መነሻ ገጽዜናትንታኔተጠርጣሪን ለመያዝ ቤተሰብን የማገት ድርጊት

ተጠርጣሪን ለመያዝ ቤተሰብን የማገት ድርጊት

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአራት ዓመት በፊት የተወገደውን ስርዓት ተክቶ የመጣውን አገዛዝ በትልቅ ተስፋ እንደተቀበለው የሚታወቅ ነው። ሆኖም ሕዝብ ከመጣው ለውጥ በወጉ ተጠቃሚ ሳልሆን ተመልሼ ከበፊቱ የባሰ ስርዓት ውስጥ ገብቻለሁ ሲል መስማት የተለመደ ሆኗል።
በርካታ ዜጎች በግጭቶችና በጦርነት ምክንያት ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ በርካቶችም በሰላም እጦት ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ስር የሰደደው ሥራ አጥነትም እንዲሁ ወጣቶችን ለአመጽ፣ ዝርፊያና ስደት እንደሚዳርጋቸው በተደጋጋሚ ይገለጻል።

ለረዥም ወራት የቆየው የሰሜኑ ጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች አሁንም ድረስ መቋጫ ባለማግኘታቸው በስጋት ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

በተለይ የሰሜኑ ጦርነት አፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎችን ክፉኛ ያደቀቀ ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን ጉዳቱ እንደቀጠለ መሆኑ ይነገራል።
ይሁን እንጂ መንግሥት አገሪቱ የሰሜኑን ጦርነት በድል እንደተወጣችው በመግለጽ፣ ከጦርነቱ ማግስት በሚፈጠሩ ችግሮች ማኅበረሰቡ ተቸግሯል በሚል በተለይ በአማራ ክልል በቅርቡ የተጀመረ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያደረኩኝ ነው ማለቱ ይታወቃል። ውጤታማ የሕግ ማስከበር ተግባር ነው ሲል በሚጠራውም በዚህ ዘመቻ የታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን ግን በርካቶች ሲገልጹ ይሰማል።

ለአብነትም ሰዎችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰር፣ የታሰሩበትን ቦታ መደበቅ፣ ለረዥም ጊዜ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ማቆየትና ከቤተሰቦቻቸው እንዳይገናኙ መከልከል ይገኝበታል። አካላዊ ጥቃቶች እንደሚሰነዘሩ ከሚነገረው በላይ ደግሞ በመንግሥት ሊያዙ ያልቻሉ ተጠርጣሪዎች እጅ እንዲሰጡ ለማድረግ የቅርብ ዘመዶቻቸውን ማገት በብዛት እየተስተዋለ እንደሆነ ይነገራል።

ይህም ሕዝቡ ለለውጡ ከነበረው ተስፋ አንጻር ይደረጋል ተብሎ ያልታሰበና፣ ከለውጡ እሳቤ በተቃራኒ የሚፈጸም ሆኖ መገኘቱ ብዙዎችን ያሳዘነ ስለመሆኑ ይደመጣል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሰኔ 04/2014 የተያዙ ሰዎች መብት በአስቸኳይ ይከበር ሲል ባወጣው መግለጫ፣ በዚሁ ሰበብ በተያዙ ሰዎች ላይ እየተፈጸሙ የሚገኙ የመብት ጥሰቶችን አብራርቷል።

በዚህም የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕግ ማስከበር በሚል ተይዘው ከነበሩ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የተወሰኑት ምሥራቅ ጎጃም ደጀን ወረዳ የትኖራ ቀበሌ እና ደቡብ ጎንደር ዞን ነፋስ መውጫ (ጋይንት) ከተማ ላይ ለይቶ ማቆያ ተብሎ በሚጠራ ቦታ በእስር ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ተጠርጣሪዎች ቤተሰብን ጨምሮ ከማንም ጋር መገናኘት እንደማይችሉ ኢሰመጉ ካሰባሰብኳቸው መረጃዎች ለመረዳት ችያለሁ ብሏል።

