በአርማጭሆ ከአንድ ሺ አምስት መቶ በላይ ሰዎች በአንድ ወር ውስጥ ተፈናቀሉ

0
620

በማዕከላዊ ጎንደር ታች አርማጭሆ የሚገኙ ነዋሪዎች ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ድንገት ወደ አካባቢው እየመጡ በሚፈፅሙት ጥቃት እና አልፎ አልፎ እየታየ ባለው የተደራጀ ዘረፋ አማካኝነት ከአንድ ሺ አምስት መቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን በመተው ተፈናቅላዋል፡፡
እምሩ ባንተይሁን የተባሉ አንድ የወረዳው ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተለመዱ እየሆኑ የመጡት እነዚህ ተግባሮች በነዋሪው ዘንድ ከፍተኛ ስጋት የፈጠሩ ሲሆን አራት የተለያዩ ሰብሎችን የያዙ መኪኖችም ሰብላቸው ተዘርፎ መኪናዎቹ መገኘታቸውንም ይናገራሉ፡፡

‹‹በተለያየ ወቅት መጨመር እና መቀነስ እያሳየ የሚመጣው ጥቃት በተለይም በድንገት በመሮሪያ ቤቶች ላይ በሚሰነዘሩ ጥቃቶች በሰው ህይወት ላይ ጥፋት ማምጣት ሲጀምር ያለን አማራጭ መሰደድ ነው›› ያሉት እምሩ ‹‹ችግሩ ከወረዳው የጸጥታው ኃይሎች በላይ መሆኑ ደግሞ ስጋታችንን ከፍ አድርጎታል›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸው የታች አርማጨሆ ወረዳ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አብዱልቃድር የሱፍ እንደገለጹት፣ ‹‹በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ችግር እንደነበር እሙን ነው፤ በዛም ሳቢያ በርካታ የአካባቢው ሰዎች ጥቃቱን በመፍራት አካባቢያቸውን ለቀው ተሰደዋል እነሱም ቢሆኑ በመመለስ ናቸው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት መጋቢት 2011 ላይ በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሮ በዞኑ 50 ሺሕ ተፈናቃዮች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የዞኑ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው አብዛኞቹም ተፈናቃዮች አርሶ አደሮች ሲሆኑ ሦስት ሺሕ የሚደርሱ የመንግሥት ሠራተኞችም ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውንና እነዚህንም እስከ ነሃሴ 2011 እንዲመለሱ መደረጉን የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መንበሩ አውደው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከጳጉሜ 3/2011 ጀምሮ በአካባቢው እንደገና ባገረሸው ግጭት ሳቢያ በታች አርማጨሆ ወረዳ መፈናቀሉ መከሰቱን መንበሩ ተናግረዋል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተመሳሳይ የፀጥታ ችግር ያለባቸው ምሥራቅ ደምቢያ፣ ምዕራብ ደምቢያ፣ ጭልጋ ቁጥር አንድ፣ ጭልጋ ቁጥር ሁለት፣ አይከልና አርማጭሆ አካባቢዎች መሆናቸውንም አክለው ገልፀዋል፡፡

በ2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 4 ሺህ 361 ቤቶች በግጭቱ የተቃጠሉ ሲሆን፣ ተፈናቃዮቹን መልሶ ለማቋቋም የዞኑ አስተዳደርና የክልሉ መንግሥት በጋራ በመሆን የተቃጠሉ ቤቶችን መልሶ ለመገንባትም ቆርቆሮና ሚስማር የክልሉ መንግስት አቅርቦ ቤቶቺም ሙሉ ለሙሉ ተጠናው ነዋሪዎች መረከባቸውንም መንበሩ ገልጸዋል፡፡

አሁን በተፈጠረው ገጭት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደቀዬአቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩንም የወረዳው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አብዱልቃድር ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡

መስከረም 16/2012 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በታች አርማጭሆ ወረዳ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 3ሺህ 555 የብሬን ጥይት በቁጥጥር ስር መዋሉን የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ አስታውቋል፡፡ እነዚህ መሳሪያዎች የአካባቢውን ሰላም ለማወክ በዳንሻ በኩል ወደጎንደር ሲገቡ የተያዙ ናቸው ሲሉ አብዱልቃድር ይናገራሉ፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here