በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ በርካታ የፌዴራል ተቋማትን የበጀት አጠቃቀም አስመልክቶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በየዓመቱ የሚያካሂደውን ኦዲት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል።
ይህም የኦዲት ሪፖርት በመንግሥት የተቀረጹ ፕሮጀክቶች የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋላቸውንና የታለመላቸውን ግብ በስኬት መወጣታቸውን ለማወቅ የሚያስችል እንደሆነ ይነሳል። ሆኖም በየዓመቱ የተደረጉ የተጠቃለሉ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በየዓመቱ በርካታ ገንዘብ በእነዚህ ተቋማት ያለአግባብ ባክኖ እንደሚቀር ነው።
የቅርብ ጊዜው ይቆየንና፣ ለአብነትም መለስ ብለን ከ10 ዓመት የነበረውን እናውሳ። በግንቦት ወር 2002 ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበ የ2001 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት መሠረት፣ የጎላ ክፍተት አሳይተዋል ተብለው በተለዩ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት ተገኝቶባቸው ነበር።
በዚህም በፋይናንስ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 17/1989 አንቀፅ 38 እና 40 በተደነገገው መሠረት የሰነድ ሂሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ36 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች 1 ቢሊዮንና 400 ሚሊዮን ብር ውዝፍ የሰነድ ሂሳብ ተገኝቷል። ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት ደግሞ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር ነበሩ።
ይህ ውዝፍ የሰነድ ሂሳብ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ከፍተኛ ገንዘብ የነበረ ሲሆን፣ በመሥሪያ ቤቶች የሥራ ማስኬጃ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የሥራ እንቅስቃሴን የሚያዳክም ከመሆኑም በላይ ለምዝበራና ለብክነት ሰፊ በር የሚከፍት መሆኑ ይጠቀሳል። ችግሩ የሚከሰተውም ተቋማቱ የፋይናንስ ደንብና መመሪያዎችን ተከትለው ባለመሥራታቸው እንደሆነ ነው የሚገለጸው።
በየዓመቱ የሚቀርቡ የበጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የሆነ የበጀት ምዝበራና ብክነት የሚፈጸምባቸው ቀዳሚ ተቋማት ናቸው። በተጨማሪም በገቢዎች ሚኒስቴር ስር የሚተዳደሩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከፍ ያለ የሕዝብ ሀብት አላግባብ እንደሚያባክኑ በኦዲተር መሥሪያ ቤቱ በኩል ይገለጻል።
እንደማሳያ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የ2013 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛና ካፒታል በጀት ብሩ በድምሩ 286 ሚሊዮን ብር በላይ ሥራ ላይ አላዋለውም።
ዩኒቨርሲቲው ወደ ውጪ ለትምህርት የሚሄዱ መምህራን የትራንስፖርት አበል ክፍያ ማቋረጥ ሲገባው ባለመቋረጡ፣ ሥራ ለለቀቁ ሠራተኞች ያላግባብ ደሞዝ በመክፈልና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች አላስፈላጊ ወጪዎችን በማውጣት የመንግሥትን በጀት ለታለመለት ዓላማ ሳያውል መቅረቱ ተመላክቷል።
በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲሁ ተመሳሳይ የሀብት ብክነት የሚፈጽሙ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ደግሞ በኦዲት አሰራሩ መሠረት የታዩ ክፍተቶች ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ እንደማይወስዱ ተመላክቷል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2013 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ግኝት እንደሚያሳየውም በበጀት ዓመቱ የተፈቀደው በጀት ብር 136 ሚሊዮን 711 ሺሕ 682 ብር ሲሆን፣ በሂሳብ መደብ ብር 145 ሚሊዮን 929 ሺሕ 931 ብር ወጪ የተደረገ በመሆኑ ከተመደበው በጀት በላይ 9 ሚሊዮን 218 ሺሕ 249 ብር ባልተፈቀደ በጀት ክፍያ ተፈጽሟል።
በመሥሪያ ቤቱ በዋናው ፋይናንስ በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የሂሳብ መደቦች ከተደለደለው መደበኛ በጀት ሥራ ላይ ያልዋለ 128 ሚሊዮን 488 ሺሕ 326 ብር ተገኝቷል።
እንዲሁም በየአገራቱ በሚገኙ ኤምባሲዎች ውስጥ በበርካታ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከሕግ አሠራር ውጭ መባከኑን ሪፖርቱ ያመላክታል።
ባለፈው ሳምንት (ማክሰኞ ሰኔ 14/2014) የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች 6ኛ ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት ምክር ቤቱ ያጸደቀውን የ2013 በጀት ለታቀደለት ዓላማ መዋል አለመዋሉን ተከታትሏል።
