በጋምቤላ በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የወሊድ መቆጣጠሪያ ተጠቃሚዎች ቁጥር በ13 በመቶ ቀነሰ

0
805

በጋምቤላ ክልል ባለፉት ኹለት ዓመታት ሲከሰቱ በነበሩ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የጤና አገልግሎቶችን ባግባቡ ተደራሽ ለማድረግ ባላመቻሉ ከኹለት ዓመት በፊት 33 በመቶ ደርሶ የነበረው የወሊድ መቆጣጠሪያ ሽፋን በ13 በመቶ በማሽቆልቆል 20 በመቶ ደረሰ።

በፀጥታ መደፍረስ አማካኝነት በከተሞች እና በወረዳዎች መሠራት የነበረባቸው የሥነ ተዋልዶ ሥራዎችን እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለማከናወን አለመቻሉ መሰረታዊ ምክንያት ይሁን እንጂ፣ የተለያዩ ችግሮች ለሽፋኑ መቀነስ ምክንያት እንደሆኑ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ካን ጋልዋክ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ የወሊድ መቆጣጠሪያን መጠቀም እንደ ነውር የሚታይ መሆኑ የወሊድ መቆጣጠሪያን ለመጠቀም ያላቸው ፍላጎት ዝቅተኛ ነው ተብሏል። በተጨማሪም በማህበረሰቡ ዘንድ ብዙ ልጆችን መውለድ እንደ መልካም ልምድ ይታያል ያሉት ካን፣ በአማካይ አንዲት እናት ከ6 በላይ ልጆች እንደምትወልድ ተናግረዋል።

የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን መጠቀም ልምድ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎም በክልሉ የኤች. አይ. ቪ ኤድስ ስርጭት 4.7 በመቶ መድረሱን ኃላፊው አረጋግጠዋል። ክልሉ ከኢትዮጵያ በኤች. አይ. ቪ ኤድስ ስርጭት ቀዳሚ ነው ያሉ ሲሆን፣ ስርጭቱን ለመቀነስ የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉም ብለዋል። የኤች. አይ. ቪ ኤድስ ምርመራ ዘመቻዎችን በማዘጋጀት ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ዜጎችን መድኀኒት ለማስጀመርም እየተሠራ ነው ብለዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድም ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት የሚፈቀድ ሲሆን ይህም ሴቶች እና ህፃናት ለተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደሚዳረጋቸው ካን ገልፀዋል።

የግንዛቤ ለውጥ ለማምጣት ወንዶችንም ጭምር የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እና ሚስቶቻቸውን እና ልጆቻቸውን ወደ ጤና ተቋማት በማምጣት የወሊድ መቆጣጠሪያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ሥራዎችን ማከናወን መጀመሩንም ተናግረዋል።

በክልሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ በወሊድ መቆጣጠሪያ አማራጮች ላይ በስፋት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ብቻ መሆኑን ካን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2019 ከ15 እስከ 19 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 38 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ ማግኘታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ ሕዝብ ፈንድ ሪፖርት የሚያሳይ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የፈለጉትን ዓይነት ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ መጠቀም የቻሉት 62 በመቶ ሲሆኑ ያገኙትን የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶች የሚጠቀሙ ደግሞ 40 በመቶ ናቸው። ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ ይፋ የተደረገው ሪፖርቱ በተመሳሳይ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 22 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በአንፃሩ ለወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎቶች ተደራሽ እንዳልሆኑ አመልክቷል።

የጋምቤላ ክልል አማካይ የውልደት መጠን 5.3 ሲሆን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሰረትም የክልሉ የሕዝብ ቁጥር ከ450 ሺሕ በላይ እንደደረሰ ያሳያል። የሕዝቡ ቁጥር ትንሽ ቢሆንም የክልሉ የሕዝብ ብዛት በክልሉ ያለውን ኢኮኖሚያዊ አቅም ያገናዘበ ሊሆን ስለሚገባው ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራበታል ሲሉ ካን ይሞግታሉ።

ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር መጨመር በመጪዎቹ ዓመታት ከሰሃራ በታች ለሚገኙ አገሮች ጥራት ያለው የትምህርትና የጤና አገልግሎት ማቅረብን ከባድ ያደርገዋል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ ሕዝብ ፈንድ ሪፖርት ጠቁሟል። ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮች የውልደት ምጣኔ በአንዲት እናት 5.1 ልጆች ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ያላቸውን የወሊድ ምጣኔ በተሻለ መቀነስ እንደቻሉ፣ ዓመታዊ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ምጣኔያቸው እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2018 ባሉት ጊዜያት ወደ 2.5 በመቶ መውረዱን ሪፖርቱ ያስረዳል።

እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2020 ድረስ የኢትዮጵያ ዝቅተኛው የመውለጃ ዕድሜ በአማካይ 29.7 እንደሚሆን እና የእድሜ ጣሪያ ለሴት 68 እና ለወንድ ደግሞ 64 ዓመት መድረሱንም ሪፖርቱ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 107.5 ሚሊዮን እንደደረሰና ከ15 እስከ 64 ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ከጠቅላላው ሕዝብ 56 በመቶ እንደሚሆኑ፣ 40 በመቶ የሚሆኑት ከዜሮ እስከ 14 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ፣ 65 ዓመትና ከዚያ በላይ የኖሩ የአራት በመቶ ድርሻ እንዳላቸውም በሪፖርቱ ተካቷል።

በክልሉ አንድ ጠቅላላ ሆስፒታል፤ አራት መደበኛ ሆስፒታሎች፤ 32 ጤና ጣቢያዎች እና ከ100 በላይ በሚሆኑ የጤና ኬላዎች የወሊድ መቆጣጠሪያ ይሰጣል የተባለ ሲሆን ለቁጥሩ መቀነስ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው የባህል ተፅዕኖ እና የግንዛቤ እጥረት በምክንያትነት ተነስቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here