ዐቃቤ ሕግን ያስፈራሩት ግለሰብ ፍርድ ቤት ቀረቡ

0
630

በሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች የተፈፀመ የሙስና ወንጀልን የሚያጣሩ ዐቃቤ ሕጎች ጋር በመደወል ምርመራውን እንዲያቋርጡ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በማድረስ እና የዐቃቤ ሕግ ሥራን በማደናቀፍ ተግባር ተጠርጥረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት የቀረቡት የኮሎኔል ጉደታ ኦላና ምርመራ ተጠናቆ እንዲቀርብ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን ውስጥ ፍርድ ቤቱ 7 ተጨማሪ ቀናትን ፈቅዷል።
ፖሊስ የኮለኔል ጉደታ ኦላናን ጉዳይ ኅዳር 10 ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ የነበረ ሲሆን ተጠርጣሪው በቃለ ምሕላ የገንዘብ አቅም እንደሌላቸው አስረድተው መንግሥት የተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ተፈቅዶላቸው ነበር፡፡ ኅዳር 13 በዋለው ችሎት ዐቃቤ ሕግ ይህንን ተቃውሞ ተጠርጣሪው በባለቤታቸው ሥም ባንክ የተቀመጠ ከአራት መቶ ሺሕ ብር በላይ እና ሱሉልታ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ቤት በመሸጥ ከአምስት መቶ ሺሕ ብር በላይ እንዳገኙ የሚገልጽ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡ ተጠርጣሪው በበኩላቸው ከመሬት ሽያጩ የተገኘው ገንዘብ ለሌላ ግንባታ መዋሉን እንዲሁም በባለቤታቸው ሥም ባንክ የሚገኘው ገንዘብም የአደራ ገንዘብ ቢሆንም እሱም እንደታገደባቸው ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ማስረጃ እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቶ እስከዚያው ድረስ በተከላካይ ጠበቃ ፖሊስ በጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ዙሪያ ክርክር እንዲያደረጉ ወስኗል፡፡
የተከላካይ ጠበቆቻቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ቀላል ወንጀል ነው ሲሉ የጊዜ ቀጠሮውን የተቃወሙ ሲሆን፣ ፖሊስ እስከ አሁን ከሰበሰበው ማስረጃ በተጨማሪ ምን ሊያጣራ እንደሆነ ባልገለጸበት ሁኔታ፥ ከሙስና ጋር በተያያዘም ላቀረበው ጥርጣሬ በቂ ማስረጃ ሳይኖረው ሕገ መንግሥታዊው የዋስትና መብታቸው የሚገደብበት በቂ ምክንያት የለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ ከኢትዮ ቴሌኮም የጠየቀበት የሰነድ ማስረጃ እና የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማጠናከር ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አስረድቷል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤትም ምርመራ ተጠናቆ ለተጨማሪ ምርመራ 7 ቀን በመፍቀድ ኅዳር 20/2011 እንዲቀርቡ ወስኖ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here