በዚህም በተመረጡ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተከናወነው ኦዲት እንዳስረዳው፤ ጋምቤላ እና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲዎች በድምሩ 1 ሚሊዮን 513 ሺሕ ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት እንደተገኘባቸው ተመላክቷል።
ሐዋሳ፣ ሚዛን ቴፒ እና ቀብሪ ደሃር ዩኒቨርስቲዎች ደግሞ በድምሩ 1 ሚሊዮን 1 ሺሕ ብር በላይ በክፍያ መመሪያ ከተወሰነው የገንዘብ መጠን በላይ ተከፍሎ መገኘቱን ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ አስገንዝቧል።
የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተም የሰነድ ሂሳብ በወቅቱ ለማወራረድ ሲጣራ፣ በ133 መሥሪያ ቤቶች እና በ26 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች 13 ቢሊዮን 100 ሚሊዮን 235 ሺሕ 836 የሚሆን ብር እና በአራት መሥሪያ ቤቶች ከሥራ ተቋራጮች የሚፈለግ ያልተሰበሰበ 10 ሚሊዮን 183 ሺሕ ብር በላይ በደንቡ መሠረት እንዳልተወራረደ ተገልጿል።
በተጨማሪም፣ በስድስት መሥሪያ ቤቶች እና በሰባት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች 106 ሚሊዮን 841 ሺሕ ብር በላይ ማስረጃ ባለማቅረቡ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ያልተቻለ ተሰብሳቢ ሂሳብ መኖሩም ነው በኦዲት ሪፖርቱ የተመላከተው።
እንዲሁም ገቢ ካልሰበሰቡ መሥሪያ ቤቶች መካከል በጉምሩክ ኮሚሽን የቃሊቲ እና የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በድምሩ 260 ሚሊዮን 995 ሺሕ ብር በላይ፣ በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች የባሕር ዳር ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ ምዕራብ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እና የቅዱስ ጴጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በድምሩ 85 ሚሊዮን 693 ሺሕ 695 ብር እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል።
ማስረጃ ባለመሟላት ምክንያት የገቢውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ስላልተቻለ የተሰበሰበውን ገቢ ሂሳብ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግም እንዲሁ፣ በሰባት መሥሪያ ቤቶች ከተለያዩ ገቢዎች የተሰበሰበው ገቢ 154 ሚሊዮን 406 ሺሕ ብር በላይ አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎች ባለመሟላታቸው የገቢውን ሂሳብ ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለመቻሉን ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ አስረድቷል።
ምክር ቤቱ የኦዲት ሪፖርቱ ለሁሉም አስፈጻሚ አካላት ደርሶ ተገቢው ማስተካከያ እንደሚደረግ እና የማያስተካክሉ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እንዲሁም አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚደረግ አስገንዝቧል። ሆኖም ከዚህ መሰል የካሜራ ፊት ንግግር የዘለለ እርምጃ ሲወሰድ አይስተዋልም የሚሉ ቅሬታዎች ይደመጣሉ። በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው የተነሱ የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ወይም ተጠያቂ የሆኑ አካላት ነበሩ ለማለትም አያስደፍርም። ቢኖሩ እንኳን ለሕዝብ ግልጽ አለመሆኑ ነው የሚነገረው።
ተቆጣጣሪ አካላት የዋና ኦዲተርን የኦዲት ሪፖርት በግብዓትነት በመጠቀም ሥራቸውን የሚከውኑበት አግባብ ዝቅተኛ መሆኑን የፌዴራል ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሲገልጽ ይደመጣል።
ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱም ቢሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር፣ በተከታታይ የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ ‹‹ተቀባይነት የሚያሳጣ›› የሚል አስተያየት የቀረበባቸውን መሥሪያ ቤቶች የመሩ የሥራ ኃላፊዎች ለመንግሥት የሥራ ኃላፊነት የማያበቃ በሚል እንዲያዙ አልፎም ተጠያቂ እንዲሆኑ መሥራት እንደሚኖርበት ይታመናል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ስሜነህ ኪሮስ በጉዳዩ ዙሪያ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ተቋማት የተበጀተላቸውን በጀት ለታለመለት ዓላማ ያውላሉ የሚለውን ከመገመት ውጭ ግልጽ የሆነ ማስረጃ ሲያቀርቡ አይስተዋሉም የሚል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።
