በኮንትሮባንድ የሚገቡ ተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚዘውሩት የስልክ ገበያ

0
1418

በኢትዮ ቴሌኮም በ2018 ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ከ40 ሚሊዮን በላይ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ያሉ ሲሆን አሁን ባለውም የተንቀሳቃሽ ስልኮች የመዳረስ መጠን የፍላጎት አቅሙ በዓመት ከ10 ሚሊዮን በላይ እንደሚያድግ ይገመታል። ከዚህም ውስጥ ከ98 በመቶ በላይ የሚሆነው ዓመታዊ ፍላጎት እየተሟላ ያለው በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ነው።

በአሁኑ ወቅትም ከአጠቃላይ ዓመታዊ የአገሪቱ ሞባይል ስልክ ፍላጎት 98 በመቶ በላይ የሚሆነው በሕገወጥ መንገድ በኮንትሮባንድ ወደ አገር ወስጥ በሚገቡ ስልኮች እንደሚሸፈን ተገልጿል።

ያለውን ሰፊ ፍላጎት ለሟሟላት እና በቀጣይ ጊዜያት በአገሪቱ የሚፈጠረውን ሰፊ ገበያ በመመልከት በርካታ የውጪ እና የአገር ውስጥ ድርጅቶች ሞባይሎችን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም በዘርፉ ቢሰማሩም የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የኮንትሮባንድ ንግድ ፈተና ሆነውባቸው ህልወናቸውን እየተፈታተኑት እንደሚገኙ ተገልጿል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ ሞባይል ገጣጣሚዎች ማኅበር ባጠናው ጥናት መሰረት ከኹለት ዓመታት በፊት 65 ከመቶ የነበረው በኮንትሮባንድ የሚገቡ ስልኮች በገበያ ውስጥ ያላቸው ሽፋን መጠን አሁን ከ98 በመቶ በላይ ደረሶ እንደሚገኝ በሕጋዊ መንገድ አገር ውስጥ የተገጣጠሙ እና ወደ አገር ውስጥ የገቡ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ድርሻ ከ2 በመቶ እንደማይበልጥ ያሳያል። ይህንንም ተከትሎ በአገር ውስጥ የሚገኙ ሞባይል ገጣጣሚዎች በተስፋ መቁረጥ ውስጥ በመሆናቸው ሠራተኞችን ለመቀነስ መገደዳቸውን ከዚህም ባለፈ እራሳቸውም በኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ እየተሳተፉ እንደሚገኙ የማኅበሩ ፕሬዘደንት አማረ ተፈራ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

የሕገወጥ ሞባይል ስልክ ዝውውርን እና ገበያን ለመግታት መንግሥት የብሔራዊ መሣሪያዎች መለያ እና መመዝገቢያ ዘዴ (National Equipment Identity Registration System, NEIRS) ከኹለት ዓመታት በፊት ወደ ሥራ በማስገባት ስልኮችን በማይመሳሰል መለያ ቁጥር (IMEI) ለመመዝገብ የሚያስችል ዘዴን ተግባራዊ አድረጎ የነበረ ሲሆን በወቅቱ 2.7 ሚሊዮን ሕገወጥ የመለያ ቁጥር የነበራቸውን ተንቀሳቃሽ ስልኮች ለመያዝ አስችሎ ነበር በዚህ ሳቢያ የሕጋዊ አስማጪዎች እና ገጣጣሚዎች የገበያ ድርሻ ከ90 በመቶ በላይ በመድረሱ እንዲበረታቱ ምክንያት ሆኖ የነበረ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቋረጡ መልሶ አደጋ ላይ ጥሎናል ሲሉ አማረ ተፈራ (ዶ/ር) ይገልፃሉ።

የምዝገባውን መቅረት ተከትሎ 10 የነበርነው አገር ውስጥ የተናቀሳቀሽ ስልክ ገጣጣሚዎች ወደ 35 ቁጥራችን ከፍ ብሏል ያሉት አማረ ተፈራ (ዶ/ር) በወቅቱ ኢትዮ ቴሌኮም ምዝገባው ለምን ቀረ የሚል ጥያቄን ብናነሳም ከቴሌኮሙ በራሳችን መንገድ እንፈታዋለን የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል ብለዋል።
የቴክኖ ሞባይል ሕግ ክፍል ኀላፊ ገነነ አዘነ በበኩላቸው ድርጅቱ በኮንተሮባንድ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ስልኮች ከፍተኛ ጫና እየረሰበት እንደሆን የገለፁ ሲሆን በኢትዮ ቴሌኮም ተጀምሮ የነበረው የመለያ ቁጥር መለያ ምዝገባ በኮንትሮባንድ የሚገቡ ስልኮችን ለመቆጣተር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ነበረው ብለዋል። በመሆኑም የኮንትሮባንድ ንግድ ቀንሶ የሕጋዊ አምራቾች እና አስመጪዎች በጥሩ መነቃቃት ላይ ነበርን ያሉ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቋረጡ ኮንትሮባንድ ንግዱ መልሶ እንዲስፋፋ አድርጎታል ብለዋል።

በኮንትሮ ባንድ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ስልኮች ግብር የማይከፍሉ፤ እሴት የማይጨምሩ እና ሠራተኛ የማይቀጥሩ በመሆናቸው በዝቅተኛ ዋጋ ለገበያ እንደሚቀርቡ፤ ኅብረተሰቡም ዋጋ ቅናሹን በመመልከት ወደ ኮንተሮባንድ ስልኮች እንደሚኼድ ገነነ አዘነ ተናግረዋል። በተጨማሪም የቴክኖ ሞባይልን ሥም በመጠቀም እና በማመሳሰል የሚመረቱ እና በኮንትሮባንድ የሚገቡ ስልኮች በኩባንያው ገበያ ድርሻ እና ከጥራት ጋር ለሚነሱ ጥያቄዎች በድርጅቱ ሥም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው ብልዋል።

አክለውም አሁን ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድ ወረራ እንኳን በአነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ገጣጣሚዎች ቀርቶ እንደ እኛ ያሉ ዓለም ዐቀፍ ኩባንያዎች ሊቋቋሙት አይችሉም ያሉ ሲሆን መንግሥት ተጀምሮ የነበረውን የመለያ ቁጥር ምዝገባ መጀመር እና ዘርፉን በትኩረት ሊመለከተው እና ድጋፍ ሊያድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።

የብሔራዊ መሣሪያዎች መለያ እና መመዝገቢያ ዘዴ ከኹለት ዓመታት በፊት ወደ ሥራ በማስገባት ስልኮችን በማይመሳሰል መለያ ቁጥር የመዝገብ ሒደት መቋረጥን አስመልክቶ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ ጨረር አክሊሉ ጥያቄ ብናቀርብም በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የብረታብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዘረፉ ለተሰማሩ እና በኢንስቲትዩቱ የሚታወቁ 11 የተንቀሳቃሽ ስልክ አምራቾች እንዳሉ ይገልፃል። ከእነዚህም ውስጥ ኹለቱ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እና መሰል ችግሮች ከዘርፉ መውጣታቸውን በሥራ ላይ ላሉት ግን ጥሬ ዕቃዎችን ከውጪ ሲያስገቡ የሚጨምሩትን ዕሴት በመመልከት ኹለተኛ መደብ ግብር ከፋይነት ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ፤ የዕውቀት ሽግግር እንዲያደርጉና ከውጪ ባለሙያዎች ቅጥር እና በምርት ወቅት ለሚፈጠር ብክነት ግብር ቅነሳ እንዲገኙ የማድረግ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የኢንስቲትዩቱ የዕቅድ ኀላፊ ጥላሁን አባይ ይገልፃሉ።

ሆኖም አንዳንድ አምራቾች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጪ አምጥተው ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ አመራቾች ነን፤ ኹለተኛ መደብ የግብር ቅናሳ እና ሌሎች ማበረታቻችን ይገቡናል በሚል ያለ አግባብ ጥቅም ለማግኘት በመጠየቃቸው ገንዘብ ሚኒስቴር ከወራት በፊት እነዚህን ማበረታቻዎች እና ኹለተኛ መደብ የግብር ከፋይነት ጥቅምን ማገዱ ለአገር ውስጥ አምራቾች ከፍተኛ ችግር ሆኖባቸዋል።

ከጉምሩክ ኮሚሽን የተገኝ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው በጀት ዓመት ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ተንቀሳቃሽ ስልኮች በኮንትሮባንድ ሲነቀሳቀሱ መያዙን የሚገለፅ ቢሆንም ይህ ቁጥር በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ከገቡት ተንቀሳቃሽ ስልኮች መካከል 10 በመቶ የሚሆነውን ብቻ የሚሸፍን ነው።

የገቢዎች ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ኀላፊ ኡሚ አባጀማል ኮንትሮባንድ እንደ አገር በብዙ ቦታዎች ተንሰራፈቶ ይገኛል። ከፍተኛ ችግርም እያመጣ ነው ከተንቀሳቃሽ ስልኮች በላይ በሰዎች ሕይወት ላይ አደጋን የሚፈጥሩ የጦር መሳሪያዎች እና መጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኀኒቶች ሳይቀሩ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ ገልፀዋል።

በሚኒስቴሩ ተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚገቡባቸውን ቦታዎች የመለየት ሥራ ተከናውኖ የሞያሌ፤ ጅጅጋ እንዲሁም ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ በዋነኝነት ከፍተኛ የሕገወጥ ተንቀሳቃሽ ሽልኮች ዝውውር ያሉባቸው ስፍራዎች መሆናቸው በመለየቱ ግብረ ኀይል በማቋቋም ጥብቅ ክትትል በመከናወን ላይ ነው ብለዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ሕገወጥ ነጋዴዎችን የበለጠ ጠንካረ እንዲሆኑ እያደረገ ሲሆን በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩ ነጋዴዎች ባለተገባ ንግድ ፉክክር ተሰላችተው ወደ ሕገወጥ የንግድ ዝውውር እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here