መንግስት የህወሃት ቡድን የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ ኤርፖርት እንዳያርፉ መከልከሉን አስታወቀ

0
823

ሐሙስ ሰኔ 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የህወሃት ቡድን የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ ኤርፖርት እንዳያርፉ መከልከሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

መንግስት በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል።

ከተለያዩ አለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበርም አስፈላጊ መሰረታዊ ድጋፎች በየብስም በአየርም ሲያጓጉዝ ቆይቷል።

በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሃት ቡድን ይህንን የመንግስትን ጥረት ጥላሸት ለመቀባትና የሃሰት ፕሮፖጋንዳውን ለመንዛት ሲል ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰብአዊ ድጋፎች የሚገቡበትን ሂደት ለማስተጓጎል በተደጋጋሚ መሞከሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።

በየብስ የሚገቡትን ሰብአዊ ድጋፎች ለትግራይ ህዝብ እንዳይደርሱ መንገድ በመዝጋትና የእርዳታ ማስተላልፊያ ኮሪደሮች አካባቢ ትንኮሳ በመፈጸም ከራሱ የፕሮፖጋንዳ ስሌት ባሻገር ለትግራይ ህዝብ ግድ አንደሌለው በተግባር እያሳየ መምጣቱን ነው መንግስት የገለፀው።

መንግስት በቡድኑ በኩል የሚመጡ እንቅፋቶችን በመቋቋም አስፈላጊውን ያልተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ማድረጉ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅና የተሰጠው መሆኑ ገልጿል።

ሆኖም አሁን መንግስት ያመቻቸውና በየቀኑ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም የህጻናት አልሚ ምግቦች የሚላክበትን የአየር በረራ የሽብር ቡድኑ መከልከሉና ከትናንት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ ኤርፖርት እንዳያርፉ ማድረጉ ታውቋል።

መንግስት ይህ የህወሃት ቡድን እርምጃ ቡድኑ የትግራይን ህዝብ የሃሰት ፕሮፖጋንዳው መሳሪያ ከማድረግ ውጪ ሌላ አላማ እንደሌለው ዳግም በተግባር የሚያረጋግጥ ነው ብሏል።

ይህንን የቡድኑን ውሳኔ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው የክልከላውንም ምክንያት እንዲያጣራም መልዕክቱን አስተላልፋል።

በተጨማሪም መንግስት እስካሁን ሲያደርግ እንደቆየው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ የትግራይ ክልል ዜጎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here