ኢሬቻ የምርቃትና የምስጋና ገበታ ባሕል ወይስ ሃይማኖት?

0
1560

በትላንትናው ዕለት የአዲስ አበባ ጎዳናዎችና አደባባዮቿ በጥቁር፣ ቀይና ነጭ ቀለማት ባንዲራዎች አሸብርቋል። የኦሮሞ ወጣት ወንዶች በየመንገዱ እየጨፈሩ ጎዳናውን አድምቀውት ውለው አምሽተዋል። በዛው መጠንም የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በጥብቅ የፀጥታ ቁጥጥር ሥር ወድቀዋለ፣ የጸጥታው ቁጥጥርም መደረግ የጀመረው ከረፋድ ጀምሮ ነበር።

ዛሬ በአዲስ አበባ የሚከበረው ኢሬቻ በቀጣይ ዓመታትም ለአዲስ አበባ ተጨማሪ ውበት፤ ተጨማሪ ድምቀት ሆኖ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።
የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ዛሬ በአዲስ አበባ ነገ ደግሞ በቢሾፍቱ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ የኢሬቻ በዓል አከባበር አመጣጥ አፈ ታሪክን መነሻ በማድረግ ለምን እንደሚከበር፣ ሃማኖታዊና ባሕላዊ አንድምታውን እንዲሁም በበዓሉ ላይ የሴቶች ተሳትፎን በተመለከተ መጻሕፍት አገላብጣና የሚመለከታቸውን ባለሞያዎች በማነጋገር ኢሬቻን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

አፈታሪክ እንዲህ ይላል፤ አቴት ኹለት ወንድሞች ነበሯት። ከዕለታት በአንዱ ቀን በአንድ ጉዳይ ይጋጩና ታላቅ ወንድም ታናሹን ይገድለዋል። በዚህም እህት በእጅጉ ታዝናለች፤ ሟች ወንድሟንም አልቅሳ ትቀብራለች። ይህ ሲሆን ገዳይ ወንድም ከአካባቢው ርቆ ጠፍቶ ነበር። ታድያ ወንድሟ በተቀበረበት ቦታ ላይ ኦዳ ተከለች፤ ያንን ኦዳም ከአባይ ውሃ እየቀዳች ታጠጣው ጀመር፤ ይኼኔ ችግኝ የነበረው ጸደቀ። እናም በየዓመቱ ወንድሟን ለመዘከር ቀብሩ ላይ መሔዱን ተያያዘችው፤ ኦዳው ሥር።

ከዓመታት በኋላ የጠፋው ገዳይ ወንድም ተመልሶ ኹለቱ ቤተሰቦች በጉማ ይታረቃሉ፤ በኦዳው ሥር። ይህ አፈታሪክ ከዛሬ 12 ሺሕ ዓመት በፊት ጀምሮ የተሰማና የተነገረ ሲሆን አፈታሪክ ብቻ አልነበረም። ለገዳ ስርዓት አብዛኛው እንቅስቃሴ መነሻ የሆነ እንዲሁም የኢሬቻም ጅማሬ ነው።
ይህን ታሪክ ያጫወቱን በኦሮሞ ባሕል ማዕከል የኦሮሞ ታሪክ ጥናት ቡድን መሪ እና የታሪክ ተመራማሪ ዓለማየሁ ኃይሌ፤ “እርሷ [አቴት] በሠራችው ጸሎትና ለቅሶ እግዚአብሔር እርቀ ሰላምን አውርዷል ማለት ነው። እና ከዛ በኋላ አቴት የቤተሰብ ጠባቂ ተባለች” ሲሉ አክለዋል። ከዚህ በኋላም ነው ኦዳ የሕግ ማርቀቂያና የስምምነት ቦታ፣ ኢሬቻም በዚህ ማስታወሻነት አንድ ብሎ የጀመረው፤ በአፈ ታሪክ።

የኢሬቻ መሠረት
ከላይ እንደተጠቀሰው በአፈ ታሪክ የኢሬቻ አጀማመር ወደ 12 ሺሕ ዘመናት ይራቅ እንጂ በገዳ አቆጣጠር (አንድ ገዳ 7 ዓመት ከ8 ወር ወይም 8 ዓመት) ከ6 ሺሕ 660 ዓመት በፊት የተጀመረ ነው ሲሉ ዓለማየሁ ያስረዳሉ። የገዳ ስርዓት ባለበት፤ የኦሮሞ ሕዝብ በሚገኝበት ሁሉም ኢሬቻ አለ። በዓሉ ዋቄፈንና ከተባለውና ከጥንቱ የኦሮሞ ሕዝብ እምነት የፈለቀ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ የታሪክ ተማሪ የሆኑት ሰለሞን ስዩም፤ ኦሮሞ እውነትን በሦስት ዓውዶች ያያል ይላሉ። ቀዳሚው “ኡማ” የሚባል ሲሆን ፍጡር ማለት ነው፤ ይህም በፍልስፍና ‘ኮስሞሎጂ’ እንደሚባል ይገልጻሉ። ‘ኡማ’ ህዋ (Universe)ን እና በህዋ ላይ ያለውን ሁሉ የሚያጠቃልል ማለት ነው። በጥቅሉ የትኛውም ቁሳዊና መንፈሳዊ ነገር፤ የሰው ልጅን ጨምሮ ‘ኡማ’ ወይም ፍጡር ይባላል።

ፍጡር ካለ ከፍጡር የሚልቅና ሁሉን የሠራ ፈጣሪ መኖር ስላለበት፤ ኹለተኛው አውድ ‘ዋቃ’ ወይም አምላክ ነው። ‘ዋቃ’ አልፋና ኦሜጋ ተደርጎ ይቆጠራል። ታድያ አንዳንድ መጻሕፍት ‘ዋቃ’ ሰማይ ማለት ነው ሲሉ ኦሮሞ ሰማይ ነው የሚያመልከው በማለት እንደሚናገሩ ይገልጻሉ፤ ምንም እንኳ ሰማይ የሚገለጥበት የራሱ የሆነ ቃል ቢኖርም። በአንጻሩ ደግሞ ሌላ ጥናት በላቲን ሲጻፍ የመጀመሪያዋ ፊደል የሚጻፍበት አኳኋን ትርጉሙን እንደሚወስንና ‘ Wakka’ ሲሆን አምላክ፤ ‘ wakka’ ሲሆን ደግሞ ሰማይ ነው የሚሉም አሉ፤ እንደ ሰሎሞን ገለጻ።