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ለገጣፎ ነዋሪ የሆኑ አንድን ግለሰብ በ20/09/2014 ከመኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ አባል ለጥያቄ ትፈለጋለህ በሚል ያለምንም ፍርድ ቤት ማዘዣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው እንደታሰሩና የተያዙበት ምክንያት እንዳልተነገራቸው፣ ብሎም የምግብና ውሃ አቅርቦት በሌለው ጠባብ እስር ቤት ውስጥ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ታስረው እንደሚገኙ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አክሎም፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ እንዲሁ ከፍተኛ የሆነ ከሕግ አግባብ ውጭ እስራት እየተፈጸመ ነው ብሏል። በዚህም ሰዎችን ወደ ፖሊስ ተቋማት በመውሰድ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንደሚፈጸሙ፣ እንዲሁም ማንም ሰው የታሰሩትን ሰዎች መጠየቅ እንደማይፈቀድለት ነው የገለጸው።

በቅርቡ ፍርድ ቤት በዋስ እንዲፈቱ የወሰነላቸው በአዲስ አበባ የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ፖሊስ ይዞ ማቆየቱም እንዲሁ የሕግ አግባብን ያልተከተለ እንደሆነ አስገንዝቧል።

የሕግ ማስከበር በሚልም ቤት እንፈትሻለን በማለት ከበባ በማድረግ ሕጻናትን ጨምሮ እናትና ሚስትን፣ ቤተሰብን የማዋከብና ፍርሃት ውስጥ የማስገባት ተግባር ስለመኖሩ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ሲወጡ ይሰማል።

ሌሎች እጅ እንዲሰጡ ሲባል በመያዣነት ተይዘው የሚሰቃዩ ሰዎች መበራከት፣ ሊጠይቁ የሄዱ ሰዎች እንግልት እንደሚደርስባቸው አልፎም ተርፎም በሄዱበት ታስረው ሊቀሩ እንደሚችሉ የሚገልጹ የሕዝብ እሮሮዎች መሰማት ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል።

ዘመዶቻቸውን ከማሳደድ በተጨማሪም፣ በዚህ መንገድ ተፈልገው የተያዙ ሰዎች እስር ቤት ውስጥ የሚደርስባቸው ስቃይ ከፍ ያለ እንደሆነም ነው እየተነገረ ያለው።

የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት አንቀጽ 17 ላይ ስለነፃነት መብት ሲገልጽ፣ ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ፣ ክስ ሳይመሠረትበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም ይላል።

አንቀጽ 19 ላይም እንዲሁ ወንጀል ፈጽመዋል በመባል የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያው በሚገባቸው ቋንቋ እንዲነገራቸው መብት አላቸው ይላል።

ይሁን እንጂ፣ በዚህ ወቅት ሰዎች በዘፈቀደ እንደሚታሰሩና ከታሰሩም በኋላ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ መብቶች እንደማይከበሩላቸው ነው የሚታየው።

- ይከተሉን -Social Media

በኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች 6ኛ ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ፣ የምክር ቤት አባል የሆኑት ክርስቲያን ታደለ ባለፉት ሦስት ሳምንታት «ሕግ ለማስከበር» በሚል በተከፈተው ዘመቻ ዜጎች በሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም ዐቀፍ የሰብአዊ መብት መከበር ስምምነቶች ጭምር ጥበቃ የሚደረግላቸውን መብቶቻቸውን የጣሰ፤ ከሕግ ማስከበሩ ይልቅ ሕጋዊ ሂደቶችን ያልተከተለ መሆኑ ከአፈፃፀሙ ተገንዝቤያለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም፣ ሕግ ለማስከበር በሚል ሕግ እየተጣሰ ሕጻናትን ጨምሮ 35 የሚደርሱ ዜጎች ያለፍርድ በፀጥታ አካላት ተገድለዋል። 40 የሚጠጉ የድርጅታችን መዋቅር አመራሮችና አባላት ታስረዋል። አስሮ መመርመርን የአገሪቱ ሕግ ባይፈቅድም ከ20 በላይ ጋዜጠኞች ታስረዋል። በርካታ ሺዎች ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በቀንና በሌሊት በፀጥታ አካላት እየታፈኑ ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደው ተሰውረዋል። እስከ አሁንም ፍርድ ቤት ያልቀረቡና ቤተሰብ የማይጠይቃቸው፤ የት እንዳሉም የማይታወቁ ዜጎች አሉ ሲሉ ነው ጥያቄያቸውን ባሰሙበት ወቅት የገለጹት።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ኅብረት ዳይሬክተር እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ባለሙያ መስዑድ ገበየሁ በዚህ ዙሪያ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹አንድን ሰው ላጠፋው ጥፋት የሚሆን ተጨባጭ ማስረጃ ካለ ተፈልጎ ይያዛል። ካልተያዘም በሌለበት ክስ ይመሠረትበታል። በተገኘ ጊዜም ባለው ማስረጃ መሠረት ጥፋተኛ ተብሎ ሊፈረድበት ይችላል።›› ነው ያሉት።