ሆኖም በኦዲተር ተቋም የፋይናንስ አጠቃቀም ጉድለት እንዳለባቸው ሲገለጽ ይታያል። በምን ምክንያት ጉድለት ውስጥ ገቡ የሚለውን ግን ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ነው የሚያብራራው ነው ብለዋል።
ጉድለት የተገኘባቸው ተቋማት ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ወቅትም፣ እንደማስረጃ የሚቀርብባቸው ይኸው የኦዲት ግኝት ሪፖርት መሆኑን ጠቅሰው፣ ኦዲት ሪፖርቶች በራሳቸው አዘውትሮ ክፍተት ይታይባቸዋል ብለዋል።
ለዚህም ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ኦዲት የሚያደርጋቸውን ተቋማት የሥራ ሁኔታ ምን ያህል ይረዳቸዋል የሚለውን ጥያቄ አንስተው፣ አንዳንድ ተቋማት የተለያዩና ውስብስብ ሥራዎችን ነው የሚሠሩት። ስለዚህም ኦዲተሩ የተቋማቱን ሁኔታ ተገንዝቦ ሥራውን ይሠራል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።
በዚህም ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ በራሱ ኦዲት መደረግ ይኖርበታል ካሉ በኋላ፣ አንዳንድ ጊዜ የተቋማት ወጪዎች የሚወሰኑት በተለያዩ ባለሙያዎች በመሆኑ፣ ኦዲት በሚደረጉበት ጊዜ የወጭ ሰነዱን አልቀበልም እንዲሁም ትክክለኛ የፋይናንስ አሠራር አልተከተላችሁም ሲባሉ እንደሚታይ አመላክተዋል።
ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ወጭ የወጣባቸው ሰነዶችን አልቀበልም የሚላቸው የወጭ ምክንያቱና አሠራሩ ግልጽ አይደለም በሚልና ይህንም ገንዘቡን እንደባከነ በመቁጠር ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በእርግጥም በወቅቱ ሪፖርት የማያቀርቡ እንዲሁም ከትክክለኛው አሠራር ውጭ የሚሠሩ ተቋማት እንደሚኖሩ አንስተው፣ በአብዛኛውም ከሂሳብ አያያዝ ጋር የተያያዘ ጉድለት ነው የሚታየው ብለዋል። አክለውም፣ አንዳንድ መመሪያዎች በጣም ጠንካራ በመሆናቸው ተነጋግሮ ለመፍታት እድል እንደማይሰጡ ጠቁመዋል።
ሂሳብ የሚሠሩ ባለሙያዎች፣ የተቋሙ ኃላፊ እንዲሁም ኦዲተር አካሉ ኹሉም ክፍተት እንዳለባቸው ጠቅሰውም፣ እስከ አሁን በተገኘበት የኦዲት ጉድለት ተጠያቂ የሆነ ሰው አላየሁም ብለዋል። ኃላፊው የሚጠየቀው የፖለቲካ ኪሳራ ሲያጋጥመው ነው። የፖለቲካ ኪሳራ ሲያጋጥማቸው ኦዲት ተሰርቶ ይቀርብባቸዋል። ወይም ይታሰሩና ከዚያ በኋላ ኦዲት ተደርጎ ጉድለት ተገኘባቸው ይባላል በማለት ያለውን የተጠያቂነት አለመኖር ጠቁመዋል።
አክለውም ተጠያቂ የሆኑ ተቋማት ሊኖሩ ይችላሉ ካሉ በኋላ፣ ያለው ግን የፖለቲካ ተጠያቂነት በመሆኑ አጥፊው አካል ፍርድ ቤት ሳይሆን የሚቀርበው፣ ይህን አስተካክል ብሎ የሚነግርው ምክር ቤቱ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኃላፊዎችም እንዲያስተካክሉ እድሉ ሲሰጣቸው አስተካክለው መቅረብ ሲገባቸው፣ በቀጣይም ራሱን ደግመው ይዘውት ሲቀርቡ በጣም ያሳፍራል። ይህን ነውር ተሸክመው መቀጠልም ባልተገባቸው ነበር ባይ ናቸው።
ሕጉ የሚለው ግልጽ ነው ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹አንድ ኃላፊነት ያለበት አካል ኃላፊነቱን ካጎደለ አጎደለ ነው፣ በወንጀልም በፍትሐ ብሔርም ይጠየቃል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በአቅምና ብቃት ማነስ የሚፈጠሩ ችግሮች ስላሉ ችግሩን በአቅም ግንባታ ሥራዎች ማስተካከል ይቻላል›› የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።
ተቋማት በኦዲት የሚገኙባቸውን የፋይናንስ አያያዝ ጉድለቶች ከምዝበራ ጋር እንደማያያይዟቸው ገልጸው፣ ‹‹ሌቦቹ የሠለጠኑና የተቋሙን አሰራር የሚያውቁ በመሆናቸውም በሰነድ አስደግፈው ነው የሚሰርቁት። ስለሆነም በብዙ መሥሪያ ቤቶች ስንሄድ እንደምናየው ትልቅ የአቅም ማነስ ችግር አለ። ይህ የሚስተካከለው በወንጀል በመቀጣት ብቻ ሳይሆን የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የአሠራር ሂደቶችን በመፈተሽ፣ በማሻሻልና በመቆጣጠር ሊሆን ይችላል›› በማለት አስረድተዋል።
አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በቀረቡ የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች ጉድለት በተፈጠረባቸው ተቋማት ምን ያህል በሚሆኑት ክስ እንደተመሠረተ ለማወቅ ከፍትህ ሚኒስቴር ደጋግማ ብትሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል።
ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትም እንዲሁ በኦዲት ግኝት ሪፖርቱ ላይ ስላለው ግልጸኝነት እንዲሁም ጉድለት የታዬባቸው ተቋማት ክፍተታቸውን እንዲያስተካክሉ ብሎም ተጠያቂ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምን ድረስ እየሠራ እንደሆነ ለማካተት ተሞክሮ ሳይቻል ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014



