“የተዋልደናል” ትርክት አሳሳችነት…

0
923

በፍቃዱ ኃይሉ የኢትዮጵያን አንድነት አስፈላጊነት ለማስረዳት በተለይ የፖለቲካ ልኂቃን “ተዋልደናል” የሚለውን ትርክት በማጠየቅ ለመላው ኢትዮጵያ ይሠራል ብሎ ማሰብ ችግር አለበት በማለት መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። በርግጥ እንደሚታሰበው “የዘር ጥራት” አለ ማለት እንዳልሆነ በመጥቀስ “የዘር ጥራት” የሚባለው አስተሳሰብ በራሱ ዘረኝነት
እንደሆነ የጠቆሙት በፍቃዱ፥ ኢትዮጵያውያን አንድ ለመሆን መፈቃቀድ በኀይል እርምጃ ከሚገኝ አንድ ዓይነትነት ወይም በመዋለድ ከሚገኝ ቤተ ዝምድና ይልቅ የጎላ ፋይዳ ያለው የአብሮነት ዋስትና ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ደምድመዋል።

የኢትዮጵያን አንድነነት አስፈላጊነት ለማስረዳት ጥቂት የማይባሉ ዜጎች “ተዋልደናል” የሚል ማስረጃ ያቀርባሉ። በጣም ያስደነገጠኝ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ይህንኑ መከራከሪያ ሲጠቀሙ መስማቴ ነው። “ተዋልደናል” የሚለው ክርክር፥ አንድም ስህተት ነው፣ አንድም ደግሞ “ባንዋለድ ኖሮ አንድ አገረ መንግሥት ውስጥ አብረን መኖር አያስፈልገንም፤ በልዩነት መቧደናችንም አግባብ ነው” ማለት ይመስላል። የመሟገቻዎቹ ጭብጦች ኹለት የተሳሳቱ አረዳዶችን ያመለክታሉ።

1ኛ፣ የአገረ መንግሥታዊ አንድነት ፋይዳን የምንረዳበትን መንገድ እና
2ኛ፣ ብሔረ-ሰቦችን የምንረዳበትን መንገድ
አገረ መንግሥት እና ማኅበራዊ ውል
ስለ መንግሥታት እና አገረ መንግሥታት ባሕሪይ ከተጻፉ ኀቲቶች መካከል ማንኩር ኦልሰን ስለ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ሽፍቶች የጻፈው በጣም ይማርከኛል። ዘርፎ ሒያጅ ሽፍቶች (roving bandits) በየመንደሩ ያገኙትን ሁሉ ዘርፈው እልም ይላሉ። ቋሚ ሽፍቶች (stationary bandits) በቋሚነት አካባቢው ላይ ሰፍረው፣ ከአምራቹ እያስገበሩ፣ አጥረግርጎ ዘርፎ ከሚሔደው ተንቀሳቃሽ ሽፍታ አካባቢውን እየተከላከሉ የኀይል የበላይነታቸውን (monopoly of violence) አስጠብቀው የሚኖሩ ሽፍቶች ናቸው። ሠርቶ አደር፣ አርሶ አደር፣ አብርቶ አደር ነዋሪዎች ቋሚ ሽፍቶችን ይመርጣሉ፤ ምክንያቱም ሁሉም ምርታቸው አይወሰድባቸውም፣ ከዘርፎ ሒያጅ ሽፍቶችም ተከላካይ አለላቸው። እንደዚህ ዓይነቶቹ ቋሚ ሽፍቶች ናቸው ቀስ በቀስ ወደ መንግሥትነት ያደጉት።