ከዚህም በሻገር ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ያነሱትን ሐሳብም ይጠቀሳሉ፤ ‘ ዋቃ’ ሳይሆን ‘ ዋካ’ ነው የሚባለው፤ በ’ ቃ’ እና ‘ ካ’ ንባብ መካከል የተፈጠረ ልዩነት አለ የሚለው።

በጥቅሉ ግን ዋቃ ሁሉንም የሚሸከም፣ ሁሉን የሚያኖርና የሚችል ነው፤ በኦሮሞ ሕዝብ እምነት። በክርስትናው እምነት የሀይማኖት ጸሎት ላይ፤ ‘…ሰማይና ምድርን የፈጠረ፣ የሚታየውንና የማይታየውን…ያለእርሱ ምንም ምን የሆነ የለም’ እንደሚል ሁሉ፤ በኦሮሞ እምነትም ዋቃ በዚህ መልክ ይጠቀሳል ወይም ይገለጻል ይላሉ።

ታድያ ‘ዋቃ’ ወደ ሕዝቡ የሚወርድበት መንገድ አለ፤ ይህም አያና እንደሚባል ሰለሞን ጠቅሰዋል። የተቀደሰውን አያና በሚመለከት፤ ሁሉም ሰው እንዲሁም ሁሉም ፍጡር የየራሱ አያና አለው ተብሎ ይታመናል። በማነጻጸሪያነት ክርስትናው ላይ ያለውን እምነት ያነሱት ሰከለሞን፤ “ሁሉም ሰው የየራሱ ጠባቂ መልአክ አለው እንደሚባል ሁሉ በኦሮሞም ሁሉም የየራሱ አያና አለው ተብሎ ይወሰዳል። ፈጣሪ ራሱን የሚገልጠው በዚህ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ ሦስተኛው ነው፤ ይህም ፍጡር ካለና ፈጣሪም ካለ፤ በኹለቱ መካከል ምን ዓይነት ግንኙነት ነው የሚኖረው የሚለውን ለመመስረት ‘ሰፉ’ የሚባል ሕግ መጣ። በ‘ሰፋ’ ምን ዓይነት አሠራርና ስርዓት ይኑር የሚለው ሲብራራ፣ ሰውን ማዕከል አድርጎ፤ በአንድ ሰውና በዙሪያው ባሉ ነገሮች መካከል ሁሉ ምን ዓይነት መመሪያ ይኑር የሚለውን የሚመለከት ነው።

ይህ እንዲሆን ያስቻለውን ምክንያትና የ‘ሰፉ’ን እሳቤ በተለያየ መንገድ የገለጹ የጥናት ሥራዎች መኖራቸውን ሰለሞን ያነሳሉ። በአንድ በኩል በፈጣሪና በሰው መካከል ያለው ሕግ አልባ ግንኙነት ውጥረት ስላመጣ ነው ‘ሰፉ’ ያስፈለገው ሲባል በአንጻሩ የሥነ ምግባር ፍልስፍና ብቻ ሳይሆን የሥነ እውቀት ጉዳይ ነው የሚሉም አሉ። ‘ሰፉ’ ታድያ በጥቅሉ ስርዓቱ ነው፤ የሚያስታርቀው፤ በሰውና በቀሪው ነገር ሁሉ መካከል ያለውን የሚገዛውም ነው።

ታድያ ወደ ነገራችን ስንገባ፤ ኢሬቻ አንዱ የ‘ሰፉ’ አካል ነው ማለት ነው። ኢሬቻ ፖለቲካዊ ካባ ሳይደርብ ከጥንት መሠረቱ ሲታይ፤ የትኛውም ሰው ጥሩ ነገር ሲያገኝ ፈጣሪውን እንደሚያመሰግን፣ ችግር ሲገጥመውም እንደሚለምን ያለ የየዕለት ስርዓት ነው፤ ኢሬቻ። በጋራ የሚደረግ መሆኑም አንዱ ገጽታው ሆኖ ሳለ፣ ወቅት ጠብቆ ብቻ የሚደረግ አለመሆኑን ሰለሞን ይገልጻሉ።

ለምን ይከበራል?
የኦሮሞ ሐይማኖት ማዕከል የሚያጠነጥነው ዝናብ፣ ሰላም እና ትውልድ ዙሪያ ነው። እናም ታድያ ኢሬቻ ለምን ይከበራል የተባለ እንደሆነ፤ ዝናብ፣ ሰላምና ትውልድ የሚሰጥ ፈጣሪን ለማመስገን ነው፤ ቀኑም የምስጋና ቀን ነው የሚባለው። ይህም ለፈጣሪ የሚቀርብ ምስጋና ሲሆን ዓለማየሁ ይህን ሲያብራሩ እንዲህ አሉ፤ “አንድ ሰው ታምሞ ሳለ መድኀኒት ሌላ ሰው ቀርቦ ቢሰጠው በምላሹ ዝም ብሎ አይሔድም፤ ይልቁንም ካለው ዐሥር ሳንቲምም ይሁን ለበረከት ብሎ ምስጋና ወይም ስጦታ ከሣር ጋር ይሰጣል። ሣር እርጥበ ነው፤ ልምላሜ ማለት ነው። ይህም ‘ኢሬቻ ሰጠኝ’ ይባላል። ከዛ ተነስቶ እስከ ትልቁ የኢሬቻ በዓል ድረስ ትርጉሙ ምስጋና ነው። ይህኛው ደግሞ ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረቢያ ነው።
ሰለሞን እንደጠቀሱት ሁሉ ታድያ ዓለማየሁ ሲያክሉ፤ ኦሮሞ ጠዋት ማታ ለምለም ቄጠማ ይዞ ፈጣሪን እንደሚያመሰግን ያወሳሉ። ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ በሰላም ያሳደርከኝ በሰላም አውለኝ፤ ልጆችና ከብቶቼን ጠብቅልኝ ብሎ ይጸልያል፤ ምሽት ደግሞ በደኅና ያዋልከኝ በሰላም አሳድረኝ ብሎ ፈጣሪን ይለማመናል።

