ባለፉት 10 ወራት 21 ነጥብ 29 ሚሊዮን ዶዝ የእንስሳት ክትባት ወደ ውጭ መላኩ ተገለጸ

0
1117

ባለፉት ዐስር ወራት 21 ነጥብ 29 ሚሊዮን ዶዝ የእንስሳት ክትባት ወደ ውጭ መላኩን ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በዚህም ተቋሙ የሚያመርታቸውን ክትባቶች ወደ ጎረቤትና ሌሎች 26 የሚሆኑ የአፍሪካ አገራት በመላክ 800 ሺሕ ዶላር ገቢ እንዳገኘ ገልጿል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ2013 የተላከው በመጠን ያነሰ እንደነበር እና የዘንድሮው የ250 ሺሕ ዶላር ብልጫ እንዳለው አስታውቋል።

ከዚህ ባሻገር የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የአንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የእንስሳት ክትባት በመጪዎቹ አራት ወራት እንዲቀርብላቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ተመላክቷል።

በብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የግዥና ሽያጭ ዳይሬክተር መስፍን ጌታቸው፣ በተለይ ከኒጀር ከፍተኛ ጥያቄ መቅረቡን አንስተው በድምሩ 15 ሚሊዮን ዶዝ የእንስሳት ክትባት እንደታዘዘ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ላለፉት ሦስት ዓመታትም ለኒጀር ስናቀርብ የነበርነው እኛ ነን›› ሲሉ ገልጸውም፣ ከአገሪቱ የታዘዘውን እስከ መስከረም 2015 እናቀርባለን ሲሉ አመላክተዋል።

የአገር ውስጥ ፍላጎትን በተመለከተም፣ አጠቃላይ ላለው የእንስሳት ቁጥር ይህን ያህል የክትባት መጠን ያስፈልጋል የሚል ጥናት የለም ካሉ በኋላ፣ ‹‹ይሁን እንጂ እኛ በምናመርተው ክትባት እና በምናስገባው (በአገር ውስጥ ስለማይመረት) 95 በመቶ ገደማውን የአገር ውስጥ ፍላጎት እንሸፍናለን።›› ነው ያሉት።

አንዳንዴ በአገር ውስጥ በዓመት የሚመረተው 300 ሚሊዮን ገደማ የአገር ውስጥ የክትባት ምርት የማይበቃበት ሁኔታ መኖሩን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህም ከ300 ሺሕ ዶላር ባነሰ ዋጋ ከውጭ ምርቶችን እናስገባለን ብለዋል።

ከውጭ ከሚገባው ምርት አንጻርም የአገር ውስጥ የክትባት ምርታችን 5 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም ቀድሞ ይወጣ የነበረውን ወጪ በአገር ውስጥ ምርት መተካት የተቻለበት አቅም ነው ሲሉ ተደምጠዋል። አንዳንዴ ክትባቶች ባልተጠናና በሌለ ችግር ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡና ይህም ዘርፉን እየጎዳው እንደሆነም ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በሌላ በኩል፣ ተቋሙ መድኃኒት ማምረት መጀመሩንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ‹‹anthelmintic drugs›› እና ‹‹antibiotic drugs›› የሚባሉ የመድኃኒት ዝርያዎች እንደሚመረቱ አንስተው፣ በተለይ 11 ከሚደርሱት መጀመሪያ የተጠቀሰው የመድኃኒት ዝርያ ተመርተው ለገበያ የቀረቡ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ፣ አገሪቱ ለእንስሳት መድኃኒት ግዥ ከፍተኛ ወጪ እንደምታወጣና አሁን እየተመረተ ያለውም የአገር ውስጥ ፍላጎትን የማያሟላ በጣም ጥቂት መሆኑን ገልጸው፣ ብዙ ማምረት ይጠበቃል ነው ያሉት።

ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ጊዜ 23 ዓይነት የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን፣ እንዲሁም የእንስሳት በሽታ መመርመሪያ ኪቶችን እና የእንስሳት መድኃኒቶችን እያመረተ ይገኛል ተብሏል።

ኢንስቲትዩቱ በተለይ በአፍሪካ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ ዘመናዊ የማምረቻ መሣሪያዎች እንደሚያስፈልጉት ጠቅሶ፣ ለዚህም የሚሆን የመሣሪያ ግዥ ለመፈጸም የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንቅፋት እንደሆነበት አመላክቷል።

የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከተመሠረተ 58 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፤ አሁን ላይ በዓመት 350 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት እያመረተ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here