‹ቅጥረኛ ወታደሮች› የሚለው ቃል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት የምንሰማው ሆኗል። ነገር ግን አስቀድሞም የነበረና የታወቀ፣ በተለያዩ ድንጋጌዎችም የሕግ ማዕቀፍ የወጣለት ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያም ከዚህ አንጻር ካለችባት አኅጉር አፍሪካ ብሎም ከዓለም ድንጋጌዎች የተዋሰችና የራሷ ያደረገቻቸው አካሄዶች አሏት። ሽመላሽ ወንዳለ ይህን ነጥብ መነሻ አድርገው፣ ስለ ቅጥረኛ ወታደሮች ማንነት እንዲሁም በሕግ ያላቸውን መብት በሚመለከት ተከታዩን ሐሳብ አጋርተዋል።
ይህን አጭር ጽሑፍ ለመጻፍ ምክንያት የሆነኝ በአሁን ጊዜ እየተካሄደ ያለው የሩስያ እና የዩክሬን ጦርነት ሲሆን፤ በጦርነቱ ደጋግመው ከተሰሙ ጉዳዮች አንዱ ስለ ቅጥረኛ ወታደሮች ነው። ምናልባትም በቅርብ ጊዜ ከተካሄዱ ጦርነቶች የዚህን ጦርነት ያህል ስለ ቅጥረኛ ወታደሮች በሰፊው የተዘገበበት ጦርነት ላይኖር ይችላል። ይህ በመሆኑም ስለ ቅጥረኛ ወታደሮች ከመስማት ባለፈ ስለ ማንነታቸውና በሕግ ፊት ስላላቸው መብትና ግዴታ በአጭሩ በማንሳት ያለኝን ግንዛቤ ለአንባቢያን ለማጋራት ስለወደድኩ ነው።
ከተጀመረ ወራትን ባስቆጠረውና አሁንም እየተካሄደ ባለው የዩክሬንና ሩስያ ጦርነት፤ የቅጥረኛ ወታደሮች ተሳትፎ በሰፊው ስለመኖሩና ኹለቱም አገሮች ቅጥረኛ ወታደሮችን እየተጠቀሙ እንደሆነ በተለያዩ ምንጮች ይዘገባል። ጦርነቱ በተጀመረ ሰሞን ለሩስያ መንግሥት ለመዋጋት ከሶሪያ እና ከሌሎችም አገሮች ግለሰቦች እየተመዘገቡ ነው ሲባል ተሰምቷል። በዩክሬን በኩልም ከአፍሪካ ጨምሮ ከሌሎች አገራትም ወታደሮችን ፈልጋ ማስታወቂያ አውጥታ እንደነበር የሚገልጹ ዘገባዎች ወጥተዋል። እንዲሁም ጦርነቱ ከተጀመረ ከሳምንታት በኋላ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ የሩስያ ኤምባሲ በር ላይ በወታደርነት ለመመዝገብ ተሰልፈው ታይተዋል ሲባል ነበር።
ቀደም ሲል የነበሩ ልምዶችን ስንመለከት፤ አሜሪካ እ.አ.አ. ከ2003 ጀምሮ ተካሂዶ በነበረው በኢራቅ ጦርነት ቅጥረኛ ወታደሮችን በሰፊው የተጠቀመች ሲሆን፣ ሁኔታው ስለ ቅጥረኛ ወታደሮች መኖርና ሚና የተዘገበበትና ትኩረት ያገኘበት አጋጣሚም ሆኖ አልፏል። ምንም እንኳ በአሜሪካ ሥማቸውን በመቀየር የግል ወታደራዊ ተቋራጮች (Private Military Contractors) በማለት ቢጠቀሱም፣ ነገር ግን በጦርነቱ ውስጥ በነበራቸው ሚና ከቅጥረኛ ወታደሮች ጋር ተመሳሳይ ስለነበሩ በተለያዩ ዘገባዎች ቅጥረኛ ወታደሮች ተብለው ተጠቅሰዋል።
የቅጥረኛ ወታደሮችን ማንነት ስንመለከት፤ አብዛኛውን ጊዜ ቅጥረኛ ወታደር የሚሆኑት ቀድሞ ወታደር የነበሩ፤ በተለይም በተለያዩ አገራት በልዩ ኃይልና በሌሎችም ጠንካራ የሠራዊት ክፍል ውስጥ ያገለገሉና በተግባርም የተፈተነ ልምድ ያላቸው ናቸው። እንዲሁም በብቃታቸው ተመርጠው የሚመለመሉ ስለሆኑ በብዙ አጋጣሚዎች ከመደበኛ ወታደሮች የተሻሉ እንደሆኑና ተልእኮዎችን በመፈጸምም ጥሩ ብቃት እንዳላቸው ይነገራል።
በዚህ ምክንያትም አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች መንግሥታት በመደበኛ ሠራዊታቸው ማሳካት ያልቻሉትን ወይም ለማሳካት ረጅም ጊዜ የሚወስዱ ተልእኮዎችን በቅጥረኛ ወታደሮች ማስፈጸም እየተለደ ነው። ለምሳሌ ያህል፤ የናይጄሪያ መንግሥት ቦኮ ሀራም ከተባለው አሸባሪ ቡድን ጋር በሚያደርገው ጦርነት በመደበኛ ሠራዊት መወጣት ያልቻላቸውን ተልእኮዎች ለማሳካት ቅጥረኛ ወታደሮችን እንደሚጠቀም የሚገልጹ ዘገባዎች ወጥተው ያውቃሉ። እንደ የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች እና ኳታርን የመሳሰሉ ትንንሽ ባለጸጋ አገራትም ከበድ ላለና ለውጪ አገር ተልዕኮ የሚሆን ብቁ መደበኛ ሠራዊት ስለሌላቸው ብዙ ጊዜ ቅጥረኛ ወታደሮችን እንደሚጠቀሙ ይነገራል።
በሌላ አንጻር ደሞ ከመንግሥታት በተጨማሪ አሸባሪ ቡድኖችና በተለያዩ አገራት ውስጥ ነፍጥ አንስተው ከመንግሥት ጋር የሚዋጉ ቡድኖችም ቅጥረኛ ወታደሮችን እንደሚጠቀሙ ዘገባዎች ይገልጻሉ። ለምሳሌም፤ በሶሪያ ውስጥ ከመንግሥት ጋር የሚዋጉ ታጣቂዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ቅጥረኛ ወታደሮችን ስለማሰለፋቸው ዘገባዎች ያሳይሉ።
በተመሳሳይም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል መንግሥት ከሕወሓት አሸባሪ ቡድን ጋር እያደረገ ባለው የሕግ ማስከበር ጦርነት ሕወሓት ቅጥረኛ ወታደሮችን እንደተጠቀመ የተለያዩ በፎቶ ጭምር የተደገፉ ዘገባዎች ወጥተው ነበር። መንግሥትም በበኩሉ ቅጥረኛ ወታደሮችን እንደያዘ ገልጾ ያውቃል።
“ቅጥረኛ ወታደሮች” የሚለው ቃል መደበኛ (ተራ) ነዋሪ ለሚባሉት ለብዙ አፍሪካውያን እንግዳ የነበረ ነው። ነገር ግን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም የሩስያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በአፍሪካ ውስጥ መጨመሩን ተከትሎ ምዕራባውያን አገሮች ሩስያ የዋግነር ቡድን (Wagner Group) በተባለ የቅጥረኛ ወታደሮች አቅራቢ ድርጅት በኩል በርካታ ወታደሮችን በአፍሪካ አሰማርታለች ማለታቸው በሰፊው ተዘግቧል። ሩስያም ጉዳዩን ለማስተባበል ስትል ትሰጠው በነበረ ምላሽ ምክንያት የኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ መገናኛ ብዙኀን ስለ ቅጥረኛ ወታደሮች በተደጋጋሚ ተሰምቷል።
ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች ምክንያት “ቅጥረኛ ወታደሮች” የሚለው ቃል በአሁን ጊዜ ለብዙ ኢትዮጵያውያን አዲስ ባለመሆኑ ብዙዎች ሲሰሙት ቃሉ እንግዳ ላይሆንባቸው ይችላል። በመሆኑም፤ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ቅጥረኛ ወታደሮች ማንነት አጠቃላይ ግንዛቤ ማስጨበጥ ሲሆን፣ ቅጥረኛ ወታደሮች የሚባሉት እነማን ናቸው? በሕግስ ምን መብት አላቸው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳትና ለጥያቄዎቹ መልስ ለመስጠት አንዳንድ ነጥቦችን እናያለን።
መነሻ ርዕሳችን ቅጥረኛ ወታደሮች በሕግ ያላቸው መብት ምንድን ነው? የሚል ስለሆነ ቅጥረኛ ወታደሮች ማለት ምን ማለት ነው? ከሚለው ጀምረን በተለያዩ ሕጎች ስላላቸው መብትና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በአጭሩ እንመለከታለን።
ስለ ቅጥረኛ ተዋጊዎች ማንነት ከተካተተባቸው ሕጎች መካከል አንደኛው እ.አ.አ. በ1977 የወጣው የ1949 የጄኔቫ ስምምነት ፕሮቶኮል ቁጥር አንድ ነው። ኹለተኛው ደግሞ በ1977 ቅጥረኛ ወታደሮች በአፍሪካ እንዳይኖሩ ለመከልከል የወጣው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስምምነት ሲሆን፣ ሦስተኛው በ1989 የወጣውና ቅጥረኛ ወታደሮችን መቅጠርና መጠቀም፣ በገንዘብ መደገፍና ማሠልጠንን የሚከለክለው ዓለም ዐቀፍ ስምምነት ነው። እነዚህም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የ1949 የጄኔቫ ስምምነት ፕሮቶኮል 1 ቅጥረኛ ወታደር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ፍቺ ያስቀመጠ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት ተከታዮቹን ነጥቦች ዘርዝሯል፤
ማንኛውም በአገር ውስጥ ወይም ከአገር ውጭ በቅጥረኛ ወታደርነት የተቀጠረ ሰው፤
በግጭት ወይም ጦርነት ውስጥ በቀጥታ የተሳተፈ፤
በግጭቱ ውስጥ ለመሳተፍ ያነሳሳው በዋናነት የግል ጥቅምን ለማግኘት በመፈለግ እና በግጭቱ ውስጥ በተሳተፉት ወገኖች ወይም በውክልና ቃል የተገባለት ሆኖ ለተመሳሳይ ማዕረግ እና ተግባር ላሉ ወታደሮች ከሚከፈለው በላይ ቁሳዊ ማካካሻ የሚከፈለው፤
በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑ ወገኖች የአንዳቸውም ዜጋ ያልሆነ ወይም በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆነ ወገን የሚቆጣጠረው ክልል ነዋሪ ያልሆነ፤
በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች አባል ያልሆነ፤ እና
በግጭቱ ውስጥ የሌለ አገር የመከላከያ አባል ሆኖ ለይፋዊ የሥራ ግዴታ ያልተላከ።
ስለሆነም፤ በ1949 የጄኔቫ ስምምነት ፕሮቶኮል 1 መሠረት አንድ ወታደር ቅጥረኛ ወታደር እንዲባል ከላይ የተዘረዘሩት መስፈርቶች ማሟላት አለባቸው። መስፈርቶቹም በአንድ ጊዜ ተሟልተው መገኘት ያለባቸው (cumulative requirements) ናቸው። ይህም ማለት፤ አንድ የተያዘ ወታደር ቅጥረኛ ወታደር ነው ወይም አይደለም የሚለውን ለመለየት በሚደረግ ማጣራት (ምርመራ) ከላይ ከተጠቀሱት መስፈርቶች ውስጥ አንዱ ከጎደለ አንድ ወታደር ቅጥረኛ ወታደር ሊባል አይችልም ማለት ነው።
አንድን ወታደር ቅጥረኛ ነው ወይም አይደለም የሚለውን ለመወሰን መስፈርቶቹን ካየን ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ፤ ቅጥረኛ ወታደሮች በሕግ ምን መብት አላቸው? የሚለው ይሆናል። በዚህም መሠረት ያላቸውን መብቶች ከላይ ከተጠቀሱት ሕጎች ጋር በማገናዘብ እንመልከት።
በፕሮቶኮሉ መሠረት ቅጥረኛ ወታደሮች እንደ ተዋጊና የጦር ምርኮኛ አይታዩም። ይህም ማለት፤ አንድ ቅጥረኛ ወታደር ሲያዝ መደበኛ ወታደር ሲያዝ ወይም ሲማረክ በሕግ ያሉት መብቶች አይኖረውም። ስለሆነም፤ የያዘው አካል እንደ ተዋጊ ወይም የጦር ምርኮኛ አድርጎ የማየት ወይም የማቆየት ግዴታ የለበትም።
ይህ ቢኖርም ግን የያዘው አካል እንደ ተዋጊ ወይም የጦር ምርኮኛ አድርጎ ሊያየውና በዚያው የሕግ አግባብ ሊያስተናግደው ይችላል። በሌላ አገላለጽ፤ ቅጥረኛ ወታደርን የያዘ አካል ቅጥረኛውን እንደ የጦር ምርኮኛ ቆጥሮ አግባብነት ባለው ሕግ ሊያስተናግደው ወይም በራሱ አገር የወንጀል ሕግ ሊዳኘው ሥልጣን አለው ማለት ነው። በዚህ መሠረትም ሩስያ በምሥራቅ ዩክሬን በዶንባስ ክልል ውስጥ በቅጥረኛ ወታደርነት ተሰልፈው ሲዋጉ የተያዙ እንግሊዛውያን ላይ በራሷ ሕግ በመዳኘት የሞት ፍርድ ፈርዳባቸዋለች።
ቅጥረኛ ወታደሮች በፕሮቶኮሉ መሠረት እንደ ተዋጊ ወይም እንደ ጦር ምርኮኛ ባይቆጠሩም፣ ነገር ግን ለአንድ ሰው የሚገባ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ሊደረግላቸው ግድ ይላል። ስለሆነም፤ የያዛቸው አካል ሰብዓዊ መብታቸውን የማክበር ግዴታ አለበት። በራሱ ሕግ ቢዳኛቸው እንኳ መሠረታዊው መብታቸውን ለምሳሌ ያለመሰቃየት መብታቸውን ሊያከብርላቸው ይገባል ማለት ነው።
በ1977 ቅጥረኛ ወታደሮች በአፍሪካ እንዳይኖሩ ለመከልከል የወጣው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስምምነት ከጄኔቫ ስምምነት ፕሮቶኮል 1 ጋር በአብዛኛው ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው። ነገር ግን የቅጥረኛ ወታደሮችን ፍቺ በሚሰጠው ቁጥር 3 ስር፣ በግጭቱ ውስጥ ለመሳተፍ ያነሳሳው በዋናነት የግል ጥቅምን ለማግኘት በመፈለግ የሚለውን የአስተሳሰብ መስፈርት አስወጥቷል። ይልቁንም በግጭት ወይም ውጊያ ውስጥ የሚሳተፈው እየተከፈለው ወይም ሌላ ቁሳዊ ጥቅም ሊያገኝ ቃል ተገብቶለት ከሆነ ከመደበኛ ወታደሮች ከፍ ያለ ወይም ያነሰ ቢከፈለው ለውጥ አያመጣም፤ እንደ ቅጥረኛ ወታደር ይቆጠራል። ፕሮቶኮሉ ግን ከፍ ያለ ክፍያ ማግኘትን እንደመስፈርት ያስቀምጣል።
ሌላው የአፍሪካውን ስምምነት ከፕሮቶኮሉ የሚለየው ዋና መገለጫ የአፍሪካው ስምምነት ቅጥረኛ ወታደር መሆን ወንጀል እንደሆነ በግልጽ ደንግጓል። ይህም ማለት፣ አንድ ቅጥረኛ ወታደር በግጭት ውስጥ በመሳተፉ ለፈጸመው ሌሎች ወንጀሎች ተጠያቂ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ቅጥረኛ ወታደር መሆን በራሱ ለብቻው የሚጥልበት የወንጀል ተጠያቂነት አለ።
በሌላ በኩል ደግሞ በ1989 የወጣውና ቅጥረኛ ወታደሮችን መቅጠርና መጠቀም፣ በገንዘብ መደገፍና ማሠልጠንን የሚከለክለው ዓለም ዐቀፍ ስምምነት ስለ ቅጥረኛ ወታደር ፍቺ ሲሰጥ ትንሽ ሰፋ ያለ ሆኖ ከጄኔቫ ስምምነት ፕሮቶኮል 1 ጋር በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን፣ በተለይም በፕሮቶኮሉ ፍቺ ቁጥር 2 ስር ያለውንና “በግጭት ወይም ጦርነት ውስጥ በቀጥታ የተሳተፈ” የሚለውን መስፈርት አስወጥቷል።
ይህም ማለት ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድም ተሳትፎ ማድረግ ቅጥረኛ ወታደር ሊያስብል ይችላል። እንዲሁም እንደ አፍሪካው ስምምነት ሁሉ ቅጥረኛ ወታደርነትን ወንጀል አድርጎ ደንግጓል።
እዚህ ጋር እግረ መንገዳችንን ብናየው መልካም የሚሆነው እ.አ.አ. በ2002 በሥራ ላይ የዋለውን የዓለም ዐቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ሕግ ሲሆን፣ ቅጥረኛ ተዋጊነት በዚህ ሕግ መሠረት ወንጀል ተብሎ አልተደነገገም። ፍርድ ቤቱ ከቅጥረኛ ወታደሮች ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን እንዲያይም ሥልጣን አልተሰጠውም።
በአጠቃላይ፣ ስለ ቅጥረኛ ተዋጊነት የወጡትን ከላይ የተጠቀሱ ሕጎች ስንመለከት የሚከተሉትን ማጠቃለያዎች ማስቀመጥ እንችላለን። የጄኔቫ ስምምነት ፕሮቶኮል 1፣ ቅጥረኛ ወታደሮች ስለማይኖራቸው መብቶች፤ ማለትም እንደ ተዋጊ እና የጦር ምርኮኛ መታየት እንደማይችሉ ቢያስቀምጥም፣ ነገር ግን ቅጥረኛ ወታደር መሆን ምን እንደሚያስከትል አላካተተም ወይም ቅጥረኛ ወታደርነትን ወንጀል አድርጎ አልደነገገም። ይልቁንም ትኩረቱ ሰብዓዊ መብት አያያዛቸውን በተመለከተ ሆኖ መሠረታዊ መብቶቻቸው እንዳይጓደሉ ነው።
የጄኔቫ ስምምነት ፕሮቶኮል 1 ቅጥረኛ ወታደሮች እንደ ተዋጊ እና የጦር ምርኮኛ መታየት እንደማይችሉ ቢደነግግም፣ የያዛቸው አካል እንደ ተዋጊና ምርኮኛ ቆጥሮ በፕሮቶኮሉ መሠረት ሊያስተናግዳቸው ይችላል።
በ1977 ቅጥረኛ ወታደሮች በአፍሪካ እንዳይኖሩ ለመከልከል የወጣው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስምምነት እና በ1989 የወጣውና ቅጥረኛ ወታደሮችን መቅጠርና መጠቀም፣ በገንዘብ መደገፍና ማሠልጠንን የሚከለክለው ዓለም ዐቀፍ ስምምነት ቅጥረኛ ወታደሮች በግጭት ውስጥ ሲሳተፉ በፈጸሙት ወንጀል መጠየቃቸው እንዳለ ሆኖ ቅጥረኛ ወታደር መሆናቸው ብቻ ራሱን የቻለ ወንጀል ሆኖ ያስጠይቃቸዋል። ይህም ኹለቱን ስምምነቶች ከጄኔቫ ስምምነት የሚለያቸው ባህሪ ነው።
በመጨረሻም፤ ቅጥረኛ ወታደሮች በኢትዮጵያ ሕግ የሚኖራቸውን እጣ ፈንታ በተመለከተ እንቃኝ። ምንም እንኳ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ቅጥረኛ ወታደሮችን በተመለከተ ልዩ የሕግ አንቀጽ ባይኖርም፣ ነገር ግን በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9 ንዑስ-አንቀጽ 4 መሠረት ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው በሚል ይደነግጋል። እንዲሁም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 13 ንዑስ-አንቀጽ 4 መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ከዓለም ዐቀፍ ስምምነት መስፈርቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ መተርጎም አለባቸው ሲል ደንግጓል።
ስለሆነም፤ ኢትዮጵያ ቅጥረኛ ወታደሮች በአፍሪካ እንዳይኖሩ ለመከልከል የወጣው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስምምነት ፊርማ ያጸደቀች አገር በመሆኗና ስምምነቱ ቅጥረኛ ተዋጊነትን ወንጀል አድርጎ ስለደነገገ፤ በስምምነቱ መሠረት በወንጀል ተጠያቂ ልታደርጋቸው ትችላለች። ነገር ግን፣ የጄኔቫ ስምምነትንም ፈርማ ያጸደቀች አገር በመሆኗ ደግሞ ቅጥረኛ ወታደሮችን በግዛቷ ውስጥ ከያዘች፤ ምንም እንኳ እንደ ጦር ምርኮኛና ተዋጊ ልትመለከታቸው ግዴታ ባይኖርባትም፣ ስምምነቱ የጣለባትን መሠረታዊ መብታቸውን የማክበር ግዴታ አለባት።
ሽመላሽ ወንዳለ፤ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ እና በዓለም ዐቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ኹለተኛ ዲግሪ፤ በኢ-ሜል አድራሻቸው [email protected] ላይ ይገኛሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014