የቋሚ ሽፍቶች (በዘመናዊ አጠራራቸው መንግሥታት) የሽፍትነታቸው ደረጃ በሕዝቦች ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ፣ እየቀነሰ መጥቷል። የኀይል የበላይነታቸውም ለሕዝብ ወገንተኛ በሆነ ሠራዊት እንዲተካ ጥረት እየተደረገ ነው። የሽፍቶቹ መሪዎችም በሕዝብ የሚሾሙበትና የሚሻሩበት ስርዓት እየተዘረጋ ነው። በተለያዩ ቋሚ ሽፍቶች መካከል መከባበርም አለ፤ ሉዓላዊነት ይባላል። ቋሚ ሽፍቶች እንዳቅማቸው የሚወሰን የተፅዕኖ አድማስ ነበራቸው፤ አሁን ያ የተፅዕኖ አድማስ በዓለም ዐቀፍ ማኅበራት ዘንድ ዕውቅና ያለው ድንበር ይባላል። ይህንን በድንበር የሚታወቅ ግዛት፣ ነዋሪውን ሕዝብ፣ አስተዳዳሪውን ‘መንግሥት’ የሚባል ቡድን እና ዓለማቀፋዊ ክብርና ዕውቅና ያለውን ስብስብ አገረ መንግሥት (state) እንለዋለን።

በአገረ መንግሥት እና በነዋሪዎቹ መካከል ያልተጻፈም የተጻፈም ሥምምነት አለ፤ ‘ማኅበራዊ ውል’ በመባል ይታወቃል። ነዋሪዎቹ (በዘመናዊ አጠራራቸው ዜጎች ይባላሉ) ከመብታቸው እና ከምርታቸው ላይ እየሸረፈ የመውሰድ መብት ለመንግሥታቸው ይሰጡና በምላሹ ቀሪ መብቶቻቸውን እንዲያስከብርላቸው እና ቀሪ ንብረታቸውን እንዲጠብቅላቸው ግዴታ ይጥሉበታል። ምናባዊው የሕዝብና የመንግሥት ግንኙነት የሚመሠረተው ሁለቱም ይህንን ማኅበራዊ ውል አክብረው ሲንቀሳቀሱ ነው። አለበለዚያ ስርዓት አልበኝነት (anarchy) ሊሰፍን ይችላል።

የአገረ መንግሥታት እና ብሔረመንግሥታት አመሠራረት
በአንድ አገረ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የአገር ፍቅር ያዳብራሉ፣ (አንቶኒ ስሚዝ ‘ethnosymbolism’ከሚሉት) የመገለጫ ትዕምርቶቹ ጋርም ስሜታዊ ቁርኝት ያዳብራሉ። በዚህም ታማኝነታቸው ከየትኛውም ሌላ ስብስብ የበለጠ፣ ወይም በአገረ መንግሥታቸው ውስጥ ካለየትኛውም ነጠላ ቡድን ወይም ግለሰብ የበለጠ፣ ባስ ሲልም ደግሞ ከራሳቸው የግል ጥቅምም የበለጠ ለአገረ መንግሥቱ ሊሆን ይችላል። ይህንን ስሜታዊ ቁርኝት እና ለአገረ መንግሥቱ ሕልውና ማድላት “ብሔርተኝነት” ወይም “አርበኝነት” ልንለው እንችላለን። ብሔርተኝነት ቢያንስ ብዙ አጥኚዎች እንደሚሥማሙበት አውሮፓ ውስጥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ገደማ የተጀመረ የዘመናዊ አገረ መንግሥታት መፈጠር (state formation) መጀመሪያ ሆኗል። ብዙዎቹ አውሮፓውያኖች አገረ መንግሥቶቻቸውን ከገነቡ በኋላ ማኅበረሰቦቹን በማዋሐድ፣ በተለይ በቋንቋ እና በባሕል ረገድ አንድ ብሔር አድርገዋቸዋል፤ ይህ ደግሞ ብሔር ግንባታ (nation building) ይባላል።

የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ከተፈጠረ በኋላ ብሔር ግንባታ [በበቂ] ሁኔታ አልተሠራም፤ ስለሆነም የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት በርካታ ብሔሮችን ያቀፈ ሆኗል። ነገር ግን በዚህ ድምዳሜ ላይ ሁሉም ሰዎች አይሥማሙበትም።

አንቶኒ ስሚዝ በብሔርተኝነት እና ዘውግ (ethnicity) ጉዳይ በርካታ መጽሐፍትን ያበረከቱ ዕውቅ ምሁር ናቸው። ስሚዝ ብሔራዊ ማንነትን በአምስት አላባውያን ሊገልጹት ይሞክራሉ። እነዚህም ፩) የጋራ ግዛት ወይም ቀዬ ያላቸው፣ ፪) የጋራ ትርክት እና ታሪካዊ ትውስታ ያላቸው፣ ፫) የጋራ ሕዝባዊ ባሕል ያላቸው፣ ፬) የጋራ ሕጋዊ መብቶች እና ግዴታዎች ያሏቸው፣ እና ፭) የጋራ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስሮሽ ያላቸው ቡድኖች አንድ ብሔር ናቸው።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብሔር ልትባል የምትችለው ኢትዮጵያ ብቻ ናት፤ ሌሎቹ በሙሉ ጎሳዎች ናቸው የሚሉ በአንድ ወገን “የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን” ሲያቀነቅኑ፥ በሌላ ወገን ደግሞ ኢትዮጵያ ራሳቸውን የቻሉ በርካታ ብሔሮች ስብስብ ነች የሚሉ “የዘውግ ብሔርተኝነትን” ያራምዳሉ። ከላይ በተጠቀሰው የስሚዝ አላባውያን መሠረት ሁለቱም ቡድኖች አሳማኝ ዝርዝር አምጥተው መከራከር ይችላሉ፤ ይሁንና በተለይም ከሃይማኖት ጋር ተጣብቆ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ‘ሴኩላር’ የሆነ “የጋራ አመጣጥ ተረክ” (የንግሥተ ሳባ ተረክ ላይ የተመሠረተ ነበር) እና “የጋራ ባሕል” ማሳየት ባለመቻሉ እንዲሁም አባል የሆኑት የዘውግ ቡድኖች ለዘውግ ብሔርተኝነት ልባቸው በማድላቱ እየተሸነፈ ይመስላል።

[የዘውግ ብሔርተኞች የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን ተረኮች አፍርሰው፣ በምትካቸው የዘውግ ብሔርተኝነት ትርክቶችን ተክለዋል።] ስለዚህ የኢትዮጵያን አንድነት ፈላጊዎች ብሔርተኝነትን በብሔርተኝነት ለማጣፋት መሞከሩን ትተው የተሻለ የሚያስተሳስር አማራጭ በመፈለግ ፈንታ (ብዙ አማራጭ መንገድ አለ)፥ “ያልተዋለደ የለም” በሚል የጋራ አመጣጥን የሚያመላክት በመሠረቱ ብሔርተኛ የሆነ መከራከሪያ ማሰማት ጀምረዋል። ጥያቄው “ይህ መከራከሪያ የት ያደርሳል?” የሚለው ነው።

በርግጥ “ተዋልደናል”?
80 በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ሕዝቦች በገጠር ኗሪ ናቸው። በገጠር እና በከተማ ካሉ የአኗኗር ዘዬዎች መካከል የጎላው ልዩነት በገጠር የሚኖሩ ብዙዎች በቋንቋ እና በሃይማኖት እንዲሁም በብዙ ዕሴቶች ከሚመስሏቸው ጋር የሚኖሩ መሆናቸው እና እንቅስቃሴያቸውም (‘mobility’) በጣም ውሱን መሆኑ ነው። እጅግ ብዙዎቹን የገጠር ነዋሪዎች ብትጠይቋቸው የእናታቸው እና የአባታቸው ብሔር “አንድ” እንደሆነ ይነግሯችኋል። ይኼንን “ተዋልደናል” የሚል የከተማ ትርክት (እና በከፊል የተጎራባች ብሔረ-ሰቦች ድንበር ላይ ያሉ ማኅበረሰቦች ጉዳይ) ለመላው ኢትዮጵያ ይሠራል ብሎ ማሰብ ችግሩ ይኸው ነው።

ይኼ ማለት ግን እንደሚታሰበው “የዘር ጥራት” አለ ማለት አይደለም። “የዘር ጥራት” የሚባለው አስተሳሰብ በራሱ ዘረኝነት እንደሆነ አሁን አሁን ብዙ ምሁራን እየተሥማሙበት ነው። ይህንን በሐሳዊ ሳይንስ ለማረጋገጥ መሞከር በራሱ ‘ሳይንሳዊ ዘረኝነት’ ይባላል። በተለይም የዲኤንኤ ምርመራ መስፋፋት የዓለም ሕዝቦች ምን ያህል እርስበርስ እንደተዳቀሉ የሚያረጋግጥ ክስተት ሆኗል። ሲጀመር ሁሉም ሰዎች “ሆሞ ሳፒየንስ” (‘የብልሕ ሰው ዘር’) ዝርያዎች ናቸው። እንደዩቫል ሃራሪ ገለጻ እንደውም “የብልሕ ሰው ዘር” የሚባለው የዘመናዊው ሰው ዝርያ (በ‘survival of the fittest’) አሸንፎ ከመውጣቱ በፊት ከነበሩት የመጨረሻ ተቀናቃኞቹ (ኒያንደርታሎች) በአንድ በኩል እየተጋደለ በሌላ በኩል መዳቀሉን የዛሬ ሰው ዲኤንኤ ምርመራ ይመሰክራል።

የሆነ ሆኖ ‘ሳይንሳዊ ዘረኞች’ ከትችት ባልተረፈው ምደባቸው የሰው ልጆችን ዘር ከሦስት እስከ አምስት ድረስ ይከፍሉታል። ከነዚያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ከብዙዎቹ አፍሪካውያን ጋር በአንድ የጥቁር ዘርነታችን ነው የምንታወቀው። ብዙዎቹ አፍሪካውያኖች በአውሮጳውያን ቅኝ ግዛት ላይ የተመሠረተ ድንበር ሲያገኙ እና አገረ መንግሥት ሲመሠርቱ፥ የእኛም ቀድሞ በንጉሣዊ ስርዓት የተሰባሰበው ማኅበር ድንበሩን ከቅኝ ተገዥ ጎረቤት አገሮች ጋር ተጋርቷል እንጂ ያው “ጥቁር አፍሪካውያን” ነን። በዚህ መሠረት ከሌሎች አህጉራት የሚመጡ ሰዎችን ዜጎች አድርገን መቀበል እስከምንጀምር ድረስ፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያኖች ዘራችን “ጥቁር” ነው። ሌሎቹ ስብስቦች በሙሉ በቋንቋ እና ባሕል ላይ የተመሠረቱ ልዩነቶች ናቸው። በርግጥ ነጮች ከአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያውያንን ‘ጥቁር ኮኬዥያንስ’ ናቸው ብለው ጽፈዋል። ነገር ግን ይህም እነርሱ ካላቸው ‘የበላይነት ስሜት’ በመነሳት በጥቁር አንሸነፍም የሚል ትርክት ለመፍጠር ያደረጉት ሐሳዊ ማስረጃ ነው (ላጲሶ ጌ. ዴሌቦ (ዶ/ር))።