የኦሮሚያ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኢሬቻን በተመለከተ ባሰራጨው በራሪ ወረቀት፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የሃይማኖት (የእምነት) ተቋማትን በውስጡ የያዘው የገዳ ስርዓትን፣ ጠቅሶ የኢሬቻ በዓል በዚህ ሥር ከሚከበሩ ትልልቅ በዓላት መካከል አንዱ ነው ይላል። ኢሬቻ ማለት ጥንታዊ የአባይ ሸለቆና መስክ የኦሮሞ ሕዝቦች ዘንድ ፈጣሪ አምላክን (ዋቃን) ለማመስገን፣ ምልጃ ለመጠየቅ የሚከናወን ስርዓት ነው ሲል ያብራራዋል።

የጋራ የምስጋና በዓል የሆነው ኢሬቻ በኹለት ትልልቅ ቦታዎችና ወቅቶች ይከበራል፤ በሐይቅና ወንዞች (ኢሬቻ መልካ) እንዲሁም በተራራዎች ላይ (ኢሬቻ ቱሉ)። የዓመቱ የመጀመሪያው የሚባለውና አሁን (ዛሬ መስከረም 24 እና 25/2012) እየተከበረ ያለው አንደኛው ነው። ይህም “ከክረምቱ አስፈሪ ነጎድጓድ እንኳን ወደ ብርሃኑ አወጣኸን። ብራውን ዘመን የሰላም አድርግልን” ሲሉ ተሰባስበው በሐይቆችና በጅረቶች ዙሪያ ሆነው የሚያመሰግኑበት በዓል ነው።

የኦሮሚያ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮው ባሰራጨው በራሪ ወረቀት፣ በዓሉ በአንዳንድ ቦታዎች ‘የብራ በዓል’ ይሉታል ሲል አስፍሯል። ይህንም የሚሉት ወቅቱ የክረምቱ ጨለማ አልፎ በብርሃንና በአበባ ወራት የሚተካው በመስከረም ወር ስለሆነ ነው ይላል።

ኹለተኛው ደግሞ የበጋ ወራቶች አልፈው በበልግ ወቅት መግቢያ ላይ የሚከበረው በተራራ ላይ የሚፈጸመው ኢሬቻ ነው፤ ኢሬቻ ቱሉ። ይህም ከፍተኛ ፀሐይ የሚታይበትና የውሃ እጦት የሚከሰትበት በመሆኑ፣ መጋቢት ወር ላይ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ተሰብስቦ ፈጣሪ (ዋቃ) ዝናብ እንዲያዘንብላቸው የሚጠይቁበት ነው። “ውሃ እና እርጥቡን አትንሳን” ሲሉ ፈጣሪን የሚለምኑበት ነው። ይህም ብዙ ጊዜ በተራሮች አናት ላይ የሚደረግ መሆኑን ዓለማየሁ ይናገራሉ።

ተራራ ላይ ለምን ሆነ? ተራራ የደመና መገኛና እርጥበታማ በመሆኑ ነው። “በተራራ ላይ ወጥቶ አምላክን በጋራ መማጸንና መለመን ከጥንታዊው የኩሾችና የአባይ ሸለቆ ሕዝቦች የእምነት አተገባበር ጋር በእጅጉ የተቆራኘና የተሳሰረ ባሕላዊ ድርጊት ነው ይባላል።” ሲል የባሕልና ቱሪዝም ቢሮው ኅትመት ያክላል።

“የኢሬቻ/ኢሬሳ/ በዓል ትውፊትና አከባበር” በሚል ርዕስ የኤትኖግራፊ ባለሙያውና የታሪክ ተመራማሪው አፈንዲ ሙተቂ በማህበራዊ ድረ ገጽ ፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው ኢትኖግራፊ ቀመስ ወግ፤ “ፍጥረት የተገኘው ከውሃ ነው” ተብሎ በሚታመንበት በኦሮሞ ዋቄፈንና እምነት፤ እነዚህ በዓል ማክበሪያ ስፍራዎች በሙሉ ማለት በሚቻልበት መልኩ በሐይቅ ዳርቻ የሚገኙ ናቸው ይላል። ይህን ተከትሎ በዓሉ የሚከበርባቸው ስፍራዎች በዋናነት ስድስት ሐይቆች ናቸው።

እነርሱም “ሆረ አርሰዲ”፣ “ሆረ ኪሎሌ”፣ “ሆረ ሀዶ”፣ “ሆረ ገንደብ”፣ “ሆራ ዋርጦ” እና “ሆረ ኤረር” ይባላሉ። በዋናነት የሚከበረው ደግሞ “ሆረ አርሰዲ” በተሰኘው ሐይቅ ዳርቻ ነው ሲል አፈንዲ ይቀጥላል።

እነዚህም ብቻ ሳይሆኑ በእምነቱና በአከባበር ስርዓቱ ስምንት ተራሮችም ይገኛሉ፤ እነዚህም ሆረ አርሰዲ ዙሪያ የሚገኙ ሲሆኑ “ቱሉ ጩቃላ”፣ “ቱሉ ኤረር”፣ “ቱሉ ፉሪ”፣ “ቱሉ ገላን”፣ “ቱሉ ዋቶ ዳለቻ”፣ “ቱሉ ፎየታ”፣ “ቱሉ ወጨጫ” እና “ቱሉ ኤግዱ” ይባላሉ።
ወዲህ ወደ ኢሬቻ በዓል አከባበር ስንመለስ፤ የበዓሉን መከበር ምክንያት አፈንዲ ሲገልጽ “የኢሬቻ በዓል የሚከበረው ለዋቃ ምስጋና ለማቅረብ ነው። ዋቃ ክረምቱን በሰላም ስላሳለፈልንና ከሰማይ ባዘነበው ውሃ መልካም ፍሬ ስለሰጠን ያለ ክፍያ በቸርነቱ ለሚንከባከበን አምላክ ምስጋና ማቅረብ የተገባ በመሆኑ ነው ይላሉ” ሲል የኦሮሞ አባቶችን ጠቅሶ አስፍሯል።

