መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየዜጎችን ጭፍጨፋ ያልገታ “የለውጥ መንግሥት”!

የዜጎችን ጭፍጨፋ ያልገታ “የለውጥ መንግሥት”!

ከሦስትና አራት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እንዲከፈት የሚጠበቀው አጀንዳ እድገትና ለውጥ፣ አንድነትና ኅብረት ነበር፡፡ ነገር ግን ያ ሳይሆን ቀርቶ፣ ጦርነት፣ የንጹሐን እልቂትና መከራ የየእለት ዜና ሆኗል፡፡ ብዙ ተስፋ የተጣለበት፣ የኢትዮጵያ ትንሣኤ የሚታይበትን ዘመን ያመጣል፣ ያሻግራል የተባለና ራሱንም ‹የለውጥ ነኝ› ያለ መንግሥት፤ አሁን ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ ማስቆም አልቻለም፡፡ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን መነሻ በማድረግ፣ የፖለቲካ ምሁር በማናገርና የቀደሙ መዛግብትን በማገላበጥ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት፣ ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ በሚጠራው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር አሰቃቂ የንጹሐን ዜጎች ጅምላ ግድያ አስተናግዳለች። የንጹሐን ዜጎች ግድያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቀጥሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግር ተጋልጠዋል።

ባለፈው ሳምንት ሰኔ 11/2014 ደግሞ በምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ከ500 በላይ ንጹሐን የአማራ ብሔር ተወላጆች፣ በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሰው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጀው ሸኔ (የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት) ኃይሎች መገደላቸው ዓለምን ያስደነገጠ ድርጊት ሆኗል። በምዕራብና በምሥራቅ ወለጋ ዞኖች ማንነትን መሠረት ያደረገ ግድያ በንጹሐን ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ ያጋጠመ መሆኑን ተከትሎም መንግሥት ለዜጎች ጥበቃ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ተጠይቆ ነበር።

በምዕራብ ወለጋ በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ጅምላ ግድያ የመጀመሪያ ባይሆንም በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል። የንጹሐን ዜጎች ግድያ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን በስፋት የተቀባበሉትና የዓለም ማኅበረሰብ ያወገዘው፣ መንግሥት ዜጎችን የመጠበቅና ኢትዮጵያን ሰላም የማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የተጠየቀበት ክስተት ሆኗል።

መንግሥት በንጹሐን ዜጎች ላይ ስለተፈጸመው ግድያ በዝርዝር ያለው ነገር ባይኖርም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ስለ ግድያው መረጃ አውጥተዋል።

ኢሰመጉ ሰኔ 14/2014 በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ “የሸኔ ታጣቂ ቡድን” በቦታው ይኖሩ በነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸሙን ባደረኩት ማጣራት አረጋግጫለሁ ብሏል።

በጥቃቱ በብዛት ሴቶች እና ሕጻናት መሞታቸውን የገለጸው ኢሰመጉ፣ ከተጎጂዎች መካከል ጥቃቱን በመሸሽ መስጊድ ውስጥ ገብተው የነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና ጥቃቱ በጣም አሰቃቂ እና የጭካኔ ድርጊት መሆኑን በግልጽ የሚያሳዩ የአካል ጉዳት፣ እገታና ንብረት ውድመት መከሰቱን አስታውቋል።

የታጣቂ ኃይሉን ጥቃት በመሸሽ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ በየጫካው ተበታትነው እንደሚገኙ፣ ብዙ ቁጥር ያላቸው አስክሬኖች በአንድ አካባቢ ላይ በጅምላ እንደተቀበሩ ኢሰመጉ ይፋ አድርጓል።

በጥቃቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን እና ከሟቾች ውስጥ ብዙውን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውን ኢሰመጉ በመግለጫው አብራርቷል። በአካባቢው የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች በእሳት መቃጠላቸውን እና ጥቃቱ በከባድ መሣሪያ ጭምር በመጠቀም የተፈጸመ መሆኑን የገለጸው ኢሰመጉ፣ “ጉዳዩን አሳዛኝ የሚያደርገው አፋጣኝ የሆነ እርምጃ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተወሰደ ባለመሆኑ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ አካል ጉዳት እና ንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑ ነው” ብሏል።

ኢሰመጉ በመግለጫው በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ዘላቂ መፍትሄን እንዲያበጅ በተደጋጋሚ ጥሪ ባቀርብም፣ የፌዴራል መንግሥት እንዲሁም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱ እና ጥቃት አድራሾች ላይ ሕጋዊ ተጠያቂነትን ባለመመሥረቱ ይህ ዘግናኝ ድርጊት ለመፈጠሩ ምክንያት ነው ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ አካባቢ በሸኔ ታጣቂ ቡድን እና በመንግሥት የጸጥታ አካላት በሚወሰዱ እርምጃዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ንጹሀን ሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ንብረት ውድመት እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ኢሰመጉ ባደረኩት ማጣራት አረጋግጫለሁ ብሏል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) ታጣቂዎች መካከል ሲደረግ ከነበረው ውጊያ ጋር በተያያዘ ታጣቂው ቡድን በአካባቢው በሚኖሩ ሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብሏል።

ኹለቱ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ባወጡት መግለጫ በአካባቢው አሁንም ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት መኖሩን ጠቁመዋል። በመሆኑም ነዋሪዎች በአፋጣኝ ድጋፍ እንዲደርስላቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ተቋማቱ ይፋ አድርገዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ደኅንነት ካልተጠበቀ ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች መረዳቱን ጠቁሟል።

መንግሥት በሲቪል ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸምና አስፈላጊ የሆኑ የመከላከል እርምጃዎችን እንዲወስድ፣ በማንኛውም ሁኔታ ሲቪል ሰዎች የጥቃት ዒላማ እንዳይደረጉ ተገቢ የሆነ ጥንቃቄና ጥበቃ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያፈላልግ ኢሰመኮ ጠይቋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) መንግሥት በሲቪል ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የመከላከል እርምጃዎችን እንዲወስድ፣ በማንኛውም ሁኔታ ሲቪል ሰዎች የጥቃት ዒላማ እንዳይደረጉ ተገቢ የሆነ ጥንቃቄና ጥበቃ እንዲያደርግ እንዲሁም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያፈላልግ አሳስበዋል።

የዜጎችን ጭፍጨፋ ያልገታ “የለውጥ መንግሥት”!
በኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ከመንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡ የታጠቁ ኃይሎች በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቀጥሏል። በተለይ በኦሮሚያ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች በዜጎች ላይ የግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ የማፈናቀል፣ የንብረት ዘረፋና ውድመት ጥቃት ሰንዝረዋል።

- ይከተሉን -Social Media

መንግሥት ንጹሐን ዜጎችን ከታጠቁ ኃይሎች ጥቃት እንዲጠብቅ በየጊዜው ከሰብዓዊ መብት ተቋማት ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይወተውታሉ። በየአካባቢው የታጣቂ ኃይሎች ሰለባ የሆኑ ዜጎችም፣ አስቀድመው መንግሥት ጥበቃ እንዲያደርግላቸው በየጊዜው ጥሪ ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነቱ የሆነው መንግሥት፣ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ አልቻለም የሚሉ ትችቶች ከየአቅጣጫው ይቀርቡበታል።

ከየአቅጣጫው በመንግሥት ላይ የሚቀርበውን የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለመወጣት ክስ የሚያጠናክሩ በንጹሐን ዜጎች ጅምላ ግድያዎች አሁንም እየተፈጸሙ ነው። በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከልና ካማሽ ዞኖች ባለፉት ዓመታት ንጹሐን ዜጎች በጅምላ መገደላቸው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ መንግሥት በየጊዜው በግፍ የሚገደሉ ንጹሐን ዜጎችን ሞት ማስቆም አልቻለም።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ የሚጠራው አስተዳደር፣ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ አራት ዓመታት አልፈዋል። ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ነኝ ብሎ የሚጠራው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ኢትዮጵያን ከገጠሟት ችግሮች ያወጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፣ በተቃራኒው በለውጡ አስተዳደር የንጹሐን ዜጎች ሞት መቆሙ ቀርቶ በየአካባቢው ተባብሶ ቀጥሏል።

በኢትዮጵያ በተለይ ከ2008 ጀምሮ የወቅቱ መንግሥት በነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥርዓት ላይ ከተለያዩ ወገኖች ሕዝባዊ ተቃውሞዎች እየበረቱ የመጡበት ጊዜ ነበር። የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተከሠቱ ችግሮችን ማስቆም ባለመቻላቸው በ2010 በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን የተረከቡት።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኢሕአዴግ ሊቀ-መንበርነትና ከጠቅላይ ሚኒስትርነት በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ያቀረቡት ምክንያት፣ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን አለመረጋጋት እና የፖለቲካ ችግር ለማስወገድ የሚወሰደው መፍትሔ አካል ለመሆን በማሰብ መሆኑን በወቅቱ በሰጡት መግለጫ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ በወቅቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ፣ መጋቢት 24/2010 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ተረክበው ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመሩ አራት ዓመት አልፏቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስተሩ በወቅቱ ኢትዮጵያን ከገጠሟት ችግሮች እንደሚያወጧት በየክልሉ ተዘዋውረው ለሕዝብ ቃል ገብተው ነበር። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ የነበረው ችግር መቀረፉ ቀርቶ ተባብሶ ቀጥሏል። የታጠቁ ኃይሎች በየአካባቢው በተለይም በአሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በሲቪል ሰዎች ላይ ላለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲፈጽሙና ሲያፈናቅሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ኢትዮጵያን እያበለጸገ እንደሆነ በየጊዜው እየገለጸ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሰኔ 7/2014 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ “ሪፎርማችን ለማመን የሚከብዱ ውጤቶች እያመጣ ነው። ለእናንት አይደለም ለእኔ ለራሴ የፈጣሪን ደግነት ቸርነት የሚከናወን አልቲሜት ውጤት የሚታይባቸው አስደማሚ ውጤቶች በሪፎርም እየመጡ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

- ይከተሉን -Social Media

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር በየጊዜው ኢትዮጵያን እናበለጽጋለን ቢልም፣ ኢትዮጵያ ያጋጠማት የሰላም እጦት ለዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል። መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ባልቻለበት ሁኔታ፣ ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ መጥራቱን የሚነቅፉ አካላት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል።

ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ የሚጠራው አስተዳደር፣ ኢትዮጵያን የሚያጸና ለውጥ እያመጣሁ ነው ይበል እንጂ፣ ለውጡ በአግባቡ ባለመመራቱ ችግሩ “ከድጥ ወደ ማጡ” መሆኑን ብዙዎች ሲገልጹ ይደመጣሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ለውጥ እያመጣሁ ነው ከሚልባቸው ጉዳዮች መካከል ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አንዱ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና የፈጠረ በየወሩ እየናረ የቀጠለ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እያስተናገደች ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ ከሚጠራው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ከሚለው ለውጥ ጋር የሚጣጣም አይደለም የሚሉ ሐሳቦች ከፖለቲከኞች እስከ ፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን መሰማት ከጀመረ ሰነባብቷል። ለዚህም በቀዳሚነት የሚነሳው ምክንያት መንግሥት የኢትዮጵያ ሰላም እንዲሁም የዜጎችን ደኅንነት ማስከበር አልቻለም የሚለው ጉዳይ ነው።

ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም ዐቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህርና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ፣ “የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ለውጥ ላይ ነኝ ቢልም፣ ቀዳሚ ተግባሩን በመዘንጋቱ አሁን ላይ ከሕዝብ ጋር ያለው ግንኙነት በለውጥ መንፈስ የተቃኘ አይደለም” ይላሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ነገር፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር የመንግሥት የመጀመሪያ ተግባር የሆነውን ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ሲገባው፣ የዜጎች ሞትና መፈናቀል መባባሱን ነው።

ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በመንግሥት ላይ የሚነሳው ቀዳሚ ጥያቄ፣ “መንግሥት ሥልጣኑን በአግባቡ አልተጠቀመም የሚል ነው” ያሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣትና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ባልቻለበት ሁኔታ ቅድሚያ የሚሰጠውን ሰላም ዘንግቶ ስለ ለውጥ ማውራት ከሕዝብ ጋር ያራርቃል ይላሉ።

ለውጥ ማለት ቀድሞ መሠረታዊ የሕዝብ ችግሮችን መፍታት፣ ሕዝብ የሚረካበትና ምቹ የሆነ አገልግሎትና አስተዳደር መፍጠር ነው የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር አሁን ላይ ሕዝብ እያረካ ነው ማለት አይቻልም ይላሉ። መጀመሪያ አካባቢ ሕዝብ የተቀበለው ለውጥ የሚመስል ነገር ነበር የሚሉት መምህሩ፣ ቀስ በቀስ የተጠበቀው ለውጥ ከታሰበው መስመር ወጥቷል በማለት ያስረዳሉ።

መንግሥታዊ ለውጥ በመሠረታዊነት ችግሮችን ማስተካከል፣ ሙስናን ማስቀረትና የሕዝብ እርካታን መሠረት ያደረገ ሆኖ ሳለ፣ በኢትዮጵያ የሆነው በተቃራኒው ነው። ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረው የለውጥ ሙከራ፣ ችግሮችን ማስተካከል ካለመቻሉ በላይ ችግሮች የተባባሱበት ሆኗል ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

“ኢትዮጵያ በዐቢይ አስተዳደር የገጠማት ችግር፣ የመንግሥት ለውጥ አካሄድ መስመሩን ሲስት የሚያጋጥም ችግር ነው” የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ ከለውጥ በኋላ ሥርዓት አልበኝነት ተፈጥሯል ባይ ናቸው። መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ ካልተወጣ በሕዝብ ዘንድ የሚኖረው ተቀባይነት እየተሸረሸረ እንደሚሄድ እኚህ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ይገልጻሉ።

መንግሥት በሕግ የተሰጠውን የሕግ ማስከበር ኃላፊነት በትክክል ማስከበር ካልቻለ፣ ከሕዝብ ጋር ካልተግባባ እና የአገርንና ዜጎችን ሰላም ማስጠበቅ ካልቻለ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር ለማውጣት ይቸገራልም ብለዋል። የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ የተሳነው ወይም ያልፈለገ መንግሥት ስለ ለውጥና ብልጽግና ቢያወራ፣ የመኖር ዋስትና ለሌለው ሕዝብ ትርጉም የለውም የሚሉት መምህሩ፣ መንግሥት የሕዝብ ብሶት ገንፍሎ ሳይወጣ የመንግሥትነት ሚናውን በግልጽ መወጣት እንዳለበት ይመክራሉ።

ሞትን እንደ ዋዛ መለማመድ
ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ የሚጠራው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር፣ በኢትዮጵያ ታፍነው የነበሩ ድምጾችና ብሶቶች በፈነዱበት ወቅት መምጣቱን ተከትሎ፣ ቸግሮችን ይፈታል በሚል ተስፋ በወቅቱ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ብዙም ሳይቆይ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የለውጥ ውጥን፣ ቀድመው የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎ ከታሰበው በተቃራኒ ሆኗል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት በተለይ ኦሮሚያ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እንዲሁም በሌሎች ክልሎች አልፎ አልፎ በሚከሰት የጸጥታ ችግር በርካታ ዜጎች መሞታቸውን ኢሰመጉና ኢሰሞኮ በሚያወጧቸው መግለጫዎች ሲገልጹ ነበር። በየጊዜው በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተባባሱ ቢመጡም፣ የዜጎችን ሞትና ማፈናቀል የሚያስቆም አካል አልተገኘም። በዚህም በየጊዜው የሰዎችን ሞት መስማት እንደ ተራ ነገር የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ከሥነ ልቦና ባለሙያዎች እስከ ሰብዓዊ መብት ተቋማትና ተሟጋቾች ሲገልጹ ነበር።

በተለያዩ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎች ሲገደሉ፣ መንግሥት ዜጎችን ከታጣቂ ኃይሎች ጥቃት የመጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣና የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት እንዲያስጠብቅ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ነበር። ይሁን እንጂ መንግሥት እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የዜጎችን ደኅንነትና የአገርን ሰላም ማስጠበቅ ባለመቻሉ “የሰዎች ሞት ተለማምደናል” የሚሉ ሐሳቦች በስፋት ጅምላ ግድያዎች በተፈጸሙ ቁጥር ይሰማሉ።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በ2013 በጉምዝ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ንጹሐን ዜጎች ሲገደሉ፣ ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ብዙዎች ሞትን መለማመድና የሰዎችን ሞት እንደ ዋዛ በቁጥር ማለፍ የከፋ አዙሪት ውስጥ ይከታል ብለው አሳስበዋል። ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ በወቅቱ “ሞትን በፍጹም መለማመድ የለብንም” ሲሉም መልዕከት አስተላልፈው ነበር። በየጊዜው የሚከሰት የዜጎች ሞት አዙሪት ውስጥ የሚከት መሆኑን በመግለጽ፣ የዜጎች ሞት እንዲቆም “በአደራ ጭምር” ጠይቀው ነበር።

ከሰሞኑ በወለጋ በተፈጸመው ጅምላ ግድያ ፕሬዝደንቷ በመተከል በተፈጸመው ጥቃት ላይ ያነሱት ሞትን መለማመድ ደግመው አንስተውታል። “ሞትን ከተለማመድነው ከግድያ በኋላ ከማውገዝና የሃዘን መግለጫ ከማውጣት አዙሪት አናልፍም። ከዚያ በላይ መሄድ ይኖርብናል” ሲሉ ፕሬዝደንቷ የሞት መለማመድን አሳሳቢነት አንስተዋል።

ፕሬዝደንቷ ስለ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ሁኔታና በወለጋ ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በበርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ ስለተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ማነጋገራቸውን ገልጸዋል። “ድርጊቱን በጽኑ አወግዛለሁ” ያሉት ፕሬዝደንቷ በየትም ቦታ የዜጎች ሕይወት ውድነቱና ክብሩ መሸርሸር የለበትም ብለዋል።

ይሁን እንጂ የዜጎች ሞት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ አሁንም መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቅ ከተለያየ አቅጣጫ ጥሪ እየቀረበለት ነው። መንግሥት በዜጎች ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ “የሕግ ማስከበር ሥራ” እየሠራሁ ነው ቢልም፣ የዜጎችን ሞትን ግን ማስቆም አልቻለም።
ይልቁንም መንግሥት “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ጀመርኩ ካለበት ጊዜ ወዲህ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት በየአካባቢው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው “ሸኔ” ከኦሮሚያ ክልል አልፎ በቤኒሻንጉል ጉምዝና በጋምቤላ ክልል ጥቃት መክፈቱ የቅርብ ትውስታ ነው። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ሸኔ) ሰኔ 7/2014 በጋምቤላ ክልል ከጠዋት እስከ ምሽት የቀጠለ ጥቃት እና የጸጥታ እና የደኅንነት ችግርን ተከትሎ ለአንድ ቀን የከተማዋ የመንግሥት አገልግሎቶች፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች እና ሌሎችም አገልግሎቶች ተቋርጠው መዋላቸው ይታወሳል።

ጥቃቱ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች የተከፈተ ነበር። በጥቃቱ እስከ አሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሲቪል ሰዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የታጠቁ ኃይሎች የአንድ ክልል ዋና ከተማ እስከሚቆጣጠሩ ድረስ “መንግሥት የት ነበር” የሚል ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ተነስቶ ነበር።

የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በየጊዜው “ሸኔ” ላይ የተቀናጀ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን በየጊዜው ቢገልጹም፣ የቡድኑን ጥቃት ማስቆም አልቻሉም።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚያዝያ 21/2014 በኦሮሚያ ክልል ስላለው የሰላም ሁኔታ ባወጣው መግለጫ፣ “በኦሮሚያ ክልል በተወሰኑ ዞኖች በሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎችና በውሱን አጎራባች ክልሎች በመንቀሳቀስ የንብረት ውድመት፤ ዝርፊያ፤ ግድያና መፈናቀል በዜጎቻችን ላይ በመፈጸም ላይ የሚገኘውን አሸባሪው ሸኔ ለማጽዳት የሚደረገው ኦፕሬሽን ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለያዩ አካባቢዎች በተደረገው ኦፕሬሽን በርካታ የሸኔ ታጣቂዎችና አመራሮቻቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል። የስንቅ ማዘጋጃና የሥልጠና ማዕከሎች ሆነው የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችና ካምፖች ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል። በርካታ የታጣቂ ቡድኑ ትጥቆችና ተተኳሾች ተማርከዋል” ብሎ ነበር።

መንግሥት የሸኔን “ቁሳቁሶችና ካምፖች ከጥቅም ውጭ” እንዲሆኑ አድርጌያለሁ ቢልም፣ ከመንግሥት ኦፕሬሽን በኋላም በኦሮሚያ ክልል ንጹሐን ዜጎች በጅምላ መገደላቸው አልቆመም።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች