መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየመሶብ ታወር ፕሮጀክት በኹለት ወራት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግበት ሁኔታ ይፋ ይደረጋል ተባለ

የመሶብ ታወር ፕሮጀክት በኹለት ወራት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግበት ሁኔታ ይፋ ይደረጋል ተባለ

መንግሥት በወቅቱ ዋስትና ባለመስጠቱ 10 ቢሊዮን ዶላር ያቀረቡ ባለሀብቶች ተመልሰዋል

የአዲስ አበባ ልዩ መገለጫ ይሆናል ተብሎ ከአምስት ዓመት በፊት የታቀደው የመሶብ ታወር ፕሮጀክት በመጪዎቹ ኹለት ወራት ውስጥ መቼ ወደ ተግባር እንደሚገባ ይፋ ይደረጋል ተባለ።

የመሶብ ታወር ፕሮጀክት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ፀጋዬ ተክሉ፣ ከኹለት ዓመት በፊት ይጀመራል ተብሎ የነበረው የመሶብ ቅርፅ ያለው የአዲስ አበባ ልዩ መገለጫ መሶብ ታወር፣ በተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች እንዲሁም ለሽርክና ሽያጭ ሰነድ በማዘጋጀት እስከ አሁን መጓተቱን ገልጸዋል። ሆኖም በሚቀጥሉት ኹለት ወራት ውስጥ መቼ ወደ ተግባር እንደሚገባ የምናሳውቅ ይሆናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንዲሁም የፕሮጀክቱ ጥናት ካለቀ በኋላ ሥራው 49 በመቶ የውጭ ምንዛሬ የሚፈልግ በመሆኑ የውጭ አጋር ለማፈላለግ በተሠራ ሥራ፣ ከቱርክ፣ ዱባይ፣ ኳታር፣ ኮሪያ የተለያዩ አማራጮች መጥተው ነበር። በዚህም የመሶብ እና የኦዳ ታወር ላይ ለመሳተፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር ይዘው የመጡ ባለሀብቶች ስለመኖራቸውም ጠቁመዋል።

እንዲሁም በመሶብ ታወር ፕሮጀክት፣ በሪል እስቴት ልማት፣ በሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ እንዲሁም በመንገድ ግንባታ ላይ ለመሳተፍ 10 ቢሊዮን ዶላር ይዘው የመጡ ባለሀብቶች ነበሩ ሲሉ ገልጸዋል።

ትልቅ አቅም ያላቸው የኩዌት ባለሀብቶች መጥተው የነበረ ቢሆንም፣ በቅድሚያ የጠየቁትን ሉዓላዊ ዋስትና (sovereign guarantee) መንግሥት በወቅቱ ሊሰጥ ባለመቻሉ ተመልሰው ሄደዋል፣ ‹‹ፕሮጀክቱም ቢጫ አብርቶ ይገኛል›› ነው ያሉት።

ይህ የሆነው ከስምንት ወር በፊት እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹እኛ አቀባበል ባለመቻላችን፣ ሌሎች ደግሞ አቀባበል በመቻላቸው ብዙ እያመለጠን ያለ ነገር አለ። የኩዌት ባለሀብቶቹም ኡጋንዳ ሄደው ሉዓላዊ ዋስትና ተሰጥቷቸው በትልቅ ኢንቨስትመንት እየተሳተፉ ነው።›› ብለዋል።

ባለሀብቶቹም አሁንም ጥሪ ከተደረገላቸውና የጠየቁት ዋስትና የሚሰጣቸው ከሆነ ለመምጣት ዝግጁ ናቸው። ሆኖም ደክመው ስለሄዱ ከሌላ አመራር ጋር የመነጋገር ፍላጎት የላቸውም። ሊመጡ የሚችሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋበዟቸው ብቻና ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ባለሀብቶቹ በሽርክና ለመሥራት ይዘውት የመጡትን የውጭ ምንዛሬ፣ በሠላሳ ዓመት ከነትርፋቸው በውጭ ምንዛሬ ይዘው እንዲመለሱ አስቀድሞ መንግሥት ሊያውቀው ስለሚገባ ዋስትናው ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት። አክለውም፣ ባለሀብቶቹ በሠላሳ ዓመት ውስጥ ገንዘባቸውን ይዘው ከወጡ በኋላ ፕሮጀክቱ የሕዝብ እንደሚሆንም አመላክተዋል።

ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ገነት ሆቴል ያለበት ሥፍራ ላይ እንደሚገነባ ቀድሞ እቅድ እንደተያዘ አንስተውም፣ ከዚህ የተሻለ ቦታ በመፈለግ የቦታ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።

ቀድሞ ከተያዘው 30 ሺሕ ካሬ፣ አሁን ላይ 50 ሺሕ ካሬ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰውም፣ ሲጀመር የተያዘው 20 ቢሊዮን ብር በጀት በሲሚንቶ፣ ብረትና ነዳጅ ዋጋ ጭማሬ የተነሳ የበጀት ማስተካከያ ሊኖር ይችላል፤ እስከ 25 ቢሊዮን ብር ይደርሳልም ተብሎ ይገመታል ነው ያሉት።

የዲዛይን ማሻሻያ መደረጉን አንስተውም፣ እንዲህ ዓይነት ሕንጻዎችን ለማጽዳት አስቸጋሪ በመሆኑ ሕንጻው ራሱን በራሱ ማጽዳት እንዲችል፣ ሶላር ሲስተም እንዲኖረው፣ ከአረንጓዴ ልማት ጋር ተያይዘው እንዲሄዱ በጥቅሉ ከአሁኑ ዘመናዊ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ጋር ለማጣመር ማሻሻያ ይደረጋል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በፕላን ኮሚሽን የአምስት ዓመት ሜጋ ፕሮጀክቶች ዕቅድ ውስጥ ተካቶ እንደሚገኝ ያመላከቱት ሥራ አስኪያጁ፣ ይህም የመንግሥት በጀት የሚጠይቅ ሳይሆን መንግሥት መሬት በመስጠት ከማኅበረሰቡ ጋር በሽርክና የሚሠራው መሆኑን አብራርተዋል።

የመሶብ ታወር በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ቀዳሚ የማኅበረሰብ ልዩ መገለጫ (land mark) ፕሮጀክት መሆኑን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን የቀደመ ታላቅ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ታሪክ መልሶ ማምጣት አለመቻሉን አንስተዋል። አያይዘውም አዲስ አበባ ላይ መሶብ ታወርን፣ ኦሮሚያ ክልል ኦዳ ታወር፣ ሀዋሳ ላይ ሻፌታ ታወር፣ ባህር ዳር ላይ አገልግል ታወርን እንዲሁም በሌሎች ክልሎችም ቢያንስ አንድ ልዩ መገለጫ ለመሥራት መታቀዱን አመላክተዋል።

ይህን መሰል ፕሮጀክት በሆቴልና ቱሪዝም ልኅቀት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለቱሪስት መዳረሻ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ያነሱት ሥራ አስኪያጁ፣ መሶብ ታወር ከ12 ሺሕ በላይ ሌሎቹ ደግሞ እያንዳንዳቸው ከ5 ሺሕ በላይ የሥራ እድል ይፈጥራሉ ነው ያሉት።

ሥራ አስኪያጁ መሶብ ታወር ፕሮጀክት በ2008 በ25 ወለል የመጀመሪያ እሳቤ ተነስቶ ወደ 40 ወለል ከዚያም ወደ 70 ወለል በማደጉ፣ የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት እንዲኖረው መደረጉን አውስተዋል።


- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች