ያሬድ ዘሪሁን ሹመት ይሰጠኛል ብለው እየጠበቁ ነበር

0
811

ፖሊስ በያሬድ ዘሪሁን ላይ የሚያካሒደውን ምርመራ አጠናቅሮ በ14 ቀናት ውስጥ እንዲያቀርብ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።
የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል የነበሩት ያሬድ ዘሪሁን በሰብኣዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወቃል።
ፖሊስ ተጠርጣሪው ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ያቀረበውን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ረቡዕ፣ ኅዳር 12 በዋለው ችሎት መመልከቱ ይታወሳል። በዚህም ወቅት ተጠርጣሪው “የጌታቸው አሰፋ ምክትል ሆኜ 27 ዓመት ሙሉ እንደሠራሁና በእነዚህ ዓመታት ለተፈፀሙ ወንጀሎች በሙሉ ተጠያቂ እንደሆንኩ የቀረበውና በሚዲያም የተስተጋባው ስህተት ነው፤ በዚህ ኃላፊነት ያገለገልኩት አንድ ዓመት ተኩል ብቻ ነው” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡ ያሬድ “ፖሊስ ያቀረባቸው ምስክሮች የሚያስረዱት በተቋሙ ስለተፈፀሙ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች እንጂ እኔ በግሌ ስላደረግኩት ነገር ፖሊስ የሚያቀርበው ማስረጃ የለውም” ያሉ ሲሆን “አሁን ላለው ለውጥም ከፍተኛ አስተዋፅዖ ነበረኝ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሌላ ኃላፊነት እንደሚሰጡኝ ስለነገሩኝ እሱን በመጠባበቅ ላይ ነበርኩ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም “ሊያመልጡ ሲሉ ተያዙ ተብሎ የቀረበው ዘገባ ስህተት ነው፤ ዱከም የኢትዮጵያ ጠረፍ አይደለም፤ ፓስፖርትም ሆነ የውጪ ገንዘብ እጄ ላይ ሳይገኝ ተሰውረዋል ወይም ሊያመልጡ ነው የሚለው ውሸት ነው፤ ተደውሎ ቢነገረኝ እመጣ ነበር አራት ልጆቼ ታግተውብኝ ስለነበር እና ስለተረበሽኩ ራሴን ለማዳመጥ ነው ወደ ዱከም የተጓዝኩት” በማለት ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡
ፖሊስም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተጠረጠሩበት ወንጀል ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራቸው ማስረጃ እንዳለው፣ በሙስናም እንደሚጠረጥራቸው አስረድቷል፡፡ ፖሊስ ተጠርጣሪው ለአምስት ቀን ተሰውረው እንደነበር በማስታወስ አሁንም ዋስትና ከተፈቀደላቸው ማስረጃ ሊያጠፉና ምስክሮችን ሊደልሉ ስለሚችሉ ተጨማሪ ዐሥራ አራት ቀናት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
የተጠርጣሪ ተከላካይ ጠበቆችም ፖሊስ እስከ አሁን የደረሰበትን የምርመራ ደረጃ እና ከዚያ በኋላ የሚያደርገውን ምርመራ ሳያስረዳ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀደለት እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ ይዞ አለመቅረቡን ለፍርድ ቤት ያስረዳ ሲሆን ፍርድ ቤቱ መዝገብ ይዞ አለመቅረብ ጥፋት መሆኑ ገልጾ መዝገቡ ቀርቦ ጉዳዩ በይደር እንዲታይ ወስኖ ነበር፡፡
ጉዳዩ በማግስቱ ኅዳር 13 ቀን በፍርድ ቤቱ የታየ ሲሆን ፖሊስም የምርመራ መዝገቡን አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም በግራ ቀኝ የተደረገውን ክርክር ከግምት በማስገባት ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ አግባብ ነው ሲል ለኅዳር 26/2011 ምርመራውን አጠናቅሮ እንዲቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here