የኢትዮጵያውያን የዘር ሐረግ (በዲኤንኤ)
ከበዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን የጠይምንበት ምክንያት ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ስለተቀየጥን ሊሆን ይችላል። ጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ የመግባቢያ ቋንቋዎች ግዕዝ፣ ግሪክ እና አረብኛ መሆናቸው ለእነዚህ ሕዝቦች በንግድም ይሁን በፍቅር ወይም በጦርነት መቀየጣችንን ፍንጭ ይሰጣል። ሳይንቲስቶች በዲኤንኤ የዘር ሐርግን ሲያጠኑ በሚጠቀሙበት መለያ የጋራ የዘር ምንጭ አላቸው የሚባሉትን በአንድ ‘ሃፕሎግሩፕ’ ውስጥ ያስቀምጧቸዋል። ብዙ ኢትዮጵያውያን ለምሳሌ ከግሪኮች ጋር አንድ ዓይነት ‘ሃፕሎግሩፕ’ እንዳላቸው በጥናት ታውቋል።
ሞጣ ዋሻ ውስጥ የዛሬ 4 ሺሕ 500 ዓመት ገደማ ኖሯል የተባለለት (በተለየ አጋጣሚ የዘረመል ቅንጣቱ ያልጠፋ) ሰው ዲኤንኤ ፍተሻ እንደሚያስረዳው በብልሕ ሰው ዝርያ ወደ መላው ዓለም መሰራጨት የተሻለ ተቀባይነት ያለው መላ ምት “ከአፍሪካ ወደ ውጪ” የሚባለው ነው። ሆኖም የብልሕ ሰው ዝርያ እንደወጣ አልቀረም። ለምሳሌ የሞጣ ዋሻ ውስጥ የተገኘው ቅሪት ዲኤንኤ እንዳመላከተው እና ተከታታይ ሌሎች ጥናቶች እንዳጠናከሩት የዩሮዢያ (ዩሮፕ እና እስያ) ወደ አፍሪካ ቀንድ ተመልሶ መጥቶ እንደነበር ያሳያል። በወቅቱ ከዩሬዢያ የመጡት ሰዎች የአፍሪካ ቀንድ ሕዝብን ሩብ የሚያክሉ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ ሱማሌ እና ጅቡቲ ሰዎች ዲኤንኤ ውስጥ 30 በመቶ አሻራቸውን ጥለዋል። ስለሆነም እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችም በወል ትውስታ የተዘነጋ ቅይጥ የዘር ሐረግ አላቸው ማለት ይቻላል።

ይህንን የሚያጠናክሩ ሌሎችም የዲኤንኤ ምስክርነቶች አሉ። የዲኤንኤ ምሥሥሎሾችን በክላስተር ለይቶ የሚያስቀምጥ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየው “62 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን አይሁዶች፣ ኖርዌዮች እና አርመኖች ያሉበት የመጀመሪያው ክላስተር ውስጥ” እንደሚገኙ ያሳያል። ጥናቱ እንደጠቆመው ብዙዎቹ አፍሪካኖች የሚገኙበት ክላስተር ውስጥ ካሉት ባንቱዎች እና አፍሮ-ካሪቢያኖች ምድብ የሚገቡት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 24 በመቶ ብቻ ነው።

ስለ ብሔረሰቦች የምናስበው…
ስለ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች የምናስበው እንደ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወይም የባሕል ስብስቦች ሳይሆን በሐር ሐረግ የሚወረሱ እንደሆነ “የተዋልደናል” ትርክት ያሳያል። ይህ ምን ያህል ሥር የሰደደ ነው የሚለውን ለመቃኘት እንዲመቸኝ ፌስቡክ ላይ መጠይቅ አቅርቤ ነበር። የፌስቡክ ገጼን ከሚከታተሉ 761 የመጠይቁ መላሾች ውስጥ ማንነት “ብሔራዊ ማንነት” (ማለትም ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ሶማሌነት፣ ወዘተ.) በዘር ሐረግ ነው የሚወረሰው ብለው የሚያምኑት 36 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው፤ በባሕል ነው የሚወረሰው (ወይም ባሕሉ ውስጥ በማደግ ነው የሚገኘው) ብለው የሚያምኑት ደግሞ 64 በመቶዎቹ ናቸው። ይህ ግን መላውን ሕዝብ ይገልጻል ብሎ ማሰብ በጣም የተሳሳተ ይሆናል። ብዙዎቹ የፌስቡክ ተጠቋሚዎች የተሻለ መረጃ እና ‘ኤክስፖዠር’ ያላቸው በመሆናቸው ማንነት በባሕል እንደሚገኝ የግል ተሞክሮ ያላቸው ስለሚሆኑ፥ ይህን ዕድል ካላገኙ ብዙኀን ኢትዮጵያውያን የተለየ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል።

አገራዊ አንድነት…
በዚህ ርዕስ ‘What’s a nation?’ የሚል መጣጥፍ እ.ኤ.አ. በ1882 የጻፈው ፈረንሳዊው ኧርነስት ሬናን ነው። ሬናን በወቅቱ በአውሮፓ የፈነዳው ብሔርተኝነት እና የብሔርተኝነቱ ልክ አሁን እንደኛ አገር በጠራ የዘር ሐረግ ውዥንብር ላይ መመሥረቱ ነበር ለዚያ መጣጥፍ መወለድ ምክንያት የሆነው። እኔም ከዚያ መጣጥፍ ላይ አንድ ኹለት አንቀፆች ልጠቃቅስና ጽሑፌን ልደምድም።

“ሦስት ቋንቋ እና ኹለት ሃይማኖት ተከታይ ሕዝቦች ያሏት ስዊዘርላንድ አንድ አገር ስትሆን፣ አንድ ወጥ ሕዝብ ያላት ቱስካኒ እንዴት አገር መሆን አቃታት? የኦስትሪያ አገረ መንግሥት እንዴት ብሔረ መንግሥት መሆን ተሳነው? እንዴት ነው የብሔርነት/ዜግነት መርሕ ከዘር ሊለይ የቻለው? እነዚህን ነጥቦች ነው አንድ አሳቢ ሰው አዕምሮው አርፎ እንዲቀመጥ መልስ ሊያገኝለት የሚገባው።”

በተመሳሳይ፣ እኛም አገር እንዲህ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። “እንዴት ነው 80 ቋንቋዎች እና ብዙ ሃይማኖቶች ያሏት ኢትዮጵያ አንድ አገር ስትሆን፣ አንድ ቋንቋ እና ሃይማኖት ያላት ሶማሊያ አንድ መሆን ያልቻለችው?” አንድ አገር መሆን የሚያስፈልገው ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን እንዳሳዩን ተገንጥሎም ነጻነት እና ዴሞክራሲን ማግኘት እንደሚቻል እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል ነው። እንደ ሱማሌ አንድ ቋንቋ እና ሃይማኖት የሚከተል አገር (ብሔረ መንግሥት) መሆን ለብሔራዊ አንድነት ዋስትና ስለማይሆን ነው።

ሬናን ይቀጥላል፦ “ስለዘር ያወራነው፣ በቋንቋም ቢሆን ይሠራል። ቋንቋ ሰዎችን አንድ እንዲሆኑ ሊጋብዛቸው ይችላል፤ ነገር ግን አንድ እንዲሆኑ አያስገድዳቸውም። አሜሪካና እንግሊዝ፣ ደቡብ አሜሪካ እና ስፔይን አንድ ዓይነት ቋንቋ ይናገራሉ ነገር ግን አንድ አገር አልመሠረቱም። በተቃራኒው ግን ስዊዘርላንድ በተለያዩ ሦስት እና አራት ቋንቋ የሚናገሩ አባሎቿ ተመሥርታለች። በሰው ዘንድ ከቋንቋ በላይ የኾነ አንድ ነገር አለ፤ እሱም መፈቃቀድ ይባላል።”

የኢትዮጵያውያን አንድ ለመሆን መፈቃቀድ በኀይል እርምጃ ከሚገኝ አንድ ዓይነትነት ወይም በመዋለድ ከሚገኝ ቤተ ዝምድና ይልቅ የጎላ ፋይዳ ያለው የአብሮነት ዋስትና ነው።

በፍቃዱ ኃይሉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና ጸሐፊ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው befeqe@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here