ኹለተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ከሰኔ 23 እስከ ሰኔ 25 ድረስ ይከበራል

0
1244

ማክሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኹለተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት “ንቁ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም ለዲሞክራሲና ለልማት” በሚል መሪ ቃል ከሰኔ 23 እስከ ሰኔ 25/2024 ድረስ በሂልተን ሆቴል ይከበራል።

ሳምንቱን በማስመልከትም የኹነቱ አዘጋጆች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን መስሪያ ቤት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የጋራ መግለጫ በዛሬው ዕለት ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ ሳምንቱ በዘርፉ ያሉ ድርጅቶች በማህበረሰቡ ውስጥ በሚያደርጓቸው እቅስቃሴዎች ያላቸውን ሚና ለህዝብ እና ለባለ ድርሻ አካላት የሚያስተዋውቁበትን ዕድል ለመፍጠር ታስቦ መዘጋጀቱ ተናግረል።

የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ፤ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ ጋር የጀመሩትን መልካም ግንኙነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በተጨማሪም “መብትና ግዴታውን በውል የተረዳ፣ በውይይት እና በምክንያታዊነት የሚያምን፣ የነቃና በነጻነት የተደራጀ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተጀመሩ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት
ግንባታ ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል” ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሰላም ግንባታ፤ እንዲሁም መጪው የብሔራዊ ምክክር ሂደት አካታችና ግልፅኝነትን የተላበሰ እንዲሆን በቅርበት ማገዝ እንዳለባቸው እንደሚታመንም ተናግረዋል፡፡

“የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንትን ማክበር አንድም የዘርፉን የገጽታ ግንባታ እንቅስቃሴን የበለጠ ለማጉላት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር ይረዳል” ያሉት ደግሞ፤ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ ናቸው።

ሄኖክ አክለውም፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ክብረ በዓል ከመንግስት፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከብዙሃን መገናኛ ጋር ያላቸውን እና የሚኖራችውን ግንኙነት ከምንጊዜውም በበለጠ ያጎለብታል ተብሎ እንደሚታመንም ተናግረዋል።

ከዚህም በላይ በጋራ ሳምንቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰላም፣ በልማት በዲሞክራሲ፣ በመልካም አስተዳደር ግንባታ፣ በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታና በሌሎች መስኮች የሚያደርጉትን ድጋፍና ጥረት ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት እንደሚሆንም ዋና ዳይሬተሩ አስረድተዋል፡፡

ከሰኔ 23 እስከ ሰኔ 25 2014 ድረስ በሚከበረው በዚህ ታላቅ ዝግጅት ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚያስተዋውቁ የፓናል ውይይቶች፣ ኤግዚቢሽን፣ የመገናኛ ብዙሀን መርሃ ግብሮች እና ሌሎች የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱም ተገልጿል፡፡

በዚህ በኹለተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ላይም ከ100 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንደሚሳተፋበት ይጠበቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here