“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ኢትዮጵያ የአንተም የአንቺም አይደለችም። ኢትዮጵያ የልጆቻችን እና የእነርሱ ልጆች ቅርስና ሀብት ናት። አገር ሁሌም እንደዛ ነው። ነዋሪው ትውልድ፣ ነፍስ አውቃለሁ ባዩ ትውልድ የአገር አገልጋይ፣ ባሪያ ወይም ሎሌ ነው። የሀገር ባለሀብትና ባለቤት ሕጻናት ልጆች ናቸው። አንድ ብሂል አለ አይደለ? ሀገር የቀደመ ትውልድ ያቆያት፣ ለመጪው የምንሰጣት አደራ ናት የሚል።
ይህ ያለንበትና ጉዳዩ የሚመለከተው የእኛ/የአንቺ/የአንተ/የእኔ ትውልድ አደራ እንደበላ ወይም እየበላ እንዳለ ይቆጠራል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት ልጆች ያለወላጅ ቀርተዋል፤ ብዙዎቹ ከኖሩበት ተፈናቅለዋል። ምን እየሆነ እንደሆነ አያውቁም።
የሰው ልጅ ግብሩ ምን እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችል ነፍስ የማወቅ እድሜ ላይ ሳይደርሱ፣ ሰው የተለየ ጠባይና ‹ባህሪ› እያሳየ ይገኛል። እናም ለእነዚህ ጨቅላዎች ሰው አቅፎ የሚስም፣ ጣፋጭ ገዝቶ የሚሰጥ ደግ አልያም ክፉ ሲሆን ሲያጠፉ ቆንጠጥ የሚያደርግ ወይ በጨፈቃ የሚጋረፍ ፍጡር አይደለም። ሰው አምሳያውን ሰው ከምድር ገጽ ለማጥፋት ስለት የሚያነሳ፣ የማይሳሳና ጥይት የሚተኩስ፣ ርህራሄ የሌለው፣ ደም ያሰከረው ፍጡር ነው።
አሁን ላይ ወላጆቻቸውን በግፍ በተነጠቁ፣ በጦርነት የተነሳ ከሚያውቁት አካባቢ ለቅቀው በየመጠለያው ባሉ ሕጻናት ዐይኖች ውስጥ ምን መስለን የምንታይ ይመስላችኋል? መቼም የሕጻናት ነፍስ ቂምን የምትይዝ አይደለችም እንጂ፣ ከሰው ይልቅ የሌሊት አውሬን የተሻለ ሳይፈሩ ሊቀርቡ የሚችሉ አይመስላችሁም?
በወለጋ ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ፣ እንክብካቤ የሚሹና አካላዊም ሆነ አእምሮአዊና ሥነልቦናዊ ጤናቸው በብዙ የታወከ ሕጻናት በብዛት አሉ። እነዚህ ልጆች ያድጋሉ። የሚያድጉት ግን ትርጉሙን ከሚፈልጉለት መከራና ካዩት አሰቃቂ ምስል ጋር ነው። መልሱን በምን መንገድ እንደሚፈልጉ አናውቅም፤ አይታወቅም።
በሚያሳዝን ሁኔታ፣ የሕጻናትን የነገ አገር ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ሕጻናቱንም እየበደልን፣ ጊዜና ሊኖሩ የሚችሉትን ሕይወት እየነጠቅናቸው ነው ያለነው።
‹‹ልጄን ሌሊቱን ሙሉ ከእቅፌ ሳላስወጣት ነው ያደርኩት። በአገራችን የሚፈጸመውን ግፍ ዐየሁ። ሕጻናት በጭካኔ ተገድለዋል፤ ብዙዎቹ ወላጆቻቸውን አጥተዋል። ልጄን ነጥቀው ለመከራ የሚዳርጉብኝ መስሎኝ እንደፈራሁ ነው ሌሊቱ የነጋው። ፈጣሪን አስቀድመኝ ብዬ ልጠይቀው ወይስ…? አይባልም እንጂ…ባልወለድኩ ያሰኛል።›› አለች አንድ እናት፤ መሀል አዲስ አበባ የምትኖር።
የእናቶችን የወላጆችን ሕመም ማሰብ ይከብዳል። ከምንም በላይ ግን አገር በጽኑ ታምማለች። ትድንበትን አዲስ ትውልድ እንኳ ጤነኛ አድርጋ ማቆየት ስለመቻሏ ያጠራጥራል። ፍትህ ነፍስ ስለማያውቁ፣ ሰላምና ፍቅር ብቻ ስለሚገባቸው የንጹህ ነፍስ ባለቤት ለሆኑ ሕጻናት። ኢትዮጵያ የእነርሱ ናት። እርሷን የተሻለች አድርገን ማቆየት ባንችል እንኳ ቢያንስ ሕጻናቱን ከክፉ እንጠብቃቸው። ፍትህ ለሕጻናት!
መቅደስ ቹቹ
ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014


