መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየ”ቀይ አሻራ ይፋፋም!” ጥሪ

የ”ቀይ አሻራ ይፋፋም!” ጥሪ

አኬልዳማ እየተባለች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ደም ምድር እየተገለጸች በምትገኘው ወለጋ ሰሞኑን የተሰማው ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ዓለም ከዳር ዳር ሰምቶት እያወገዘው ይገኛል። ሠሞኑን የአገራችንን ኢ-መደበኛ ሚዲያ ተቆጣጥሮ የቆየው ይህ ግፍ ብዙ ፅንፍ የወጡ ጉዳዮችን እንድንታዘብ አድርጎናል።

ሰቅጣጭ ምስሎችን እያዘንን እና እየተቆጨን እንድንመለከት ከማድረጉ በተጨማሪ፣ ምንም ልናደርግላቸው የማይቻለንን የዜጎችን ሰቆቃ አሰምቶን እንድንብሰለሰል እንቅልፍም እንድናጣ አድርጎናል። ሩቅ አገር ቢፈፀም የሚያሳዝነን ድርጊት እኛው ላይ በእኛው ተፈፅሞ ዓለም ሲነጋገርበት አየን።

ይህን ድርጊት ለይስሙላም ቢሆን ያላወገዘ ባይኖርም የተወሰነው የተደሰተ ይመስል ዝምታን መርጦ ከጨፍጫፊዎቹ ጎን መቆሙን ዐሳይቷል። አቅም ያለው መንግሥት ብሔራዊ ሐዘን ማወጅ ሲከለክልና እርምጃ ለመውሰድም ሲያመነታ ያዩ አቅም የሌላቸው አዛኝ ሰዎች ግን በተሻለ የተቻላቸው ሲጥሩ ተስተውለዋል።

የሕዝቡን እሮሮ ከማሳወቅ ባሻገር፣ ከግድያው ተርፈው በየጎጡና ጥሻው ተሸሽገው ያሉ ተጨማሪ ግፍ እንዳይፈፀምባቸው አልያም እርዳታ እንዲያገኙ ሲጥሩ ተስተውለዋል። መንግሥት ጉዳዩን ጆሮ ዳባ ልበስ ያለ ይመስል ችግኝ ተከላና ሌሎች አርቲ ቡርቲ የሆኑ መርሃ ግብሮችን ሲያከናውን በመታየቱ በብዙዎች ተኮንኗል።

የቻሉ በጽሑፍ፣ በዜማና፣ በግጥም እንዲሁም በንግግር የሁኔታውን አስከፊነትና የመንግሥት ባለሥልጣናትን እንዝህላልነትንም ሆነ ተሳታፊነት ለሕዝብ ሲያሳውቁ፣ ያልቻሉ ደግሞ በቅስቀሳው ተሳትፈው ኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲያውቀው አድርገዋል። በዚህም ሂደት በርካታ የዓለም መገናኛ ብዙኀን ሲዘግቡት፣ የእኛዎቹ የመንግሥት ልሳኖች ግን አፋቸውን እንደጋሪ ፈረስ ተለጉመው ዝምታን መምረጣቸው ብዙዎችን ይበልጥ አብግኗል።

ከሕዝብ በሚሰበሰብ ሀብት የኅብረተሰቡ ስሜት እንዲጨቆን ማድረጉ ሳያንስ፣ “መርጦ አልቃሽ” የሚል ሥያሜ በማሰጠት ለማሸማቀቅ የተጀመረው አካሄድም ከሽፎ ታይቷል። በአማራ ክልል የተፈፀሙትን አጉልተው ለማሳየት የሚላላጡ የአሁኑን በለሆሳስ ማለፋቸውም ትዝብት ላይ የጣለ ነበር።

ይህ ሁሉ የሐዘን ክስተት በተፈጠረበት ሳምንት መንግሥት “አረንጓዴ አሻራ” ብሎ ኑ ችግኝ ትከሉ ማለቱ ብዙዎች ደጋፊዎቹን ጭምር አሳፍሯል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ “ሰው እየተነቀለ ችግኝ መትከል ለማን እንዲሆን ነው” በሚል መጪውን ለማመላከትም ተሞክሯል። በሌላ በኩል ወለጋ የሚፈፀመውን ግፍ ዓለም ጭምር እንዲያውቀው “ቀይ አሻራ” እና ሌሎች መፈክሮች መቀስቀሻ መፈክሮች ሆነው በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ሲሰራጩ ታይተዋል።

“ቀይ አሻራ” የሚለው ለአረንጓዴው ምትክ ሆኖ የቀረበ እንደሆነ ቢነገርም፣ የመራጮቹ ሐሳብ ስላልተካተተበት ለበርካታ መላምት መንስዔ መሆኑ ታይቷል። ቃሉ ለምን ተመረጠ? ከሚል ጥያቄ ግርጌ የመንግሥት እጅ እንዳለበት ጭምር የሚጠቁም የሴራ ጥንስስ መኖሩም ተጠቁሟል። “ነጭ ሽብር በቀይ ሽብር ይቀለበሳል” ሲባል እንደነበረው፣ አረንጓዴው ተነቅሎ “ቀይ አሻራ ይፋፋም” የሚል ትውልድ እንደሚነሳ አመላካች አስተያየቶችም ተሰጥተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች