ከኤ.ቲ.ኤም ማሽን ላይ ያገኘውን ገንዘብ ተመላሽ ያደረገው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባልደረባ ከባንኩ የዕውቅና የምስጋና ደብደቤ ተሰጠው

0
1772

ማክሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ከኤ.ቲ.ኤም ማሽን ላይ ያገኘውን ገንዘብ ለንግድ ባንክ ተመላሽ ያደረገው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሥራ ባልደረባ ለፈፀመው የአርዓያነት ተግባር ከባንኩ የዕውቅና የምስጋና ደብደቤ ተሰጥቶታል፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የኮንትሮ ባንድ ቀጥጥር ፖሊስ መምሪያ ሬጅመንት 14 የሥራ ባልደረባ የሆነው ሳጅን እስታሉ ተስፋዬ እሸቴ ሰኔ 11 ቀን 2014 ከቀኑ 1፡00 ሰዓት አካባቢ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ፤ አባይ ማዶ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ከኤ ቲ ኤም ማሽን የራሱን ገንዘብ ለማውጣት ያቀናል። ግን በቦታው ሲደርስ ያልጠበቀው ነገር ይገጥመዋል ከኤ ቲ ኤም ገንዘብ ማውጫው ላይ በርካታ ብሮች ይመለከታል ቀርቦ አንስቶ መቁጠሩን ይናገራል።

ይህ ገንዘብ በስህተት ሌላ የባንክ ተጠቃሚ አዞት በሲስተም ችግር ሳይወስድ ትቶት የሄደውን 4000 ብር መሆኑን ይገምታል። እናም የግል ጥቅሙ ሳያታልለው ወደ ቅርብ አለቃው በመሄድ ጉዳዩን ሪፖርት ካደረገ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ይዞ በመግባት ለቅርንጫፉ ኃላፊ የሆነውን በሙሉ አስረድቶ በታማኝነት ብሩን ተመላሽ ማድረጉን ገልጿል።

ገንዘቡን ከአባሉ የተቀበለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አባይ ማዶ ቅርንጫፍም የአባሉ ተግባር ለኹሉም ማህበረሰብ አርዓያነት ያለው መሆኑን በመጥቀስ የዕውቅና ምስጋና ደብደቤ በክብር መሰጠቱን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም አባሉ የፈፀመው ተግባር መንግስትንና ሕዝብ የጣለበትን አደራ በገባው ቃል መሰረት ጊዜያዊ ጥቅም ሳያታልለው አርዓያነት ያለው የሚያኮራ ተግባር መፈፀሙ ለሌሎችም አስተማሪ በመሆኑ ምስጋናውን አቅርቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here