ኢትዮ ቴሌኮም እስከ 23 በመቶ የሚደርስ የደሞዝ ጭማሪ አደረገ

0
1192

በኢትዮጵያ ካሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሰው ኀይል ከሚቀጥሩ ተቋማት አንዱ የሆነው እና ከ 15ሺሕ በላይ ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ኢትዮ ቴሌኮም ለሠራተኞቹ እስከ 23 በመቶ የሚደርስ የደሞዝ ጭማሪ አደረገ። የቴሌኮሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ባሳለፍነው ሳምንት ለሠራተኞች በላኩት የውስጥ ማስታወሻ ቴሌኮሙ ጭማሬውን እንዳፀደቀው አስታውቀዋል።

በየዓመቱ ከአስር በመቶ በላይ የደመወዝ ጭማሬ የማድረግ ልምድ ያለው ቴሌኮሙ፣ በዚህ ዓመት ያደረገው የደሞዝ ጭማሪ መጠን ግን ከተለመደው መጠን ከፍ ያለ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሠራተኞች ተናግረዋል።

መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት የቴሌኮሙን ኢንዱስትሪ ለግሉ ዘርፍ ክፍት ለማድረግ መወሰኑን ተከትሎ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ሲሠራ የቆየው ቴሌኮሙ፣ በተደጋጋሚ በሚመጣው የውድድር መድረክ ከምንም በላይ መወዳደሪያዎቹ ሠራተኞቹ እንደሆኑ መግለጹ ይታወቃል።

በ2011 የበጀት ዓመት ማገባደጃ ላይም የመኖሪያ ቤት እና የተሸከርካሪ ብድር ቢሊዮኖችን ፈሰስ በማድረግ ከተለያዩ ባንኮች ጋር በገባው ውል መሰረት ለሠራተኞቹ ማመቻቸቱ ይታወቃል። በተመሳሳይም የመኖሪያ ቤት አበል ክፍያን ባለፈው በጀት ዓመት መጨመሩ ይታወሳል። በተያዘው ዓመትም የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የ3 ወር ደሞዝ ጉርሻ መስጠቱንም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሠራተኞች ተናግረዋል።
ቴሌኮሙ 15 ሺሕ 646 ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን የሴት ሠራተኞች ቁጥር 28 በመቶ እንዲሁም ወንድ ሠራተኞች 72 በመቶውን ይይዛሉ። የቴሌኮሙን መሰረተ ልማት የሚጠብቁ 18 ሺሕ ቋሚ የጥበቃ ሠራተኞችም አሉት።

በ2011 የበጀት ዓመት መባቻ ላይ እስከ 50 በመቶ ድረስ የታሪፍ ቅናሽ ያካሔደው ቴሌኮሙ፣ በበጀት ዓመቱ 36.3 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ገቢዎች የሰበሰበ ሲሆን 98.3 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከዓለም ዐቀፍ አገልግሎት ገቢ ተሰብስቧል። ከዚህ ውስጥም ያልተጣራ ትርፍ 24.5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸርም የ5.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ለዓመታት ያልተከፈለ 4.7 ቢሊዮን ብር ግብርን ጨምሮ በአጠቃላይ 16.2 ቢሊዮን ብር ግብር መክፈሉንም ከወራት በፊት አስታውቋል።

የኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 43.6 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች 41.92 ሚሊዮን፣ የዳታና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 22.3 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ስልክ 1.2 ሚሊዮን እንደሆኑ ታውቋል። በአጠቃላይ የቴሌኮም ተደራሽነት 44.5 ደርሷል።
አንድ መቶ ሃያ አምስት ዓመታት ዕድሜ ያለው ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል ለማዛወርና ሌሎች የውጭ የቴሌኮም ኩባንያዎች ገብተው እንዲሠሩ የማድረግ ሥራውን በማስመልከትም፣ የገንዘብ ሚኒስቴር በሳለፍነው ሳምንት በሰጠው መግለጫ ዓለማቀፍ አማካሪ ድርጅቶችን በመቅጠር ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

የቴሌኮሙን ከፍተኛ ድርሻ መንግሥት ይዞ ቀሪውን ወደ ግል ባለቤትነት ለማዞር መታሰቡን እና ይህንንም ለመወሰን ምክንያቱ ቴሌኮሙ ገና የዓለማቀፍ ተወዳዳሪነት ደረጃ ላይ አለመድረሱን ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም የቴሌኮሙን ድርሻ ለመሸጥ ከቀረቡት አማራጮች መካከል 49 በመቶ የሚሆነውን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረግ አንዱ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም የተወሰነው በመንግሥት አደራ ተቀምጦ የካፒታል ገበያ በሚጀመርበት ወቅት ለሕዝብ ይቅረብ የሚለው ነው።

ኹለተኛ አማራጭ ሆኖ የተያዘው በመንግሥት እጅ እንደሚቆይ ከተነገረው 51 በመቶ ላይ የተወሰነውን የካፒታል ገበያው ወደ ተግባር ሲገባ ለሕዝብ የሚቀርብ ይሁን የሚለው ሲሆን ቀሪ 49ኙ ግን ለባለሃብቶች የሚሸጥ ይሁን የሚለው ነው።

የአክሲዮን ገበያውን ለማቋቋም መንግሥት ሥራ የጀመረ ሲሆን በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት ወደ ሥራ ለማስገባት ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here