የብር ዋጋ መዳከም ለኢትዮጵያ ጥቅም ወይስ ጉዳት?

0
3233

የኢትዮጵያ መገበያያ ብር ከዶላር ጋር ያለው የምንዛሬ አቅም በተለይ ባለፉት ኹለት ዓመታት በመንግሥት ውሳኔ በከፍተኛ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሽቆልቁሏል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በተከተለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የኢትዮጵያ ብር ከዶላር አንጻር ያለውን የምንዛሬ ተመን እንዲያሽቆለቁል ያደረገው የውጭ ንግድን ለማበረታታትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት በሚል ስሌት ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ከኹለት ዓመት በፊት የጀመረው “አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን አሠራር፣ የኢትዮጵያን ብር ትክክለኛ ዋጋውን እንዲያገኝ እና የውጪ ንግድን ለማሳደግ ይረዳል በሚል የብርን የምንዛሬ ተመን ከንግድ አጋር አገራት ተመን አንጻር እያዳከመ መጥቷል። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብርን የውጭ ምንዛሬ ተመን በየጊዜው በከፍተኛ መጠን እንዲያሽቆለቁል ማድረጉን ተከትሎ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ የኢትዮጵያ ብር በከፍተኛ ሁኔታ የዋጋ ማሽቆልቆል ገጥሞታል፡፡

ከኹለት ዓመት በፊት ሰኔ 16/2012 የአንድ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተመን 43 ብር ከ494 ሳንቲም ነበር፡፡ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ሰኔ 16/2014 ድረስ አንድ ዶላር 52 ብር ከ33 ሳንቲም ሲሆን፣ በኹለት ዓመት የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ምንዛሬ ጋር ሲነጻጸር 10 ብር የሚጠጋ ቅናሽ ታይቶበታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የብር ዋጋ ከውጭ ምንዛሬ አንጻር ያለው ዋጋ እንዲቀንስ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማት ግፊት ሲያደርጉ ነበር፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም መንግሥት የብርን ዋጋ ያወረደው የውጪ ንግድን ለማሳደግ አስቦ ሳይሆን፣ የዓለም ዐቀፍ ገንዘብ ተቋማት ጫና በርትቶበት ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት እንደ ኢትዮጵያ ሸማች ወይም የውጪ ምርት በገፍ የሚያስገቡ አገራት የመገበያያ ገንዘባቸው ዋጋ ካሳጡ ለዋጋ ግሽበት እንደሚጋለጡ በመጥቀስ ነው፡፡

እንደ ዓለም ባንክና ዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ፈንድ (አይ.ኤም.ኤፍ.) ያሉ የዓለም ዐቀፍ ገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ያለው የምንዛሬ ተመን እንዲዳከም ሲያደርጉ የነበረው ግፊት፣ ከኹለት ዓመት ወዲህ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም ከኹለት ዓመት በፊት ከዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍና የዓለም ባንክ ለሦስት ዓመት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ድጋፍ በተመለከተ ባደረገው ውይይት እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠው በሂደት ብርን ማዳከምና ከጥቁር ገበያው ጋር ማመጣጠን ነበር፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያ ከገባችበት የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለመውጣት የዓለም ዐቀፉ ገንዘብ ተቋም፣ አይ ኤም ኤፍ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሲመቻችላት፣ ከተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በዋነኝነት የብር የውጭ ምንዛሬ ተመንን በፍጥነት መቀነስና የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በሂደት በገበያ ፍላጎት እንዲወሰን ማድረግ ነበር።

ኢትዮጵያ በገባችውም ውል መሠረት በቋሚነት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታትና የገበያ ሥርዓቱንም ለማስተካከል እየሠራች ትገኛለች። ይሁን እንጂ የብር ዋጋ በየጊዜው እየቀነሰ መምጣት የተዛባውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይበልጥ እያዛባው እንጂ የታሰበውን ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እየገለጹ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 7/2014 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ምንዛሬ ጋር ያለው ተወዳዳሪነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደና ዋጋ እያጣ ነው የሚል ጥያቄ ከምክር ቤት አባላት ቀርቦላቸው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ “የዚህ ሁሉ ውጤት መምጣት ከመጠን በላይ የነበረውን ኢትዮጵያ ብር ዋጋ በመቀነሳችን ነው” ብለዋል፡፡ የብር ዋጋ ከመጠን በላይ ከመለጠጡ (overvalued) የተነሳ መስተካከል ነበረበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ ብር ዋጋ በመቀነሱ፣ የውጪ ምንዛሬ የዋጋ ማስተካከያ ዕድገት አሳይቷል ይላሉ፡፡

ይሁን እንጂ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የውጭ ምንዛሬ ዕድገት የታየው በተለይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ገቢ የምታገኝበት የቡና ምርት ባለፉት ኹለት ተከታታይ ዓመታት ዓለም ዐቀፍ ገበያ ላይ የዋጋ ጭማሪ በመታየቱ ነው ይላሉ፡፡

ኮርፖሬት ፋይናንሻል ኢንስቲትዩት ስለ ገንዘብ የዋጋ ቅነሳ (money Devaluation) ከአንድ ዓመት በፊት በሠራው ሰፊ ትንተና፣ የገንዘብ ዋጋ መቀነስ ማለት “ከውጭ ምንዛሬ ወይም ደረጃ አንፃር የአንድ አገር የገንዘብ ዋጋ ወደ ታች መውረድ ነው” ሲል ይገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብር ካለው መግዛት አቅም በላይ ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማቱ ሲወተውቱ ነበር። ተቋማቱ ብር ዶላርን የመግዛት አቅሙ ከፍ ያለ በመሆኑም የወጪ ንግድን ለማበረታታት በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ የግብይት ሥርዓት ቢዘረጋ አገሪቱ ያለባትን ማነቆ መፍታት እንደሚያስችላት ሲያሳስብ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም የኢትዮጵያ ብር ዋጋ እንዲቀንስ መደረጉ የውጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግና የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እድል መፍጠሩን ቢገልጹም፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በዚህ አይስማሙም፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የመግዣ ዋጋቸውን በመጨመር ያለውን ፍላጎት እንዲቀንስ ለማድረግ ቢታለምም፣ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው ምርቶች መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ጭማሪ እንዲኖር አድርጎታል። የሚገቡትም ሸቀጦች በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋ መቀነስ ሳይሆን በከፍተኛ ሁኔታ በመናር የዋጋ ግሸበቱን በማባባስ የኑሮ ውድነቱን እንዳከበደውም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የባንክ ባለሙያው ዳንኤል ሽፈራው እንደሚሉት፣ ከውጭ ምንዛሬ አንጻር የብር ዋጋ ማነስ በዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማት የሚመከር ቢሆንም፣ ጥቅምና ጉዳቱ በአገራት ተጨባጭ ሁኔታ የሚመዘን ነው ይላሉ፡፡ የብርን ዋጋ በመቀነስ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብና የውጪ ንግድን ማሳደግ የሚቻል ቢሆንም፣ ሸማች ለሆኑ አገራት የጎንዮሽ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ይገልጻሉ፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት አንድ ዶላር በኢትዮጵያ ብር የሚመነዘርበት ዋጋ እየጨመረ ሲሄድ የዶላር አቅም እየጨመረ በሄደ ቁጥር፣ በዶላር ተገዝተው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያስከትላል ይላሉ፡፡ ባለሙያው እንደምክንያት የሚያነሱት፣ የውጭ ምርት የሚያስገቡ ባለሀብቶች ዶላር ለማግኘት የሚያወጡት ብር በየጊዜው እየጨመረ ሲሄድ ወይም የብር ዋጋ እየወረደ ሲሄድ በቀጥታ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደሚከሰት ጠቁመዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ጠቅሞናል ባሉት የብር ዋጋ መቀነስ ጥቅምና ጉዳት በተመለከተ “ዘ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚስት ቪው” ላይ በሰጡት ሙያዊ ትንተና፣ የብር ዋጋ መቀነስ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እድል የሚፈጥር ቢሆንም፣ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳሉት ይገልጻሉ፡፡

ከሚያስከትላቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል የዋጋ ንረት አንዱ መሆኑን የሚያነሱት ዋሲሁን፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚያስገቡ አስመጭዎች ዶላር በውድ ዋጋ በሚገዙበት ወቅት ገበያ ላይ ሲቀርብ በዚያው ልክ እየጨመረ እንደሚመጣ ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ የውጭ ምርቶችን የምትሸምት አገር እንደመሆኗ፣ ዶላር በብር መንዝረው የውጪ ምርት ለኢትዮጵያ ገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መሆኑን ዋሲሁን ያነሳሉ፡፡ በዶላር ዋጋ መጨመርና በኢትዮጵያ ብር ዋጋ ማነስ የሚከሰተው የውጪ ምርቶች ዋጋ መናር በከፍተኛ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ መሆኑንም ባለሙያው ያነሳሉ፡፡

የብር ዋጋ ማነስ በውጪ ንግድ ገቢና በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመነት ስበት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ቢኖረውም፣ ለውጭ ገበያ ከምትልከው በላይ የምታስገባው ከፍተኛ በሆነባት ኢትዮጵያ ጥቅሙ ያመዝናል ማለት እንደማይቻል የባንክ ባለሙያው ዳንኤል ይገልጻሉ፡፡ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማት እንደሚመክሩት የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ አግዟል እንዳይባል፣ የብር ዋጋ በየጊዜው እየወረደ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት እየተቸገረች መሆኑን የባንክ ባለሙያው ዳንኤል ይገልጻሉ፡፡

የገንዘብ ተመኑ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የመግዣ ዋጋቸውን በመጨመር የገቢ ንግዷን ለመተካትም ቢታሰብ እንኳን፤ አገሪቱ በዋነኝነት ከውጭ የምታስገባው ነዳጅ፣ መድኃኒትና መሠረታዊ ሸቀጦች መሆናቸውን የሚገልጹት ዳንኤል፣ የእነዚህ እቃዎች ዋጋ መናር ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያስከትልም ያስረዳሉ።

ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣ አገራት የገንዘባቸው ዋጋ እንዲቀንሱ ከሚመክሩባቸው ምክንያቶች መካከል አንድ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ መንግሥት የብርን ዋጋ እንዲቀንስ በማድረጉ ኢትዮጵያ በውጪ ምንዛሬ እጥረት መፈተኗን ማስቀረት አለመቻሉን የባንክ ባለሙያው ዳንኤል ይገልጻሉ፡፡

የብር ዋጋ በየጊዜው እየወረደ መምጣቱ ጠቅላይ ሚኒስተሩ እንዳሉት ጥቅሙ የጎላ አለመሆኑን የሚገልጹት ዳንኤል፣ ለዋጋ ንረት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የብርን ዋጋ ማሳነስ አካሄድ ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ችግሩ ካልተቀረፈ፣ ቢያንስ በብር ዋጋ ማነስ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ማስቀረት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየወሩ የምታስመዘግበው የዋጋ ግሽበት ከ30 በመቶ በላይ በመሆኑ በዜጎች ላይ እያሳረፈ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ ሆኗል። ከዋጋ ግሸበትም ጋር ተያይዞ መሠረታዊ የሚባሉ ሸቀጦች ዋጋ መናርም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ባለፉት ኹለት ዓመታት የተተገበረው የብርን አቅም ማሳነስ እርምጃ፣ መንግሥት እንዳሰበው ውጭ ንግድን ማበረታትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን አለማስቀረቱን የባንክ ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡ በየወሩ እየገሰገሰ ለሚገኘው የዋጋ ግሽበት መንግሥት የኢትዮጵያን ብር ዋጋ እንዲቀንስ ማድረጉ አንዱ ምክንያት መሆኑን ዳንኤል ይናገራሉ፡፡

መንግሥት የኢትዮጵያን ብር ካዳከመባቸው ምክንያቶች መካከል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ዋጋ ከረከሰ በርካታ ገቢ ይገኛል የሚል ነበር፡፡ እንዲሁም የወጪ ንግዱም ይበረታታል በሚል ቢሆንም ከምርታማነት እንዲሁም ከተወዳዳሪነት ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here