።

ስለዚህ ልዩነት መኖሩን በጸጋ መቀበል ነው። አንድ ነን አልልም። ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንድ የምንሆነው በሥልታዊ ግቦቻችን ነው። ኢትዮጵያን መውሰድ ወደምንፈልግበት አቅጣጫ፣ የብሔር ፖለቲካን በዜግነት ፖለቲካ በመተካት ባለን ሐሳብ፣ ማኅበራዊ ፍትህን ለዜጎች እኩል እድል በሚሰጥ የፖለቲካ ተሳትፎ የኢኮኖሚ ነጻነትን በሚያጎናጽፍ መርሃችን ላይ አንድ ላይ ነን።

ግን እዛ ላይ እንዴት እንደርሳለን የሚል የአካሄድ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡ ይህ እኛ አገር ስለሆነና የፖለቲካ ባህሉ ስላልነበር እንጂ በሌላው ዓለም የተለመደ ነው።

እና የማረጋግጠው ብናሸንፍም ብንሸነፍም አንድ ላይ ለኢዜማና ለአገር መሥራታችን ይቀጥለል። ብናሸንፍ ከእነ አንዱዓለምና ሀብታሙ ጋር ተጨባብጠን የጋራ ሥራችንን እየሠራን እንቀጥላለን። ቢያሸንፉንም አብረን ተሰልፈን እንሠራለን። ስለዚህ ብዙ የሚያሳስብ ጉዳይ አይመስለኝም።

የፕሮፌሰር ብርሃኑና የእርስዎ ተፎካካሪ አንዷአለም፤ ብርሃኑ ነጋ ብልጽግናን አትንኩብኝ እንደሚሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቃለመጠይቅ ገልጸዋል። የኢዜማ መሪ ሆኖ ብልጽግናን አትንኩ ማለት ለኢዜማ ስጋት አይሆንም ወይ?
በመሠረቱ ይህ እውነት አይደለም። ለመከላከል ሳይሆን አንዷለም ይቅርታ ጠይቀዉበታል። ይቅርታ በአደባባይ የጠየቁበት ጉዳይ ስለሆነ እርሳቸው ሊያብራሩት ይችላሉ። ግን ተራ ስም ማጥፋት እና ጥላሸት መቀባት ካልሆነ በቀር፣ ኢዜማ ውስጥ ኢዜማ መሪ ሆኖ ብልጽግናን አትንኩብኝ ሲል፣ እኔ በነበረኝ ተሳትፎ ባለፉት ዓመታት አንድም ቀን አልሰማሁም፣ ሊልም አይችልም። ይህን በማለታቸው አንዷለም ተጸጽተው በአደባባይ ይቅርታ ስለጠየቁ፣ ይቅርታ በጠየቁበት ጉዳይ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠት ጠቃሚ አይመስለኝም። በይቅርታ ተዘግቷል ብዬ አስባለሁ።

የእናንተ አስመራጭ ቡድን የሐሳብ ልዩነቱን መሠረት በማድረግ ኢ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድም የእነ አንዱዓለምን ቡድን ለማፈን ሞክራል ተብሏል። ምንድን ነው ያደረጋችሁት?
አንድ ነገር ከማጥረት ልጀምር፤ የአስመራጭ ቡድን አንድን ለኢዜማ ይሠራል፣ ለአገር ይጠቅማል ያለውን የአመራር ስብስብ ለማስመረጥ የሚሠራ ቡድን፤ በሁሉም ተወዳዳሪዎች አላቸው። ይህ እንዲኖረን የሚያስገድደው የአስመራጭ ኮሚቴ ያወጣው መመሪያ ነው። ዘጠኝ አባላት ያሉት ቡድን ማዋቀር አለብን።

ይህ ቡድን የተዋቀር አሁን እጩዎች ከታወቅን በኋላ ነው። ለመወዳደርና ኢዜማን ለመምራት ፍላጎት ያላቸው እጩዎች ወደ አደባባይ መጥተው ተመዝግበው፣ እኔ መሪ መሆን እፈልጋለሁ፣ ሊቀመንበር መሆን ወይም ጸሐፊ መሆን እፈልጋለሁ ብለው ከተመዘገቡ በኋላ ነው ቡድን የተቋቋማው። ከዛ በፊት ቡድን የሚባል ነገር የለም።