በዓሉ በቀደመው ዘመን እና በጥንታዊ ኦሮሞዎች ዘንድ ሲከበር፤ በነገድ ደረጃ የሚከበርና የአከባበር ሥነ ስርዓቱም በዞን ደረጃ ባሉ የበዓል ማክበሪያ ስፍራዎች የሚፈጸም ነው። እነዚህ ስፍራዎች የሚገኙት ደግሞ የእያንዳንዱ የኦሮሞ ነገድ የፖለቲካና የመንፈሳዊ ማዕከላት ባሉበት አቅራቢያ ነው፤ እንደ አፈንዲ ገለጻ።

ኢሬቻ የሚከበረው አዲስ ዓመት በሚገባበት ዓመት ይልቁንም ከመስቀል በዓል ሦስት ቀናት በኋላ ነው። ይህ ቀን ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ እስካልዋለ ድረስ በዓሉ እንደሚከበር ዓለማየሁ ይናገራሉ። በኦሮሞ ባሕል አንድ በዓል ከተከበረ በኋላ ለሦስት ቀናት ማረፍ የሚጠይቅ ባሕል በመኖሩ ነው ከመስቀል በኋላ ሦስት ቀን የሚጠበቀው። ያም ብቻ አይደለም፤ ሁሉም ቦታ በእኩል ቀን ነው የሚከበረው ይላሉ።

ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ወይስ ባህላዊ?
ኢሬቻ መዋቅራዊ አቀማመጡ ሃይማኖታዊ እንደሆነ ይነግረናል። ይልቁንም የዋቄፈንና እምነት ተከታዮች በስፋት የሚያከብሩት በዓል እንደሆነም ሲነገር ይሰማል። ይሁንና የማንኛውም እምነት ተከታይ የሆነ ሰው ኢሬቻ ላይ እንዲታደም ፈቃድ አለው። ነገሩ ከኦሮሞ ታሪክ አጥኚዎችና ከታሪክ ተመራማሪዎች ይሁን ወይም ከአድማጭና ተመልካች ማኅበረሰብ ተከታታይ አለመሆን፤ ሌላ ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ቢሆንም፤ ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ የሚነሳ ነው፤ ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ነው ወይስ ባሕላዊ በዓል?

ሌንሴ አያና በኦሮሞ ባሕል ማዕከል ጊቢ ከኢሬቻ ጋር በተያያዘ የቀረበው ዓውደ ርዕይና ባዛር ላይ ለመሳተፍ ተገኝታለች። የክርስትና እምነት ተከታይ ስትሆን የኢሬቻ በዓልን ነፍስ ካወቀችበት ዕድሜ ጀምሮ ትሳተፍ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ገልጻለች። ለሌንሴ ኢሬቻ የኦሮሞ ተወላጅነቷና የማንነቷ አንድ ክፍል ነው። በበዓሉ ላይ ስትታደምም ያሉት ባሕላዊ ድርጊቶች እንደሚማርኳት ትገልጻለች።

እንደ ሌንሴ ያሉ እጅግ በርካታ የኢሬቻ በዓል ተሳታፊና አክባሪ ሰዎች አሉ። የዋቄፈና እምነት ተከታይ ባይሆኑም እንኳ የኢሬቻ በዓልን እንደ አንድ የኦሮሞ ባሕልና የማንነት መገለጫ ወስደው የሚሳተፉበት። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰለሞን እንዳሉት በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘትና መሠረት አለው፤ ነገር ግን ከባሕል የሚደባለቀ ነው። በዚህ ልክ አይሁን እንጂ በሌሎች ሃይማኖታዊ በዓላት በተመሳሳይ ከባሕል ጋር መቀላቀል የሚታይ መሆኑን አንባቢ ሳያስተውል አይቀርም። ብዙ ጊዜ ደግሞ አሸናፊ ሆኖና ጎልቶ የሚወጣው ባሕላዊ እሴት መሆኑንም መታዘብ ይቻላል።

አንድ አምላክ አለ ብሎ የሚያምንና እርሱንም ‘ዋቃ’ እያለ የሚጠራ የኦሮሞ ማኅበረሰብ፤ ይህን አምላክ ‘አንድ ነገር ግን ባለብዙ [መቶ] ስም’ ይለዋል፤ በአፋን ኦሮሞ “ቶኪቻ መቃ ኢባ”። ታድያ በዚህም የእምነት መሠረት ላይ በኢሬቻ ምስጋና የሚቀርብለት ይህ ባለመቶ ሥም አንድ አምላክ በመሆኑ ሃይማኖታዊ መሠረቱ እዚህ ላይ የሚሰመር ነው። ለዚህ አምላክ የእምነቱ ተከታይ ያልሆነ ሰውም ምስጋና ቢያቀርብ መልካም ነው ተብሎ ስለሚታሰብም ለማንም አይከለከልም። በተጓዳኝ ደግሞ በተለይ በጊዜ ሒደት የኢሬቻ ባሕላዊ እሴቶቹ ከፍ እያሉ መጥተዋል ሲሉ ሰለሞን ይጠቅሳሉ።
‘ቂም ይዞ ጸሎት፣ ሳል ይዞ ስርቆት’ እንዲል፤ የተጣሉ ሰዎች ሳይታረቁ ኢሬቻ ላይ መገኘት አይችሉም፤ በትውፊቱ። በዚህ ምክንያት ወደ ኢሬቻ ያልሔደ ሰው ደግሞ መገለል ሊደርስበት ስለሚችል አማራጩ እርቅ ማውረድ ነው። እናም ኢሬቻ እንዲህ ያለ አሉታዊ የሆነ በጎ ተጽዕኖ በማሳደር ያደርጋል። ይህም ባሕላዊ እሰቱን የበለጠ ከፍ እንዲል አድርጎታል። ይህም ብቻ ሳይሆን በቀደመው ጊዜ ለዕጽዋት መጠበቅና መንከባከብን አንዱ ጉዳይ በመሆኑ፤ ፈጣም ለልምላሜ ቅርብ ነው ተብሎ ስለሚታመን ለተፈጥሮ ሀብት ጥንቃቄ ማድረግም አለ።

ሰለሞን ሲናገሩ፤ ኢሬቻ አንድነት በማምጣት ረገድ፣ ሌሎችን በመከተል ሞዴል መሆን አይቻልምና ሰው ወደ ማንነቱ እንዲሔድ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ይላሉ። ኢትዮጵያም እርሷ ጋር ብቻ የሚገኙ፣ የራሷ የሆኑ እንደ ኢሬቻ ያሉ ሀብቶቿን ቀድማ ነበር ማውረስ የነበረባት ባይ ናቸው።
የአንድነት የስበት ኃይል በርትቶ የሚታይበት የኢሬቻ በዓልም፤ ባለው ማኅበራዊ ፋይዳ ምክንያት ሃይማኖታዊ መሠረቱ እንዳለ ሆኖ ባሕላዊ ገጽታው ጎልቶ ሊወጣ ችሏል። ሰለሞንም በዚህ ያምናሉ፤ እንዲህም አሉ፤ “በተለይ ጊዜያዊ ለሆኑ ስሜቶች ባለመገዛት፣ ፖለቲካዊ አንድምታ ባለመስጠት የሚከበር ከሆነ፣ ኢሬቻ የሚያስተሳስር እሴት ነው። የሌሎችን የማንነት መገለጫ የራስ በማድረግ አየተሳሰርን እንሔዳለን የሚል ሃሳብ አለኝ።” ብለዋል።

ታድያ ግን ይህን ጥያቄ ለማንሳት አንድም ምክንያት የሚሆነው በዓሉን ከተለያዩ ሰው ሠራሽ ተግባራት ጋር እኩል በመታየቱ ምክንያት ነው የሚሉ አሉ። ‘ባዕድ አምልኮ’ የሚለው ቃል ይህንን ሐሳብ የሚገልጸው ከሆነ ይህን ቃል እንጠቀማለን። ታድያ አንዳንድ ሰው ሠራሽ ተግባራት በበዓሉ ላይ ያሉ አመለካከቶችን እንደከፋፈለው ሰለሞን ጠቀስ አድርገው አልፈዋል።

ኢሬቻና ‘ሰው ሠራሽ’ ተግባራት
ሰው ሠራሽ ተግባራት የተባሉት ሰዎች በልምድ የኢሬቻ በዓልን አስታከው የሚፈጽሟቸውና በገዳ ስርዓትም ሆነ በኢሬቻ አከባበር ላይ አሉ ተብሎ ያልተጠቀሱ ተግባራትን ነው። እነዚህን በአንድ ጎን ‘ባዕድ አምልኮ’ የሚባሉት ናቸው።

እናም ታድያ የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ሐይቅና ወንዝ ላይ እንስሳ አርደው ደም የሚያፈሱ፣ መስዋዕት የሚያቀርቡ አልታጡም። ይህ ግን ትክክለኛ እንዳልሆነ በተለያየ ጊዜ ባሕሉንና ስርዓቱን የሚያውቁ የኦሮሞ አባቶች ይናገራሉ። የዘንድዎውን የኢሬቻ በዓል በተመለከተም በበዓል ማክበሪያ ስፍራዎች የሚከናወኑ ባዕድ አምልኮዎች የኦሮሞን ባሕል የሚወክሉ እንዳልሆነ የአባገዳዎች ምክር ቤት አፈጉባኤ ጫላ ሶሪ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፤ የኢሬቻ በዓል ሲከበር ባዕድ አምልኮ የሚመስሉ ኦሮሞ የማይፈጽባቸው ተግባራት ይከናወናሉ። በግ አርዶ ጭንቅላቱን ውሃ ውስጥ መጣል፤ ጥቁር ዶሮዎችን እራስ ላይ በማዞር ውሃ ውስጥ መክተት፣ አረቄና ውስኪ ውሃ ውስጥ መጣል እና ሽቶ ማርከፍከፍን የጠቀሱ ሲሆን፣ እነዚህ ተግባት ሊቆሙ ይገባል ሲሉ አሳስበዋልም። ቃል በቃል “በእነዚህ ነገሮች ኦሮሞ ፈጣሪውን አይለምንም፤ ምስጋናም አያቀርብም” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን በተመለከተ ታሪክ አጣቅሶ አፈንዲ በበኩሉ ሲያስረዳ፤ ከጣልያን ወረራ በኋላ ጠንቋዮቹ በዚያ አካባቢ መስፈራቸውን ይገልጻል። ነገረ ታሪኩን ከአፈንዲ ቃል በተሻለ ማብራራት ስለማይቻል ቃል በቃል እንዲህ ይላል፤

“በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ በዓላትን የማክበርና ዋቃን የማምለክ ተግባራት እንዳያከናውን ታገደ። ይሁንና ልዩ ልዩ የኦሮሞ ጎሳዎች እየተደበቁም ቢሆን ወደ ማክበሪያ ስፍራው መሔዳቸውን አላቋረጡም። በጣሊያን ዘመን ደግሞ እንደ ጥንቱ ዘመን ሰብሰብ ብለው በዓሉን ማክበር ጀመሩ።

የገላን፤ የቢሾፍቱ እና የዱከም ወረዳዎች በጥንታዊው የቱለማ ኦሮሞ ደንብ መሰረት የነገዱ ፖለቲካዊና መንፈሳዊ ማዕከላት ናቸው፤ እነዚህ መሬቶች በቱለማ ኦሮሞ ዘንድ “ቅዱስ” ተብለው ነው የሚታወቁት። “ቃሉ” የሚባለው የሕዝቡ መንፈሳዊ መሪም የሚኖረው በዚህ አካባቢ ነው። የቱለማ ኦሮሞ ኢሬቻን የመሳሰሉ ታላላቅ በዓላት የሚያከብረውም በዚሁ ስፍራ ነው።

ጣሊያን ሲወጣ እንደገና በጅምላ ወደ ስፍራው እየሔዱ በዓሉን ማክበሩ ቀረ። ነገር ግን ኦሮሞዎች ከጣሊያን በኋላም በተናጠልና በትንንሽ ቡድኖች እየሆኑ መንፈሳዊ በዓላቸውን በስፍራው ማክበራቸውን አላቋረጡም።

እንግዲህ በዚያ ዘመን ነው ጠንቋዮቹ በአካባቢው መስፈር የጀመሩት። እነዚህ ጠንቋዮች ይህንን ስፍራ ምርጫቸው ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት ሕዝቡ መሬቱን እንደ ቅዱስ ምድር የሚመለከት መሆኑን ያውቃሉ። “ቃሉ” የሚባለው የጥንቱ የኦሮሞ አገር በቀል እምነት መሪ በስፍራው እየኖረ የሕዝቡን መንፈሳዊ ተግባራት ይመራ እንደነበረም ያውቃሉ። የኦሮሞ ቃሉ በሕዝቡ ከፍተኛ ክብር እንደሚሰጠው እና ንግግሩ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዳለውም ይገነዘባሉ። “ቃሉ” አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ከ“ዋቃ” የተሰጠውን ገደብ ሳይጥስ “ራጋ” የማከናወን ሥልጣን እንዳለውም ይረዳሉ።
እንግዲህ ጠንቋዮቹ የዘረፋ ስትራቴጂያቸውን ሲወጥኑ በጥንታዊው የኦሮሞ የዋቄፈና እምነት ተከታዮች ዘንድ እንደ ቅዱስ የሚወሰደው ያ ማዕከላዊ ስፍራ ብዙ ገቢ ሊዛቅበት እንደሚችል ታያቸው። በመሆኑም በዚያ ቅዱስ ስፍራ ከትመው ከጥንቱ የኦሮሞ ቃሉ ሥልጣንና ትምህርት የተሰጣቸው እየመሰሉ ሕዝቡን ማጭበርበርና ማወናበድ ጀመሩ። እናም የቢሾፍቱ ቆሪጦች እና ኢሬቻ በምንም መልኩ አይገናኙም። ስለዚህ ኢሬቻን ከጥንቆላም ሆነ ከባዕድ አምልኮ ጋር ማያያዝ ስህተት ነው” ይላል።

ሴቶች በኢሬቻ
“ኢሬቻ የሚጀምረው ከሴቶች ነው፤ የበዓሉ ምክንያት አንድም የእርቅ መነሻነት ነውና ነው።” ሲሉ የገለጹት የታሪክ ተመራማሪው ዓለማየሁ፤ በተለይ የአቴትን ድርሻ ያነሳሉ። ታድያ በኢሬቻ በዓል ላይም በኦሮሞ የባሕል ልብሶች ያጌጡና የተዋቡ ሴቶች፣ ሲቄ የያዙ እናቶች ትንንሽ ሴት ልጆችን ጨምሮ ከፊት ቀድመው እንዲሰለፉ ይደረጋል። ይህ ማለት በዓሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ለወጣት ሴቶች፣ ለልጃገረዶች፣ ለእናቶችና ለአባ ገዳ ሚስቶች ነው ማለት ነው።

በገዳ ስርዓትና ፍልስፍና ሴቶች እንደ ጻድቃን ይቆጠራሉ፤ ስለዚህ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ማለት ነው። ለባልቴቶችና ለሕጻናት ቅድሚያ የሚሰጠውም ለዚሁ ሆኖ በተጨማሪ ፈጣሪ ለእነርሱ ምህረት እንደሚያደረግም ይታመናል። ቄጠማ የሚሰጡትም እናቶችና ልጆች የሆኑት ለዛ ነው። ከኢሬቻ ባሻገር ስለ ሲቄ ያነሱት ዓለማየሁ፤ ሰዎች ቢጣሉና ጥሉ ምን ያህል የከረረና የበረታ የሚባል ቢሆን ሴቷ ሲቄዋን ይዛ “እልልልል…” እያለች ከመካከል ከገባች ሁሉም ጥል ያቆማል፤ ኹከትም ካለ ይረጋጋል። ይህም ሴትን ምክንያት ያደረገ አንዱ የሰላምና የእርቅ መንገድ ነው።

ከዚህ ባሻገር አባ ገዳ ከብቶችን ነድቶ ወንዝ ሲያሻግር መጀመሪያ በቅርብ ያለች ልጃገረድ ወንዙን እንድትመታው (በመቀነት ወይ በቀሚሷ) ያደርጋል፤ ከብቶቹን ይዞ የሚሻገረውም ከዛ በኋላ ነው። በድምሩ ሴቶች በፈጣሪ ፊት ሞገስ ማግኘታቸውን የገዳ አብዛኛው ስርዓት የሚያሳይና ያንንም የሚናገር ነው።

ታድያ እንዲህ በኢሬቻ በዓልም ሴቶች ከፊት ሆነው ‘ማሬዎ’ እያሉና የተለያዩ ዜማዎችን እያሰሙ ነው ወደ በዓሉ ማክበሪያ ስፍራ የሚያቀኑት። ይህም ዓመቱ ዞሮ መጣ፤ ብራ ሆነ የሚል ትርጓሜ ያለው ነው።

አስተያየቷን ለአዲስ ማለዳ ያካፈለችው ሌንሴ አያና፤ ነዋሪነቷ በአዲስ አበባ በመሆኑ ኢሬቻን ለማክበር በየዓመቱ ቢሾፍቱ እንደምታቀና አስታውሳለች። የኢሬቻ በዓል የምትናፍቀውና የምትወደው ክብረ በዓል መሆኑንም ለአዲስ ማለዳ ስትናገር፤ በኢሬቻ ሰበብ ቤተሰቦቿን ለማግኘት፣ ከተራራቁትና ከራቀቻቸው ጓደኞቿ ጋር ለመሰባሰብና ለመገናኘት እንደምትችልም ነው የጠቀሰችው።

ታድያ ሴቶች በበዓሉ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ የላቀ እንደሆነ፤ የሚሰጣቸው ክብርም በዛው ልክ መሆኑን አንስታለች። እንደውም ከዘመነኛው የሴቶች መብት ጋር በተገናኘ የሚታዩ የአስተሳሰብና የአመለካከት ክፍተቶች አገር በቀል በሆነው የገዳ ስርዓት እንደሌሉ፤ ይህም የሴቶችን መብት እንዲሁም ሴቶችንም በማክበር ረገድ የገዳ ስርዓት ትልቅ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው ስትል ገልጻለች።

ከኢሬቻ ማግስት
ኢሬቻ በኦሮሞ እምነት የሚከበር የአንድ ቀን በዓል ብቻ ሳይሆን ብዙ ማኅበራዊ ፋይዳ አለው። የታሪክ ተመራማሪው ዓለማየሁ እንደጠቀሱት ደግሞ አራት ዋና ዋና ክስተቶች በዓሉን ይከተላሉ። ቀዳሚው በክረምቱ የወንዞች ሙላት ምክንያት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተ ዘመዶችና ልዩ ልዩ ጎሳዎች የሚገናኙበት በዓል ነው፤ ኢሬቻ። ብዙ ጊዜ ጋብቻ ሲደረግ በጎሳ መካከል ስለሚሆን በጋብቻ የተዛመዱ ቤተሰቦች ከወንዝ ወዲያና ወዲህ ስለሚሆኑ፤ የወንዙ መጉደል የብስራት ዜና ነው። በዓሉ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ተደርጎ ስለሚቆጠርም ‘መልካም አዲስ ዓመት’ የሚል የመልካም ምኞት መግለጫም ኢሬቻን ተከትሎ ይጎርፋል።

ሌላው ደግሞ የኦሮሞ አባቶች ከዋርካ ሥር ተቀምጠው የሕግ ጉዳዮችን ማየት የሚጀምሩት ከኢሬቻ በኋላ ነው። አንዳንድ ቦታ በዓሉን ‘ የችሎት መክፈቻ’ የሚሉት ሲሆን፤ በዚህ የተነሳ ነው። መደበኛ የሚባሉ ችሎቶች በክረምቱ ወር ተዘግተው ሚከፈቱት የብራ ወር መግቢያ ላይ ነውና።
ሦስተኛው ከብቶች ጨዋማ ውሃ የሚፈልጉበት ወቅት ነውና ይህን የሚያገኙበት ነው። ወደ ሆራ ስምሪት የሚያደርጉበት ነው ይባላል። ይህም ለከብቶች መራባት የሚጠቅም መሆኑ ይነገራል።

የመጨረሻው ዋና ኩነት የመተጫጫ ወቅት መሆኑ ነው። አንዱ የኦሮሞ ጸሎት ዘር አብዛልን ነውና ልጃገረዶች እንዲሁም ቄሮዎችም (ያላገቡ ወንድ ወጣቶች) ከዕድሜ እኩዮቻቸው የሚተያዩበትና ለፍቅር የሚተጫጩበት ነው። በዚህ የተነሳ ዓመቱ ዞሮ መምጣቱን የበለጠ የሚያደንቁትና የሚወዱት እነዚህ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ሳይሆኑ አልቀሩም!

ኢሬቻ በሸገር – አዲስ አበባ ታሪክ
አዲስ አበባ የተለያዩ ባሕሎችን ታስተናግዳለች፤ የሁሉም መኖሪያም ነች። ይህች ቻይ እና ሰፊ ከተማ ዋና ከተማ ከሆነችላት ኢትዮጵያ አልፋ የውጪ አገራት ባሕሎችንም ተቀብላ ታስተናግዳለች። እንደ (የፍቅር ቀን) ቫለንታይን ዴይ ዓይነት የውጪ የሆኑ በዓላትን መጥቀስ ይቻላል። ከምንወቅሳቸው ጀምሮ ደስ እስከሚያሰኙና እስከሚያስመሰግኑ ባሕሎች ድረስ፤ አዲስ አበባ የሁሉም ቤት ናት።

ዘንድሮ ደግሞ የኢሬቻ በዓልን አስተናግዳለች፤ ሸገር – አዲስ አበባ። ከአራቱም አቅጣጫ፣ ከርቀትም ከቅርብም የተነሱ የኦሮሞ ተወላጆች ቀድመው በእልፍኟ ታድመዋል። በጫጩ (ዛጎል) ባጌጡ አልባሳት የተዋቡ ሴቶች፣ ‘ሖሮሮ’ ወይም አለንጋ የያዙ ወንዶች ለዓይን አይታጡም፤ እንክብካቤ የማይለያቸው በክብር የሚያዙና በተለያዩ ጌጦች የደመቁ ፈረሶች የአዲስ አበባን አስፋልት መንገዶች በሞገስ ይጋልቡባቸዋል። ለጎብኚዋ መስህብ፣ ለቀኗ ድምቀት ሊሆን የሚችል አዲስ ምዕራፍ ለአዲስ አበባ ተከፍቷል ማለት ይቻላል።

ኢሬቻ ሰፋ ባለ መልኩና እጅግ ብዙ የሚባሉ ተሳታፊዎችን አካትቶ መከበር የጀመረውና ዕድገት ያሳየው ከ28 እና 30 ዓመታት ቀደም ብሎ በሆራ አርሰዲ መሆኑን ዓለማየሁ ይገልጻሉ። ቀደም ብሎ ተቋርጦ ነበር፤ ይህም የሆነው ከአዲስ አበባ ምሥረታ በፊት 1860ዎቹ ምኒልክ እንጦጦ ደርሰው የነበረ ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከዚህ በኋላ በ1979 አዲስ አበባ ተመሥርታ ከተማ እየተስፋፋ ሲመጣ ክብረ በዓሉም እየቀነሰና ከመሃል እየተገፋ መውጣቱን ይገልጻሉ። ዓለማየሁ ጨምረው አሉ፤ “ገበያም ከእንጦጦ ተነስቶ የአሁኑ አራዳ ጊዮርጊስ (ቢርቢርሳ)፤ ከዛ በኋላ በጣልያን ጦርነት ጊዜ ድጋሚ በጣልያን ተነስቶ መርካቶ ተመሥርቷል” ብለዋል።

ይህ የከተማ መስፋፋት ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የተነሱ ነገሥታት የገዳ ስርዓትን ይጫኑ ስለነበር ወይም ነገሥታቱ ስርዓቱ እንዲጠናከር ባለመፈለጋቸው፤ ከዛው ጋር ተያይዞ ኢሬቻ እንደታገደም አንስተዋል። በዘውዳዊው ስርዓት ኢሬቻ ቢከለከልም ወጣቶቹ በጥምቀትና በጃንሜዳም ተቃውሞ ያሰሙ እንደነበር ዓለማየሁ አያይዘው አውስተዋል። አዲስ አበባ ሥያሜዋ ሸገር እያለ፤ ኢሬቻ “ሆራ ፊንፊኔ” የተባለ ቦታ፤ (አሁን ፍል ውሃ ያለበት አካባቢ ወንዝ ነበር) ላይ ይከበር ነበር ሲሉም ያወሳሉ።

ሰለሞን ደግሞ በበኩላቸው፤ የቦረና ኦሮሞዎች ወደ ኢሬቻ ሲሔዱ የሚዘምሩት ዝማሬ ውስጥ “ወደ ፊንፊኔ እንሔዳለን፤ ኼደንም ኢሬቻ እናደርጋለን” የሚል ስንኝ መገኘቱን አውስተዋል። ይህም ምንአልባትም ከጥንትም ፊንፊኔ የኢሬቻ ክብረ በዓል ማዕከል ሳትሆን እንደማትቀር ማሳያ ነው።
“ምክንያቱም…” አሉ ሰለሞን፣ “ ምክንያቱም ‘ ኦዳ ነቤ’ የሚባል ዱከም አካባቢ የሚገኝ የቱለማ ማዕከል ነው፤ ቱለማ ደግሞ ለኦሮሚያ ምሥራቁን፣ ምዕራቡንና ደቡቡን የሚያገናኝ ማዕከል ነበር። ምንአልባት ከሁሉም አካባቢ መጥተው ሳያከብሩ አይቀሩም የሚል ጥናት [ዓለማየሁ ኃይሌ የተባሉ ሰው የጻፉት] አለ።” ብለዋል። ይህም በእንዲህ እንዳለ ታድያ ኢሬቻ በቱለማዎች የካ፣ ጉለሌና ገላን ያከብሩ እንደነበር በታሪክ ተቀምጧል ብለዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ለኦሮሞ ብሔራዊና ተናፋቂ በዓል እየሆነ መምጣቱን ዓለማየሁ ጠቁመዋል። ይህም የሆነው መንግሥት በማገድና በመከልከል የሚሆን ነገር እንደሌለ በመረዳት “ የእኔ በዓል ነው” ብሎ ኢሬቻን በማክበሩ ነው ይላሉ።
ታድያ ኢሬቻ ተዳክሞ የነበረውን የገዳ ስርዓትን ከወደቀበት ጎትቶ አነስቶ በዓለም መድረክ እስኪታይ ድረስ አብቅቶታልም ባይ ናቸው። የገዳ ስርዓት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም ዩኔስኮ እንዲመዘገብ ያስቻለውም ይህ የኢሬቻ በዓል መነቃቃት ነው ይላሉ።
“ገዳ ሰፊ ስርዓት ነው፤ ኢሬቻ ግን አንዲት መዋቅር ናት። ገዳን ዓለምም ተቀበለው። እናም በዚህ ገዳ የሁሉም ሆነ፤ ኢሬቻ ገና እውቅና አላገኘችም፤ አባቷን ግን አንስታለች” ብለዋል፤ ዓለማየሁ። ታድያ ይህን በዓል ማክበሩ ጥቅሙ ለማኅበረሰብ እርካታ ነው። ባሕልን በቱሪዝም ምንጭነት ካልታሰበ በቀር በገንዘብ የሚተመን አይደለምና፤ የማንነቱ መገለጫ በመሆኑ ሕዝብም ደስ የሚሰኝበት ነው ብለዋል። “ዝማሬው ደግሞ የሰላምና የፍቅር ነውና የሁሉም ነው” ሲሉ አክለዋል።

አዲስ ማለዳ በኦሮሞ የባሕል ማዕከል አግኝታ ያነጋገረቻት ወጣት ሌንሴ፤ በአዲስ አበባ መከበሩ እጅግ እንዳስደሰታት ተናግራለች። ከአዲስ አበባ ለመውጣት በማትችልበት ዓመት ቤተዘመድ መጠየቁ እንኳን ቢቀር በቅርብ በዓሉን ማክበር እንድትችል ዕድሉ እንደተፈጠረላት እንደሚሰማት ጠቅሳለች። “የተወለድኩት ከአዲስ አበባ ውጪ ይሁን እንጂ አዲስ አበባም ያው ቤቴ ናት። እና ኢሬቻ በዚህ በመከበሩ ደስታ ተሰምቶኛል። በአዲስ አበባ የሚካሔደው እንዲሁም በቢሾፍቱም የሚደረገው የበዓሉ ሥነ ስርዓት በሰላም ይጠናቀቃል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ” ብላለች።

ሌንሴ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ መመኘት ከስጋት የመነጨ ነው። ኢሬቻ በየዘመኑ የፖለቲካ መሣሪያ እየተደረገ፣ በዚህም ምክንያት በየጊዜው አገር የመሩ ሰዎችም ስጋት እንዲያድርባቸው ሆኖ ዱላቸውን ሲያሳርፉበት ነበር። ዘንድሮ ከዛ በተለየ መልክ ይከበራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በቅርብ ትውስታ እንኳን ከኹለት ዓመት በፊት በቢሾፍቱ የተከሰተውና የደረሰው አደጋ በዛም የጠፋው ሕይወት የሚዘነጋ አይደለም፤ ሐዘኑም አይረሳም።
እንደ ኢሬቻ ያሉ ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉና አልፎም ሕዝባዊ የሆኑ የበዓላት ክዋኔዎች ከዚህ የጸዱ እንዲሆኑ የሚመከረው አንድም ስርዓቱንና የሕዝብ መገለጫ የሆነውን ባሕል በክብር ለማቆየት ነው። ይህ ስርዓት የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆንም የለበትም ያለችውም ሌንሴም፤ የበዓሉ አክባሪ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ምስጋና እና ስጦታ ማቅረቢያ በሆነው የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ያድርግ ብላለች።

ኢሬቻ አሁን ላይ በአዲስ አበባ መከበሩ ለከተማዋ ማህበራዊ ማተጋብሮችን ለመፍጠርና ለማጠናከር፣ አገርን ለማስተዋወቅም ፋይዳ አለው ያሉት ሰለሞን፤ ኢኮኖሚያው ጥቅሙም ሊዘነጋ አይገባም ብለዋል። ያሳሰባቸውንም ሳናገሩ አልቀሩም፤ “ ፖለቲካ ከተጫነው ባህሉ የእኔ አይደለም የሚለው [ማህበረሰብ/ብሔረሰብ] ባለመቀበል ይተባበረዋል እንጂ የእኔ ነው አይልምና፤ ከፖለቲካ አጀንዳ መራቅ አለበት” ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here