በአንድ ቢሊዮን ብር ገደማ የገበሬዎች ብድር እና ቁጠባ ተቋም ሊመሰረት ነው

0
833

በአማራ ክልል የገበሬ ማኅበራት ያለባቸውን የካፒታል እጥረት ለመፍታት በማሰብ ከአባይ ባንክ 972 ሚሊዮን ብር ብድር በመውሰድ የገንዘብ ቁጠባ ፌደሬሽን ለማቋቋም ከብሔራዊ በባንክ ፍቃድ አገኙ።

የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው፣ የሚመሰረተው ፌዴሬሽን የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና የገበሬ ማኅበራት የሚገጥማቸውን የገንዘብ እጥረት ይቀርፋል።

በመጪው አንድ ወር ውስጥ የምስረታ ሒደቱን አጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል የተባለው ይህ ፌዴሬሽን፣ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለልዑል ተስፋሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና የገበሬ ማኅበራት ትስስር ያለመኖሩ እና የሀገር ውስጥ ገበያ ጠንካራ ተወዳዳሪ አለመሆናቸው ጥምረቱ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል ተብሏል። በነባራዊ ገበያው ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል የካፒታል እጥረት መኖር ደግሞ የችግሩ መንስኤ ሲሆን ለግብርና መሠረታዊ አቅርቦቶች ብድር የሚሰጥ አበዳሪ የገንዘብ ተቋም አለመኖሩ ደግሞ ጉዳዩን የከፋ አድርጎታል ሲሉ ኃይለልዑል ይናገራሉ።

ፌዴሬሽኑ በተለይም አርሶ አደሩ የሚያመርተውን ምርት ተረክቦ ለሸማቹ የማቅረብ እና በዚህ ወቅት አባላቱ የገንዘብ ችግር እንዳያጋጥማቸው የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠሩ ይዞ ከመጣቸው አገልግሎቶች መካከል ነው።

በክልሉ ካሉት 70 ዩኒየኖች መካከል 43ቱ በአመሠራረቱ ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመው ፌደሬሽኑ ለመመስረት የሚያስፈልገውን ሕጋዊ የሆነ እውቅና እንዲሁም የአደረጃጀት መመሪያው ተዘጋጅቶ ስላለቀ በመጪው አንድ ወር ውስጥ ወደ ሥራ እንገባለን ብለዋል።

አያይዘውም እንደተናገሩት የገንዘብ ቁጠባ ፌዴሬሽኑን ከመሰረቱ ዩኒየኖች ባለፈ በውስጡ ላሉት አባላቶች በሙሉ የቁጠባና የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት እድልን የሚፈጠር እንዲሆን በተጨማሪም ለሥራ ማንቀሻቀሻ ከአባይ ባንክ 972 ሚሊዮን ብር ብድር ለማግኘት ሒደት ላይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

እንዲሁም ለአባላቱ ስልጠና የሚሰጥ፤ የተለያዩ ሰነዶች የሚያሳትም ሲሆን ከአካባቢው ለሚገኘው ህብረተሰብ ሰፊ የሆነና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ነው ፌዴሬሽኑ የተቋቋመውም ተብሏል።

እንደ ኢኮኖሚ ተንታኙ ጌታቸው ተክለ ማርያም ከሆነ፣ ይህ ፌዴሬሽን መቋቋሙ ለገበሬው የራሱ የሆነ ጥቅም ይኖረዋል። ነገር ግን ትንንሽ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብዙ አባላትን የሚያሰባስቡ ቢሆንም ከአባላቱ የሚሰበስቡትም ሆነ የሚያበደሩት ብር አነስተኛ በመሆኑ ተለቅ ያለ ካፒታል ለሚፈልጉ ሥራዎች ፋይናንስ ማቅረብ አይችሉም።

‹‹የፋይናንስ ኢንዱስትሪው አሁን ባለበት ሁኔታ ነባር የሚባሉት ማይክሮ ፋይናንሶች እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር የሚያበድሩ ሲሆን ትንንሾቹ ከ50 ሺሕ ብር ያለፈ አያበድሩም›› እንደ ጌታቸው ገለጻ። ‹‹ትንንሽ ነገሮችን ከማበራከት ይልቅ በጋራ ጠንከር ያሉ ተቋማትን ለመፍጠር ቢሰራ መልካም ይሆናል።››

‹‹በተጨማሪም አሁን ያሉት ማይክሮ ፋይናንሶች በክልል ደረጃ የተዋቀሩ ስለሆኑ እንጂ ሁሉም አንድ ላይ የሚጣመሩበት እድል ቢፈጠር በሚፈጥሩት ጠንካራ አቅም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጥቅም ያመጣሉ›› ሲሉ የኢኮኖሚ ተንታኙ ይናገራሉ። ‹‹ከተለመዱት እና በጣም ውስን ከሆኑት የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎቶች በመውጣት አዳዲስ አገልግሎቶችን በፍጥነት ማምጣት ላይም ማተኮር ይኖርባቸዋል።››

በአማራ ክልል ነባር እና በፋይናንስ አቅሙም ትልቅ የሚባለው አማራ ብድር እና ቁጠባ ባንክ ለመሆን ሒደት ላይ መሆኑ ይታወቃል። በክልሉ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ገበሬዎች የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን ተቋሙ ከበርካታ የሀገር ውስጥ የግልና የመንግሥት የገንዘብ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጭዎች ጋር ይሰራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here