በዩኒቨርሲቲዎች የግጭቶች ስጋት አንዣቧል

0
881

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ግጭት 3 ተማሪዎች ሞተዋል 31 ቆስለዋል

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶች ሰለባ እንዳይሆኑና ትምህርታቸውን ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መንግሥት ጠየቀ።
ሰሞኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተከሰተ ግጭት የሦስት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ ግጭቶች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይዛመቱ ተማሪዎች ተረጋግተው መማር እዳለባቸው ተጠይቋል።
ዩኒቨርሲቲዎችን የግጭት ማዕከል ለማድረግ እንደታሰበ መንግሥት ቀድሞ ባለው መረጃ የተረዳ መሆኑን ገልጸው ተማሪዎች የአጥፊዎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑና ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ በማለት መልዕክት አስተላልፈው እንደነበር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ኅዳር 13/2011 በሕዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት ተገኝተው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ሊያጋድሏቸው የሚፈልጉ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ “እራሴ ደብዳቤ ጽፌ መልዕክት አስተላልፌ ነበር” ብለዋል።
ይሁንና አሁንም በዩኒቨርሲቲዎች የግጭትና አለመረጋጋት ስሜት ስላለ ተማሪዎች ከግጭት እንዲርቁ ጠይቀዋል። መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ግጭቶችን በውይይትና ድርድር ለመፍታት እየጣረ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የሳይንንና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚንስትሯ ሒሩት ወ/ማሪያም (ዶ/ር) በበኩላቸው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ‹ሴት ተደፈረችና ተሰወረች› በሚል የሐሰት ወሬ ተማሪዎች ሰልፍ እንዲወጡ በማድረግ ግጭት ለመቀስቀስ መሞከሩን አመልክተዋል። በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የመታጠቢያ ቦታዎች አካባቢ ኅዳር 10/2011 በሁለት ተማሪዎች መካከል የተነሳው ግጭት በዕለቱ በፀጥታ ኃይል ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ቢደረግም በማግስቱ ግጭቱ አገርሽቶ ለሦስት ተማሪዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ሚንስትሯ ገልጸዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ “አንዲት ተማሪ በብዙ ሰው ተደፍራለች የሚል ሪፖርት መጥቶ ብዙ ሰዎች ጥቁር ለብሰው ሰልፍ እንዲወጡ ተደርጓል” ያሉት ሚንስትሯ፣ ነገሩ ሲጣራ ግን ተደፈረች የተባለችው ተማሪም ሆነች የዶርም ቁጥር ውሸት ሆኖ መገኙቱን አንስተዋል። በሰመራ ዩኒቨርሲቲም ሴት ተደፍራ ተሰወረች በሚል የሐሰት ወሬ ኅዳር 8/2011 ነውጥ ለማስነሳት ተሞክሯል ያሉም ሲሆን፣ ሲጣራ ግን ልጅቱ ቤተሰቦቿ ጋር ሔዳ መገኘቷን አረጋግጠዋል። በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ነውጥ ለማስነሳት ተመሳሳይ ወሬዎች እየተሰራጩ ተማሪዎችን ሰልፍ እንዲወጡና ወደ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ እየተሞከረ ነው ብለዋል። ይህም መንግሥት በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ለመቀስቀስ በተደራጀ መንገድ እየሔዱ ያሉ አካላት አሉ ለሚለው አንዱ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀትና የአዳዲስ ሐሳቦች ማፍለቂያ ተቋሞች በመሆናቸው ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርትና ለምርምር እንዲያውሉትም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድረ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው የግለሰቦችን ችግር በግለሰብ ደረጃ መጨረስ ሲገባ ወደ ቡድንና ሌላ ቅርፅ እየለወጡ ለጋ ወጣቶችን መጠቀሚያ ማድረጉ ተቀባይነት እንደሌለው በሰጡት መግለጫ አንስተዋል። በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች ስጋት እንዳይገባቸውም ጥሪ አቅርበዋል። በተማሪዎች አቀባበል ወቅት ኅብረተሰቡ ላሳየው ቤተሰባዊ ፍቅር በማመስገን፣ በቀጣይም የክልሉ የተማሪዎች አለኝታ ሆኖ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ታደሰ ቀነዓ (ዶ/ር) “አጠገባችሁ ያለው ተማሪ ወንድማችሁ እንደናንተው ከምስኪን ቤተሰብ የተገኘ ነው” በማለት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትርፍ አልባ ግጭት አላስፈላጊ መሆኑን አመልከተዋል። “ወንድምህን ገድለህ በፀፀት አለንጋ እየተገረፍክ ዕድሜህን ትማቅቃለህ” ያሉት ፕሬዘዳንቱ፣ ተማሪዎች በጋራ በመሆን ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ እንዲፈልጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ስለመግለጫውና በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ስላለው ሁኔታ ከዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ጠይቀን ያገኘችው መረጃ አንዳመለከተው በዩኒቨርሲቲው ያጋጠመ የፀጥታ ችግር የሌለ ሲሆን፣ የፕሬዘዳንቱ መግለጫ የሁሉም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከግጭት እንዲርቁ ለመምከር የወጣ ነው።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ማራኪ ግቢ እና ዐፄ ቴዎድሮስ ጊቢ ከትላንት በስቲያ በነበረ ሰልፍ 12 ተማሪዎች ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተነግሯል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here