አሁን የተባለው ሰነድ ተገኘ የሚባለው ይህ ከመሆኑ በፊት ነው። አንድ የመወዳደር ፍላጎት የነበረው ግሰለብ፣ አሸንፍበታለሁ ብሎ ያሰበውን ሰነድ አዘጋጀ። ሁላችንም የምርጫ ሰነድ እናዘጋጃለን፣ ይህም በጣም ዝርዝር ሥራ አለው። ይህ ሰነድ/ተገኘ የተባለው/ በሥራ አስፈጻሚ ተገኘ ተብሎ የውይይት አጀንዳ የሆነበት ጊዜ እኔ ከማን ጋር እንደምወዳደር እንኳ አልወሰንኩም ነበር። ከአንዷለምም፣ ከፕሮፌሰርም ጋር እየተወያየን ነበር። ሐሳባችሁ ምንድን ነው፣ አገርን ወዴት መውሰድ ነው፣ ኢዜማ ወዴት ነው የሚሄደው እያልኩ እያማከርኩ፣ ከኹለቱም ጋር በእኩል ቅርበትና በእኩል ርቀት እየተወያየሁ ነበር። እና የእናንተ ቡድን የሚለው መታረም አለበት። ያኔ ቡድን አልነበረም፤ እንደ ግለሰብ እኔም ከማን ጋር እንደምወዳደር እንኳ አልወሰንኩም ነበር።

አንድ ግለሰብ ይህን ጽፎ በራሱ ሥም፣ በኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ቀርቦ አዎን! እኔ ነኝ ያዘጋጀሁት፣ ራሴ ለመወዳደር እንዲያመቸኝ ያዘጋጀሁት ነው ብሎ መልስ ሰጥቶበታል። ፓርቲው ሕገ ደንብ በውስጥ አሠራር መሠረት ለዲሲፕሊን ኮሚቴ ተመርቶ እየተጣራ ያለ ጉዳይ ነው።
ይህን የመሳሰሉ ጉዳዮች በሌላም ወገን ይነሳል። ይህ የሚመነጨው ቅድም እንዳልኩት፣ አዲስ ስርዓት ለማሳየት፣ አዲስ ጅምር እየሞከርን ከመሆናችን የተነሳ፤ እዛም እዚህም ጥቃቅን የሚመስሉ ስህተቶች ይፈጠራሉ። አጠቃላይ ሂደቱን ግን ጥላሸት የሚቀባ ወይም ሌላ ሥም የሚያሰጥ ነው ብዬ ግን አላምንም።

ኢዜማ ባለፉት ዓመታት ስትራቴጂክ ግቦቹን ማሳካት እንዳልቻለ በተፎካካሪያችሁ ተጠቁሟል። በእናንተ በኩል ኢዜማ ስትራቴጂክ ግቡን አሳክቷል ማለት ይቻላል?
የሚቀሩና የሚጎድሉ ነገሮች አሉ፤ በአብዛኛው ግን አሳክተናል። የመጀመሪያው የአገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ አገርን ማስቀደም ነው። አንድ ጊዜ ፕሮፌሰር ሲናገር፣ አገር ከምትፈርስ ኢዜማ እንደ ፓርቲ ቢፈርስ ይሻላል ብሏል። ይሄ የኢዜማ መርህ ነው።

ስለዚህ አገርን ከመፍረስ ለመታደግ፤ ለምሳሌ የአገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ በወደቀበት ጊዜ፣ ሙሉ ድጋፍ በመስጠት አንዳንዶቻችንም ግንባር ድረስ ሄደን ለመሰለፍ መከላከያ ተመዝግበናል። ይሄ ብልጽግናን እንወዳለን ማለት አይደለም፤ ለአገር ነው የሠራነው። ያ ስልታዊ ግባችን ነው።
ሌላ ለምሳሌ አገራዊ ምክክር አለ። ለመካሄድ ዝግጅት ላይ ያለ፣ አጀንዳ የቀረጸ፣ ኮሚሽነሮች የተሰየሙለት ጉዳይ ነው። ይህን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ አኩርፎ ዳር መቆም ትክክል ስላልሆነ፣ የዴሞክራሲ መሠረትን ለመጣል በሚደረጉ ሙከራዎች በሙሉ፣ በኹለቱ ሥልታዊ ግቦቻችን በትብብር ስለምንሠራ፣ ይህ የትብብር ሥራ የሚቀጥል ይመስለኛል። እንዳልኩት ኹለቱን (ሥልታዊ ግቦች) በሚገባ አሳክተናል።

ያላሳካናቸው ኹለቱ፣ ጠንካራ ድርጅት መሥራትና ኹለተኛ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተወዳድሮ መንግሥት መሆን ነው። ይህ በአንድ ጀንበርና ምርጫ የሚሳካ አይደለም። ምንአልባትም ተከተታይ ምርጫ ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል። በኢዜማ አባላትና አመራር ብቻ የሚወሰን አይደለም።

ሦስተኛ ርዕሰ ጉዳይ ግን ተልይቶ ፕሮፌሰር ብርሃኑን ብቻ ወይም የተወሰነውን አመራር የሚያስጠይቅ አይመስለኝም። 400 የምርጫ ወረዳዎች አዋቅርረን ነበር፣ አሁን ምን ላይ አሉ? ስንቶቹ ሥልጠና ወስደወል? ምን ይጎድላቸዋል? ይህን የማደራጀት ሥራ በመሠረቱ የፕሮፌሰር ብርሃኑ ክንፍ የሚሠራው ሥራ አይደለም። ይህን ማደረጀት የሊቀመንበር ሥራ ነው። እንስማማና ፕሮፌሰርን ማገዝ ነበረበት ካልንና እርሱ ሥራ በዝቶበት ነበር ብለን ካመንን፤ ይህን መሥራት ያለበት ምክትሉ ነው። እሱ ደግሞ አሁን ለመሪነት የሚወዳደረው አንዱዓለም ነው።

በሌላ አነጋገር ስኬቱና ድሉን የጋራ እንደምናደርገው ሁሉ፣ ለነበሩብን ችግሮችና ድክመቶችም ኃላፊነቱን የምንወስደው እንደአመራር በጋራ ነው። ለምርጫ የሚወዳደሩትን አንዱዓለምና ሀብታሙን ጨምሮ ሁሉም እኩል ኃላፊነት የሚወስዱበት እንጂ፣ አንዱ በአንዱ ላይ ጣቱን የሚቀስርበት አይመስለኝም።

እኔ ለምሳሌ ለምክትል መሪነት ስወዳደር፣ ፕሮፌሰር የትምህርት ሚኒስትር እንደሆኑ አውቃለሁ፣ ሥራ እንደሚበዛባቸው አውቃለሁ። እርሳቸው በማይኖሩበት ጊዜ ሙሉ ኃላፊነቱን ወስጄ፤ በኋላ ይህን አልሠሩም ብሎ ለመውቀስ ሳይሆን፣ እሳቸው ያጎደሉት ወይም ባለመኖራቸው ጎደለ ብዬ የማስበውን አሟልቼ ለመሥራት ነው።

ስለዚህም ምናልባትም እሳቸውን የሚወቅሱ ሰዎች በትክክል ሥራቸውንና ኃላፊነታቸውን እነሱ ካለመወጣታቸው የተነሳ የመጡ ችግሮችም ሊሆኑ ስለሚችሉ አንዳንዴ ወደ ራስም መመልከት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። የወቀሳ ቃል ላለመናገር ነው ይህንንም የምለው እንጂ ኹሉም እኩል ኃላፊነት ነው የሚያነሳው።

ኢዜማ እንደ ፓርቲ በጣም ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ነገር ግን የብልጽግና ተለጣፊ ሆኗል የሚሉ ትችቶች ይነሳሉ። እውነት ተለጣፊ ሆኗል ወይ?
በተወሰነ ደረጃ በምናስበው ያህል ሕዝብን አደራጅተን ከሕዝብ ጋር በሰፊው መሥራት አለመቻላችን ጉድለታችን ነው። እያረምንና እየገነባነው የምንሄደው አንዱ ሥራችን አድርጌ እወስደዋለሁ። ምናልባትም መወዳደር ከምፈልግባቸው ዋነኛው ጉዳይ አንዱ ይሄ ነው።

ኹለተኛው ግን፣ ይሄ የሆነበት ምክንያት ሁሉንም ጉዳይ ኢዜማ ላይ ብቻ መጣልም ተገቢ አይመስለኝም። በወቅቱ የነበሩትን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ማስገባት ይገባ ነበር። በምርጫው ወይም ከምርጫው በኋላ በነበሩ ጊዜያት የአገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የወደቀበት ጊዜ ነበር።

እንደምናስታውሰው ከሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ከግብፅ ጋር ፍጥጫ ውስጥ የገባንበት ጊዜ ነበር። ጂኦፖለቲክሱ በከፍተኛ ሁኔታ ውጥረት ውስጥ የነበረበት ጊዜ ነበር። ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ገዢው ፓርቲ ባሉት ሰፊ አባላት ቁጥርና ባለው የገቢ እድል ተጠቅሞ በርካቶችን በእርዳታና በሴፍቲ-ኔት ጠርንፎ አባል ለማድረግ ቀለብ እየሰፈረላቸው ከወረዳ ጀምሮ እስከላይ ድረስ ባለው የሕዝብ ሠንሰለት ለመቆጣጠር አቅም ነበረው።

ይህንን ሁሉ እኛ አልነበረንም፣ ወይም ገንዘብ አሰልፈን ልንሰጥ የምንችልባቸው የሴፍቲኔት ቀለብ የምንሰፍርላቸው በኋላ ለእኛ በሰንሰለት ተጠርንፈው በፓርቲ ላይ ድምጽ ሊሰጡን የሚችሉ፣ እሱን ማድረግ አንችልም። ከዛ በተጨማሪ ኢዜማ ከተመሠረተም ገና አጭር ጊዜው ነበር። እንደፓርቲ ገና ሦስት ዓመት ሳይሞላው ነበር ወደምርጫ የገባነው።

እንደሚታወቀው ከ4 በላይ ፓርቲዎች ተዋህደው የተፈጠረ ፓርቲ ነው። እነዚህ ከተለያዩ ፓርቲ የመጣ የአሠራር ባሕል፣ የግለሰቦች ጠባይ፣ የአመራር ዘይቤ ይህ ሁሉ ተናቦና ተቀናጅቶ ወደፊት እንዲራመድ ብዙ ችግሮች ነበሩበት።

እንደኢዜማ ዛሬ ቆም ብለን ስንገመግም፣ ከነበሩብን ክፍተቶች ኹለት መሠረታዊ ችግሮችን በሚመጣው አመራር እናርማቸዋለን ብለን ከምናስበው አንደኛው፣ ሥልጡን ፖለቲካን መረዳት ነው። ሥልጡን ፖለቲካ ሲባል ከአሁን በፊት የተለመዱ የተቃውሞ ፖለቲካው የሚመራበት ወይ ፉጨትና ጩኸት ነው ወይ አንጃ ጠመንጃ ነው። ኢዜማ በእነዚህ በኹለቱ አይሄድም።

የሠለጠነ ፖለቲካ በሐሳብ ላይ የተመሠረተ እና እኛ እንዳደረግነው በዓለም ዐቀፍ ባለሙያዎች ተገምግመው ኢንዶርስ የተደረጉ፣ ተቀባይነት ያላቸው ለአገር ለወገን የሚጠቅሙ፣ ፖሊሲዎችን አርቅቀን የአደባባይ ውይይትና ክርክሮችን አድርገን ነው። ይሄ የሠለጠነ ፖለቲካ ነው።

ኹለተኛው ‹ፌል› ያደረግነው፣ የተናበበ አመራር ይዞ መሄድ ነው። እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆኖ፣ የአንዱን ጉድለት አንዱ እየሞላ የሚሄድ አመራር በበቂ ሁኔታ አላደራጀንም፣ አልነበረንም። በተለይ በሊቀመንበር ክንፍና በመሪ ክንፍ በኩል ያሉት አመራሮች ተጋግዘውና ተባብረው ከመሥራት ይልቅ አንዳንድ ጊዜ መጓተትና የሚና መደበላለቅ፣ የድርጅትን ጉዳይ መሪው እየሠራ፣ በመሪ በኩል ያሉ ሰዎች ወደዚህ ድርጅት እየሄዱ መደበላለቅ ነበረ። ስለዚህ በእነኚህ ሁሉ ችግሮች ተዳምረው ያሰብነውን ያህል ውጤት አላገኘንም። ወደፊት ይህንን እናርማለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች