ብትበልጥህስ…ብትበልጪውስ?

0
510

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ፍቀዱልኝና በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2015 የተደረገ ነው የተባለ ጥናትን ላጣቅስ ነው። አዎን! በመካከል አራት ዓመታት ቢያልፉም መረጃው ግን አሁን ድረስ የሚሠራ ይመስለኛል። ጥናቱ ምን አለ? ወንዶች በማሰብ ችሎታ አንደኛ የሆኑ ሴቶች አይማርኳቸውም። ይህ ነገር ምን ያህል እውነት ነው ብዬ ሌላ ጥናት አላደረኩም፤ ከቅርብ ጓደኞቼ ጋር አወራንበት፤ ‘አታውቂም ነበር!’ አሉኝ። ‘ወንዶች እንኳን አዋቂ ሴት ለትዳር ሊመርጡ ሴት አለቃ እንደማይወዱ አታውቂም!?’

ጥናቱ ይፋ በተደረገበት ጊዜ መረጃውን ያወጣው ኢንዲፔንደት የተባለው የዜና አውታር ነው፤ ወንዶች አዋቂ የሆነች እንደውም አዋቂ መሆኗ ብቻ ሳይሆን የምትበልጣቸውን ሴት አይመርጧትም። ጥናቱን ያደረጉት ምሁራን እንዲሁም የጥናቱ ውጤት የተገኘበት አገር ወይም አካባቢ ‘የሴቶች መብት አልተከበረም፣ ለሴቶች ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ እና በዘመን ያልተዋጀ ነው’ የሚባልበት አይደለም፤ ይልቁን በካሊፎርንያ ቡፋሎ የተባለ ዩኒቨርስቲ እና ቴክሳስ ዩኒቨርስቲ በጋራ ያደረጉት ነው።

ጥናቱ ባደረገው ዳሰሳ ተሳታፊዎችን በጽሑፍ መጠይቅ አሳትፏል። አንዱ ጥያቄ በሐሳብ ደረጃ በሒሳብና በእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ከፍተኛ ውጤት ያላቸው እንደውም ከወንዶቹ የበለጠ ውጤት ያላቸውን ሴቶች በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ እንዲያስቡ ተጠየቁ።
ማናቸውም አዋቂ ሴት ችግር ይኖርባታል ብለው አላሰቡም፤ አልከፋቸውምም። ‘እንዴታ! የፍቅር አጋርማ መሆን ይችላሉ’ አሉ። በአንጻሩ በበኩላቸው ከእነዚህ አዋቂ ሴቶች ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር የሚፈቅዱ ከሆነ ተጠየቁ። ይሔኔ ሐሳባቸውን ቀየሩ፤ አዋቂ የሆኑ ሴቶች ምንም ባይጎድልባቸው እንኳ እንደማይመርጧቸው ገለጹ።

ሁሉም ወንዶች በዚህ ይካተቱ ይሆን። አይመስለኝም። አዋቂና ብልህ፣ ብርቱና አስተዋይ ሴቶች በየዘመኑ በልጆቻቸውን በትዳር አጋራቸው ተከብበው በታሪክም ተመዝግበው አይተናል። ግን እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው። አንዳንዶች እንደውም ለስኬታማ ሴቶች ትዳር አለመያዝ፣ ቤተሰብ አለመመሥረትና በትዳር አለመቆየት ምክንያቱ ይህ እንደሆነ ሲጠቅሱ እንሰማለን። የዩኒቨርስቲዎቹ አጥኚዎችም በበኩላቸው ‘ይሔ ነገር እውነት መሆኑን ይበልጥ ለማረጋገጥ በጥናታችን ተጨማሪ ሰዎችን ማካተት ሳይኖርብን አይቀርም’ ማለታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ተናግሯል። ይሁንና ከዚህ የተለየ ውጤት ይገኛል ማለት አይቻልም።

በእውቀት ብቻ ሳይሆን በገቢ መጠንም ወንዶች በሴቶች መበለጥን አይወዱም። አንዳንዴ ሴቶችም መብለጥ የሚፈልጉ አይመስሉም፤ ነገሩ የሁሉም ጥቅም ቢሆንም። በቅርብ የማውቀውን አንድ ታሪክ አጣቅሳለሁ። ሴቲቱ የትዳር አጋሯ የሚሠራበት ድርጅት በገጠመው ኪሳራ የሠራተኛ ቅነሳ ያደርጋል። ታድያ ቤቱ እስካልታወቀ ጊዜ ወይም ባልየው ሌላ ሥራ እስኪያገኝ ድረስ በሚስቲቱ ገቢ ብቻ፣ በእማወራዋ ሊተዳደር ግድ ሆነ።

ሥራ ማጣትና ከሥራ መፈናቀል ሊፈጥር የሚችለው ስሜት የታወቀ ሆኖ የዚህ ሰው ሥራ መልቀቅ ግን እንደ ልዩ ሁኔታ ነው የተስተናገደው። በእርሷ ገቢ እንደሚተዳደር እንዳይታወቅም ጉዳዩ ለዘመድና ቤተሰብ ምስጢር ተደርጓል። እርሷም ባሏ ቤት ሲሆን ከከተማ ወጥቷል፤ ሥራ ፍለጋ ሲወጣ ቢሮ ነው እያለች ትዋሽ ነበር። ግን እርሷ ብትሆንስ ኖሮ ከሥራ የወጣችው ወይ የተባረረችው? ይህን ያህል ምስጢር ይሆን ነበር? አይመስለኝም።

ይህ ነገር በእድሜም እንደዛው ነው። እንደ ፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዕድሜ የምትበልጣቸውን ሴት ያገቡ ወንዶችን የምናውቅ ቢሆንም የተለመደ ግን አይደለም። በእርግጥ በአገራችን የወሊደን ነገር አንስተው ‘እርሷ በወሊድ ሰውነቷ ሲደክምና ስትወዳድቅ እርሱ ወጣትነቱ አብሮት ይቆያልና ትቷት ሌላ ጋር ይሔዳል’ በሚል ሐሳብ የሚከራከሩ አሉ። ልምዱ በውስጣችን የኖረ በመሆኑ ምክንያቱን ሳናውቅ ‘አይ! በዕድሜማ የሚበልጠኝ ነው መሆን ያለበት!’ የምንል ሴቶችም ጥቂት አይደለንም።

የምወደውና ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ካለ እየፈለኩለት ያለ ሐሳብ አለ፤ ‘ሴት በለጋ ዕድሜዋ የምታገኘውን ዕይታ ወንዱ በእርሷ ላይ ቢያንስ 15 ዓመት ከኖረ በኋላ ነው የሚያገኘው› የሚል። ይህ በመሆኑም በዕድሜም ቢሆን ወንዶች የሚያንሷቸውን ይመርጣሉ፤ ሴቶችም የሚበልጧቸውን። ብቻ! በዛም አለ በዚህ! በወጥ ቤት ሙያ እና በልጅ አስተዳደግ ችሎታ ካልሆነ በቀር፣ በምንም ይሁን ወንዶች (ብዙ ወንዶች) የምትበልጣቸውን ሴት አይመርጡም። ለምን እንበላቸው ይሆን?
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here