ከዚህ ውጭ የተጠርጣሪው ቤተሰብ የሚታገትበት የሕግ አሰራር እንደሌለ ጠቅሰው፣ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ብሎ የቅርቡን ሰው ማገት፣ ወንጀል ግለሰባዊ መሆኑን ወይም አንድ ሰው ለፈጸመው ወንጀል ተጠያቂው ራሱ ነው የሚለውን የሕግ ሥርዓት (Individualization of crime) የሚጥስ መሆኑን አመላክተዋል።

ሆኖም የቅጣት ዓላማ ጥፋተኛውን አካልና ማኅበረሰቡን ለማስተማር፣ አደገኛ ሰዎችን ከማኅበረሰቡ ለማራቅ ቢሆንም፣ በዚህች አገር ሕጋዊ አሰራር ከጠፋ ስለቆየ ሕገ መንግሥቱ ምን ይላል የሚለው ሰልችቶናል ሲሉ ተናግረዋል።

በቅርቡም መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች ሕግ በማስከበር ላይ ነኝ፣ ይህም ውጤት አስገኝቷል ሲል ይሰማል። ይሁን እንጂ ተግባሩ ከተጠርጣሪዎችና ከዘላቂ ሰላም አንጻር መታየት አለበት የሚል ሐሳብ አንስተዋል።

‹መንግሥት እያደረገ ያለው የጅምላ እስር ዘላቂ ሰላም ያመጣል ወይ?› ሲሉ ከጠየቁ በኋላም፣ ሰዎችን በሚታየው መልኩ በጅምላ ማሰር መጨረሻው ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው ብለዋል።

ስለሆነም ሰዎች ወደ ዘላቂ ሰላም እሳቤ እንዲመጡ ከጥያቄያቸው በመነሳት ለችግሮቻቸው ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በዚህም አሁን ላለው የተዘበራረቀው ሁኔታ መፍትሄው ከሕግ ይልቅ የፖለቲካ አካሄድ ነው ይላሉ።

- ይከተሉን -Social Media

አንድ ሰው ከተያዘ ማስረጃ ሊቀርብበት ያስፈልጋል፣ ነገር ግን አንድን ሰው ይዞ አቆይቶ መልቀቅ በራሱ እንዲሸማቀቅና ነጻነቱን እንዲያጣ እንዲሁም እንዲረበሽ የሚያደርግ በመሆኑ ሕጋዊ መሠረት የለውም ነው ያሉት።

አክለውም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕግ ፋይዳ ቢስ እየሆነ ነው ሲሉ ገለጸው፣ መንግሥት ያዋጣኛል ብሎ እየሄደበት ያለው መንገድም ትክክል እንዳልሆነ አመላክተዋል።

ለአብነትም አማራ ክልል ላይ በሚደረገው የሕግ ማስከበር የሚባል ተግባር ሰላም ተፈጥሯል ተብሎ ይወራ እንጂ፣ በየአካባቢው ውጥረት ነው ያለው ብለዋል።

በክልሉ እውነተኛ ፋኖና እውነተኛ ያልሆነ ፋኖ ተብሎ ፍረጃ መሰጠቱም አግባብ እንዳልሆነ አንስተው፣ ‹‹በጦርነቱ ወቅት ራሳቸው የብልጽግና ሰዎች ነበሩ ከፊት ሲሸሹ የነበሩት፣ አሁን ያ ወቅት ሲቀየር ማን ጠያቂ ማን ተጠያቂ ይሆናል።›› ሲሉ ጠይቀዋል።

‹‹በፋኖ ሥም ተደራጅቶ ወንጀል የሚሠራም ካለ፣ የደረሰው ጥፋት መቼ፣ የትና እንዴት እንዲሁም ከየትኛው ሕግ ጋር እንደሚቃረን በግልጽ መነገር አለበት። ሕዝቡም ዝርዝር ጉዳዮችን የማወቅ መብት አለው። ከዚያ ውጭ ዛሬ ሌላ ነገ ሌላ ምክንያት መስጠት፣ እገሌ ይቀረኛል እያሉ እያመላለሱ ማጎር፣ ሁኔታዎችን ከማባባስ በቀር ዘላቂ ሰላም አይፈጥርም።›› ሲሉ አሳስበዋል።

የዋስትና መብትን በሚመለከትም፣ ዋስትና መርህ ነው። በመርህ የተቀመጠን ጉዳይ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲፈቅድ፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በጭራሽ መሰረዝ የለበትም። ስለሆነም፣ ሰዎች በዘፈቀደ ተይዘው አንዱ የፈቀደውን ሌላው እየሻረ ሲጉላሉ ቆይተው በዘፈቀደ ሲለቀቁ እንደሚታይና ይህ ኹሉ ከሕግ የሚቃረን አሰራር ነው ብለዋል።

የማዋከብና በዘፈቀደ የማፈን ተግባር ምን ሊያስከትል ይችላል?
በርካታ ጥናቶች እንደሚገልጹት፣ በተለይ በአፍሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደልማድ ሆኖ የዘለቀው ለወጣቶች የተሻለ የሥራ ዕድል ባለመኖሩና ሥልጣን ላይ የሚቀመጠው መንግሥት ሕግና ስርዓትን ብቻ ተከትሎ የሚሠራ ባለመሆኑ ነው። ይህም ነው በአፍሪካ ውስጥ ፍላጎቶቻቸውን ለሚያስፈጽሙ የውጭ አገራት ሳይቀር ታዛዥ ሆነው እድሜያቸውን በከንቱ እንዲያሳልፉ የሚያስገድዳቸውም ይባላል።

የምክር ቤት አባል የሆኑት ክርስትያን ታደለም እንዲሁ በቅርቡ በተካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ፣ መንግሥት ከጠላት ማርከህ ታጠቅ ያለውን የአማራ ወጣት ከማነጋገር ይልቅ በያዘው ማባረር፣ በተለያዩ ክልሎች ታጥቀው መንግሥትን እየተዋጉ ያሉ ቡድኖችን መሰል ቅራኔ በሌሎች አካባቢም የሚያዋልድ ዘመቻ ላይ እንዳለ ለማሳሰብ እወዳለሁ ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

የሰብዓዊ መብት ባለሙያው መስዑድ በበኩላቸው፣ አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የዘፈቀደ እስር እየቀጠለ ሲሄድ፣ የሚያስከትለው ትልቁ ኪሳራ ሕግ ተደማጭነት እንዲያጣ ያደርጋል ነው ያሉት። ሰዎች ሕግ ሲጥሱ ምን እንደሚከተላቸው ካላወቁ፣ አለማወቅ ከተጠያቂነት ካለማዳኑም በላይ በሕግ የሚመራ ዜጋ መፍጠር ያዳግታል ባይ ናቸው።

ኹሉም እንደሚለው ሕግ መከበር አለበት፣ ሕግ በመጣስ እና ሕዝብን በማሸበር ግን መሆን የለበትም።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች