መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል የመሸጫ ስምምነቱ መቼ እንደሚጠናቀቅ አይታወቅም ተባለ

ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል የመሸጫ ስምምነቱ መቼ እንደሚጠናቀቅ አይታወቅም ተባለ

ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ከአምስት ዓመት በፊት የተጀመረው ፕሮጀክት፣ ስምምነቱ መቼ እንደሚጠናቀቅ እንደማይታወቀ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።

ለፕሮጀክቱ መሳካት ኹለቱም አገራት ድንበሮቻቸው ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር መዘርጋት የሚጠበቅባቸው በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ በኩል ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የመስመር ዝርጋታው የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ በኬንያ በኩል ያለው ግን እስከ አሁን አላለቀም ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን፣ ሂደቱ ስምምነት ያልተደረሰበት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በአንዳንድ ጉዳዮች መግባባትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በፈረንጆች 2017 እንደተጀመረ አንስተው፣ ከመጀመሩ በፊትም የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥና ሽያጭ አካል የሆኑ ስምምነቶች ነበሩ። ወደፊትም ስምምነቱ ምን እንደሚያመጣ አናውቅም ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በስምምነቱ ውስጥ የራስን ጥቅም የሚያስጠብቅ አንቀጽ እንዲኖር ያስፈልጋል። እኛ የምናቀርበውና እነሱ የሚያቀርቡትን ካላስማማን አልተስማማንም ማለት ነው ብለዋል። ሆኖም አሁን ላይ ስምምነቱ ባለማለቁ መነገር ያለባቸው ጉዳዮች ወደፊት ይገለጻሉ ሲሉ ጠቁመዋል።

ስምምነቱ በዚህ ቀን ይጠናቀቃል የሚባል አይደለም። ስምምነቱ ውስጥ ያሉ ጉዳዮች መግባባት ላይ ተደርሶባቸው ማለቅ ሲችሉ ነው አልቋል ማለት የሚቻለው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በዚህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ለኬንያ ምን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል ልትሸጥ ትችላለች ለሚለውም፣ ገና ያላለቀ ስምምነት በመሆኑ ይህን ያህል እንፈልጋለን ብለው አሳውቀዋል ለማለት እቸገራለሁ ብለዋል። አክለውም፣ ለመሸጥ የታሰበውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን የሚፈታው ስምምነቱ መሆኑን አመላክተዋል።

የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ኹለት ሺሕ ሜጋ ዋት መሸከም የሚችል ቢሆንም፣ ሆኖም ግን ኹለት ሺሕ መሸከም ይችላል ማለት ያን ያህል ይወስዳሉ ማለት ላይሆን ይችላል፣ ያነሰም ሊወስዱ ይችላሉ። ኹሉንም የሚፈታው የመጨረሻው ስምምነት ነው ሲሉ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ለሽያጭ የሚቀርበው ኤሌክትሪክ ኃይል ከአንድ ግድብ የሚሄድ ሳይሆን፣ ለዚሁ የሚሆን ወላይታ ሶዶ ላይ ከተሠራ ማሰራጫ ጣቢያ (converter station) የሚሄድ ነው ብለዋል።

ስምምነቱ አልቆ ፕሮጀክቱ ሊሳካ ይችላል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ በኢትዮጵያም በኬንያም በኩል ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው የወጣበት ሲሉ ገልጸው፣ ስለዚህ ፕሮጀክቱ አያዋጣም የሚባል አይደለም፤ ይሳካል ነው ያሉት። አያይዘውም፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር የለቀቀልንም ፕሮጀክቱ አዋጭ መሆኑ ታይቶ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በኩል 433 ኪሎ ሜትር፣ በኬንያ በኩል ደግሞ 612 ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እንደሚጠይቅ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት አገራት በመሸጥ በየዓመቱ ገቢ የምታገኝ ሲሆን፣ ይህም አገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።

በዚህም በየዓመቱ ከጅቡቲና ሱዳን የኃይል ሽያጭ ገቢ የምታገኝ ሲሆን፣ ለሱዳን ለመሸጥ የተዘረጋው መስመር ከዐስር ዓመት በፊት መጠናቀቁ ይታወሳል። ከኬንያ በተጨማሪ ለታንዛኒያም የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የመስመር ዝርጋታ እቅድ መኖሩ አስቀድሞ መገለጹ አይዘነጋም።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች