የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የአለባበስ ሕግ ይፋ ሊደረግ ነው

0
841

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የአለባበስ ስነምግባር ደንብን ለመወሰን በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚኒስቴር የተጠናው ጥናት ተጠናቆ ከጥር 2012 ጀምሮ ይፋ ሊደረግ ነው።

ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መደበኛ ተብሎ በጥናት የሚረጋገጠውን አለባበስ፣ ሀይማኖታዊ አለባበስ እና ባህላዊ አለባበሶችን ይደነግጋል የተባለው ይህ መመሪያ እስከዛሬ በየዩኒቨርሲቲው ተበታትኖ የሚገኘውን የተማሪዎች መተዳደሪያ ደንብ ይተካል ሲልም ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
‹‹በርካታ ተማሪዎች ሥነ ምግባር የጎደለው አለባበስ በመጠቀም መማር ማስተማሩን ሲያውኩ ነበር›› በማት ለአዲስ ማለዳ የገለፁት የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደቻሳ ግሩም ‹‹በተለይም ፀጉራቸውን አንጨባረው የሚመጡ በርካታ ወንድ ተማሪዎች በየዩኒቨርስቲው ማየት የተለመደ ነው›› ሲሉም ገልፀዋል።

በአዲሱ መመሪያ መሰረትም የፓርቲ አርማ ያለበት ልብስ እና ለግጭት የሚዳርጉ የተለያዩ አለባበሶችን ለብሰው የሚመጡ ተማሪዎችን የሚገድብ እና ችግሩንም የሚፈታ እንደሆነ ተናግረዋል።

ተማሪዎች በመማሪያ ክፍሎች፣ በመጻሕፍት ቤቶች፣ በምግብ፣ በመኝታና በመዝናኛ እና በጤና አገልግሎት መስጫዎች በጋራ እንደመገልገላቸው የግልም ሆነ የጋራ ባህርያትና ድርጊቶች በመማር ማስተማር ሂደትና በማህበራዊው ደህንነትና ሕልውና ላይ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል ሲሉ ተናግራዋል፡፡

ይህም በመሆኑ የተማሪዎች የትምህርት እንቅስቃሴና የማህበራዊ አኗኗር ዘይቤ በደንብና በሥርዓት ሊመራ ስለሚገባው፣ ተማሪዎች ሥርዓቱን ጠንቅቀው በማወቅ እንዲመሩበትና እንዲገለገሉበት እንደሚገባ በመታመኑ በጥናት ላይ የተመሰረተ መመሪያ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ኃላፊው አስታውቀዋል። የትምህርትንና የማህበራዊ ኑሮ አገልግሎትን ሥርዓት በአግባቡ ከተጠቀሙ ተማሪዎች የግልና የጋራ ዓላማዎቻቸውን እውን እንዲያደርጉ ሕጉ ይረዳቸዋል ይላሉ ደቻሳ።

የመማር ማስተማሩ ሂደትም ሆነ የተማሪዎችና የዩኒቨርቲው ማኀበረሰብ መልካም ግንኙነት በተማሪዎች አሉታዊ ባህሪ እንዳይደናቀፍ ተማሪዎችን በመጠበቅ፣ በማረም እና በመከላከል ጤናማ የመማር ማስተማር አካባቢ ሁኔታ ለመፍጠር እንዲቻል እና የአካዳሚ ነፃነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው የተቋቋመለት ዓላማ እንዲሳካ ገዢ ህጎችና ደንቦች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ይህ የተማሪዎች የሥነ ሥርዓት ደንብ ሕግ እንዲወጣ መደረጉን ተቋሙ አስታውቋል።

በ2002 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያወጣው የተማሪዎች የሥነ ሥርዓት ደንብን አዲሱ መመሪያ ለግብአትነት እንደተጠቀሙበትም ታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲን ጨምሮ የተለያዩ ዩኒቨርሲተዎች የሚገለገሉባቸው የተማሪዎች መተዳደሪያ ደንቦች የተማሪዎች አለባበስ ስነ ምግባርንና ሕግን የማይቃረን፣ መልካም ግንኙነትን የማይረብሽ ተገቢ ስርዓት የተከተለ ሊሆን እንደሚገባ ቢደነግጉም፣ ምን ዓይነት አለባበስ፣ የፀጉር አቆራረጥና ሌሎችም የሥነ ምግባር መርሆች በዝርዝር ባለመቀመጣቸው አፈጻጸም ላይ ችግር እንደነበረባቸው የገለጹት ደቻሳ የአሁኑ ሕግ በነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ጥርት ባለ መልኩ መውጣቱን ያስረዳሉ።

እስከዛሬ በዩኒቨርስቲዎች በነበረው የተማሪዎች ደንብ መሰረት፣ ተማሪ ጥፋት ፈጸመ የሚባለው በዩኒቨርሲቲው፣ በሰራተኞችና በተማሪዎች መደበኛ እንቅስቃሴና ስራ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጣልቃገብነት፣ መልካም ግንኙነትን የሚጥስ ወይም ዩኒቨርሲቲውን የሚጎዳ ድርጊት ሲፈጸም ነው።

በአዲሱ ሕግ ግን ቅጣት የሚበይነው በአገሪቱ ሕግ ጥፋት ወይም የወንጀል ድርጊት ተብለው በተቀመጡ መመሪያዎች ሳይሆን ራሱ ባስቀመጣቸው የቅጣት መስፈርቶች መሆኑን ከተቋሙ ለመረዳት ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here