መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናባለፉት 11 ወራት በአዲስ አበባ 23 ሰዎች ከሕንፃ ላይ ወድቀው መሞታቸው ተገለጸ

ባለፉት 11 ወራት በአዲስ አበባ 23 ሰዎች ከሕንፃ ላይ ወድቀው መሞታቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ በ11 ወራት 23 ሰዎች የግንባታ ሥራ እየሠሩ በነበረበት ወቅት ከሕንፃ ላይ ወድቀው መሞታቸውን የአዲስ አበባ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሉጌታ ሊክዲ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ሰዎች በግንባታ ሥራ ላይ በቀን ሠራተኝነት፣ በግንበኝነት እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ተቀጥረው በሚሠሩበት ወቅት ተገቢውን የደኅንነት መጠበቂያ ተጠቅመው መሥራት ባለመቻላቸው እና በሌሎች ምክንያቶች ከሕንፃዎች ላይ ወድቀው የሞትና አካል ጉዳት ያጋጥማቸዋል ብለዋል።

ከሐምሌ 1/2013 ጀምሮ መረጃው እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ባሉት 11 ወራት ብቻ 23 ሰዎች ሲሞቱ ከ50 በላይ የሚሆኑ እንዲሁ ለከባድ እና ለቀላል የአካል ጉዳት ተዳርገዋል ተብሏል። ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ ማንኛውም የግንባታ ሂደት በሚከናወንበት ወቅት የሕንፃውን ዲዛይን ወይም ካርታ ይዘው ከመጡ በኋላ ፍቃድ ሰጥቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ያደርጋል ብለዋል።

የግንባታው ሥራ በሚካሄድበት ወቅት በቆርቆሮ፣ በሸራ እና በሌሎች መሸፈኛዎች ተሸፍነው እና የሠራተኞች የደኅንነት ሁኔታ በጠበቀ መልኩ የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በአንድ ወይም በኹለት ወር ውስጥ በሕጉ መሠረት ክትትል የሚያደርጉ ባለሥልጣኑ የመደባቸው ሠራተኞች አሉ።

ይሁን እንጂ ሕጉን ጥሰው ሥራቸውን የሚያከናውኑ ድርጅቶች እና አካላት መኖራቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ሕገ ወጥ ግንባታ ያካሄዱ ድርጅቶች፣ የግንባታ ቁሳቁሶችን በማይፈቀድ ቦታ ላይ ያስቀመጡ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች 100 የሚሆኑ ድርጅቶች እና አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

መመሪያው የሚጠይቀውን ሙሉ ለሙሉ እስኪያሟሉ ድረስ የግንባታ ሂደቱን እስከ ማገድ እና የተባሉትን ሳይፈፅሙ የተገኙትን ደግሞ ጉዳያቸው በሕግ እንዲታይ የማስተላለፍ እርምጃዎች በባለሥልጣኑ መወሰዱን ኃላፊው አመልክተዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ከላይ ለተጠቀሱ እንከኖች በዋናነት የግንባታ ቁጥጥር አዋጅ ቢኖርም፣ አዋጁ ሳይታደስ ከ10 ዓመት በላይ ማስቆጠሩ እና ያለውም ሕግ እየተተገበረ አለመሆኑ ለችግሩ መከሰት ተጠቃሽ ምክንያት ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በቀጣይ በጀት ዓመት ከመጀመሪያዎቹ ወራት ጀምሮ ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ ለማጠናከር እና ተጠያቂነትን ለማሳደግ አዋጁን የማሻሻል ሥራ ያከናውናል ተብሏል።

በተጨማሪ ግንባታዎች በሚከናወኑበት ወቅት በሥራው ላይ ለተሰማሩ ሠራተኞች አንጸባራቂ፣ ሄልሜት እና ሌሎች የደኅንነት መጠበቂያዎች መሟላታቸውን እና ሌሎች የቁጥጥር ሥራዎችን ጨምሮ አሠራራቸውን ለመቆጣጠር በባለሥልጣኑ በኩል ብቻ የማይቻል ነው። በመሆኑ ከደንብ ማስከበር አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ የሚያደርስ ውይይት ይደረጋል ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በተጨማሪ በግንባታው ዘርፍ ተቀጥረው የሚሠሩ የሠራተኞች የደኅንነት ማስጠበቂያ እንዲረጋገጥ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

ባለሥልጣኑ ባለፉት ዐስር ወራት በከተማዋ የሚገነቡ ማንኛውም ግንባታዎች በሕግ የተፈቀዱ እንዲሆኑ መሪ ፕላኑንና የሕንፃ አዋጁን መሠረት በማድረግ ለ29 ሺሕ 942 ገንቢዎች የግንባታ ፈቃድ መስጠቱም ተመላክቷል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዐስር ወራት 10 ሺሕ 783 የፕላን ስምምነት፣ 3 ሺሕ 985 አዲስ ግንባታ ፈቃድ፣ 968 የማሻሻያ የግንባታ ፈቃድ፣ 174 ቀደም ብለው ለተገነቡ ሕንፃዎች የግንባታ ፈቃድ፣ 1 ሺሕ 27 ሕንፃዎች የማራዘሚያ ፈቃድ፣ 11 ሺሕ 418 ግንባታዎች የእድሳት ፈቃድ መስጠቱም ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች