ሰሞነ ኢሬቻ

0
894

የክረምቱ የጨለማው ጊዜ አብቅቷል፤ ወደ ብርሃናማው ወራት ተሸጋግረናል ይህም የሆነው ደግሞ ‹‹ዋቃ›› በአንተ ነው እና ምስጋና ይገባሃል የሚባልበት በዓል ነው ኢሬቻ። በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ አዲሱ ዓመት በጀመረበት በመጀመሪያው ወርሃ መስከረም ከመስቀል በዓል አንድ ሳምንትን ተሻግሮ የሚከበር በዓልም ነው። ታዲያ በዚህ ክብረ በዓል ላይ ከአራቱም የዓለም መዕዘናት ወደ ሐይቆች እና ከተማ ቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ ሐይቅ ሰው ይተማል። ያኔ ከተማዋ ቢሾፍቱም ከአቅሟ በላይ ሰዎችን በማስተናገድ በቁንጣን ትሰቃያለች፣ ሸብ ረቡም ይደምቃል ዋቃም ይመሰገናል ሰላም ለኦሮሞ፣ ሰላም ለኢትዮጵያ፣ ሰላም ለሰው ልጅ ይለመናል፣ አገሩን ጥጋብ ቀዬውን ሰላም ያድርግልን ይባላል ኢሬቻ ይከበራል። ከክብረ በዓሉም በኋላ ዘንድሮ እንደተገናኘን ለከርሞ ደግሞ አይለያየን ተብሎ ሰው፣ ወዳጅ ዘመድ ይመራረቃል በዓሉም ይከወናል ሕይወት ትቀጥላለች።

ዘንድሮ ግን ኢሬቻ ለየት ያለ ይመስላል የበርካታ ሰዎችንም ቀልብ በመሳብ በዓሉ ከባሕላዊ/ሃይማኖታዊው ስርዓትነቱ ባሻገር ፖለቲካዊ አንደምታው በዝቶብናል ሲሉ ተደመጡ ሰዎች ማኅበራዊ ትስስር ገፆችን ሲደምቁ ሰንብተዋል። በተለይ ደግሞ ከሳምንት በፊት በመስቀል በዓል ዋዜማ የደመራ ቀን ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ተውበው እና አጊጠው ወደ መስቀል አደባባይ ሲያመሩ የነበሩ ሰዎች በፀጥታ አካላት እንዲያወልቁ የገደዱበት አጋጣሚ ነበር። በዚህ ብቻ ሳይበቃም ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ትጠቀምበት የበረው ኮኮብ አልባው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አርማ በየትኛውም ቦታ እንዳይታይ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ ተከትሎ ፀንቶ ነበር። ይህ ግን ዛሬ በአዲስ አበባ እና ነገ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ ሐይቅ በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም ሲሉ ትችታቸውን አለፍ ሲልም የፖለቲካውን ወገንተኛነት በስፋት እያነሱ ሞግተዋል፤ ተችተዋል።

በተለይ ደግሞ ከሳምንቱ መጀመሪያ ቀናት ላይ በመሃል ፒያሳ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ አደባባይ ላይ የኦሮሚያ ክልልን ሰንደቅ አላማ መስቀል ከጠብ አጫሪነት ተለይቶ እንደማይታይ ስለ አዲስ አበባ ይመለከተናል የሚሉ ቡድኖች ልዩ ልዩ አስተያየቶችን አሰምተዋል። ከዚሁ በተጨማሪም መንግሥት በሥራ መግቢያ ሰዓት ያውም በዋዜማው ቀን አብዛኞችቹን የአዲስ አበባ መንገዶች መዝጋት ግልፅ የሆነ አድሎአዊነት መሆኑንም እያነሱ ከፍተኛ ትችት እና ቅሬታቸውን አስተጋብተዋል።

በዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ላይ ታዲያ መንግሥት በሌሎች ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክብረ በዓላት ላይ ያሳየውን የጥብቅ ቁጥጥር እና ሰብኣዊ መብት ጥሰት የሚደርስ ቁጥጥሩን ይደግመዋል ብለው እንደማያምኑም የንግግራቸው መቋጫ ያደርጉታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here