ሕግ እና የእስረኞች አያያዝ

0
1725

እስረኞች ወይም የሕግ ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ጣቢያ እና በማረሚያ ቤት በሚኖራቸው ቆይታ፣ የሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር ከዛም አልፎ ከጥፋታቸው ተምረው የሚወጡ ዜጎች እንዲሆኑ ይጠበቃል። ይህንንም የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑ በሕግ ሰፍሮ ይገኛል።

ከዚህም ባለፈ እስረኞች ቅጣታቸውን አጠናቀው በሚወጡበት ወቅት ከማኅበረሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው እና ሕግ አክባሪ ዜጎች እንዲሆኑ ማስቻል ግድ የሚል ጉዳይ ነው።

አሁን ላይ በአንጻሩ ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ 48 ሰዓት እያለፈ፣ በፀጥታ አካላት ታፍነው ተወስደው ያሉበት እስር ቤት ሳይታወቅ ቀናት እየነጎዱ እና በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች የጤና እክል አጋጥሟቸው በወቅቱ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ሳይችሉ እየቀሩ ነው። እነዚህና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙም በተደጋጋሚ ይስተዋላሉ።

እነዚህ ጥሰቶች በተስተዋሉበት ወቅት በፍጥነት እንዲስተካከሉና መሻሻል እንዲመጣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፤ የመንግሥት አካላትን በተደጋጋሚ መወትወታቸውን ያስረዳሉ።

በተጨማሪ እስረኞች ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደርስባቸው በእኩልነት እንዲታዩ፣ በታራሚዎች መካከል በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሐይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በብሔረሰብ አባልነት፣ በማኅበራዊ ቦታ እና በዜግነት ምክንያት ልዩነት እንዳይደርስባቸው ሕጉ ያዝዛል ያሉት የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ ናቸው።

እነዚህ መብቶች ሙሉ ለሙሉ ተተግብረዋል ለማለት አያስደፍርም የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ ካላግባብ እስራት የሚፈፅሙ እንዲሁም በሌላ በኩል በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በሕጉ ላይ በተቀመጠው የጊዜ ስርዓት መሠረት ለፍርድ ቤት የማያቀርቡ የመንግሥት አካላት ክፍተቶቻቸውን ማስተካከል አለባቸው ብለዋል።

በተጨማሪ እስራት ሲፈጸም ሰብዓዊ ክብርን በሚያረጋግጥ፣ ቁሳዊ እና ሞራላዊ ሁኔታን እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን እና ሌሎች ከዚሁ ጎን ለጎን የወጡ ሕጎችን ሙሉ ለሙሉ በሚያከብር መልክና ሁኔታ መሆን ይገባዋል ይላሉ።

በዓለማችን ላይ በወንጀል የተጠረጠሩ እና ተፈርዶባቸው በሕግ ቁጥጥር ስር ያሉ፣ በድምሩ በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ኢ-ሰብአዊ ከሆነ አያያዝ ለመጠበቅ እና ሰብአዊ መብታቸውን ለማስከበር በርካታ ዓለማቀፍ ስምምነቶች እና ሕጎች ወጥተዋል። ኢትዮጵያም እነዚህኑ ስምምነቶችን በመቀበል እና በሕገ መንግሥት ላይ በማካታት ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።

በተለይም የፌዴራል ማረሚያ ቤት አዋጅ 1174/12 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥትንና ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የወጡ ሕጎችን፣ ሀገሪቱ የተቀበለቻቸውን ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶችን እንዲሁም ዓለም ዐቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የእስረኛ አያያዝ ደረጃዎችን ባከበረ መልኩ ሕግ ማውጣቷ አይዘነጋም። ሆኖም ተግባራዊነቱ አጠያያቂ መሆኑን ብዙዎች ሲያነሱ ይደመጣል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ዓመት ማለትም ከኅዳር 11 ቀን 2013 እስከ ጥር 04 ቀን 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የእስረኞችን አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ በ21 የተመረጡ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ክትትል ማድረጉ ይታወቃል።

ኮሚሽኑ በጎበኛቸው የፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው እንደሆነ ባወጣው ሪፖርት አስረድቷል።

በጣቢያዎቹ ብዙ ሰዎች ያለፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ፣ “በወቅታዊ ሁኔታ” የተጠረጠሩ ናቸው በሚል መታሰራቸውን፣ ከነዚህም አብዛኛዎቹ ምርመራ ሳይጀመርባቸው እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በሕግ ከተቀመጠው ጊዜ በላይ ታስረው እንደቆዩ የሚያመላክቱ አሳማኝ መረጃዎች ቀርበዋል ነው ያለው።

በተጨማሪም፣ በብዙ ፖሊስ ጣቢያዎች ዐቃቤ ሕግ በቂ መረጃ ባለማግኘቱ ምክንያት የ‹አያስከስስም› ውሳኔ የተሰጠባቸው ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት መለቀቅ የነበረባቸው ተጠርጣሪዎች ዋና ተሳታፊ ናቸው ወይም “በሌላ ወንጀል ይፈለጋሉ” በሚል ያለ አግባብ ታስረው እንዲቆዩ ተደርገዋል።

የተለያዩ የፖሊስ ጣቢያ ኃላፊዎች “በወቅታዊ ሁኔታ” ተጠርጥረው የታሰሩ እስረኞች ጉዳያቸው የሚታየው በዞን እና በወረዳ ደረጃ በተቋቋሙ የፀጥታ ምክር ቤቶች በመሆኑ፣ ብዛት ያላቸው ተጠርጣሪዎችን በሕግ ከመዳኘት ይልቅ የፖለቲካ የአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓል ይላሉ፡፡

ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች ከሚገኙት እስረኞች መካከል የተወሰኑት በፖሊሶች በሚያዙበት ወቅት እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ድብደባ የተፈጸመባቸው ናቸው ተብሏል። እንዲሁም ለጊዜያዊ እና ቋሚ የአካል ጉዳት የተዳረጉ እስረኞች መኖራቸውን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የክትትል ቡድን በተመለከታቸው በአብዛኛዎቹ ፖሊስ ጣቢያዎች፤ ተጠርጣሪዎች ንፅሕናቸው ባልተጠበቀ እና በጣም በተጨናነቁ ክፍሎች ለጤና ጎጂ በሆነ መልኩ ይያዛሉ። ከዛም ባሻገር የምግብ እንዲሁም የውሃ፣ የመጸዳጃ እና የሕክምና አገልግሎት አቅርቦት ችግር አለ።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተጠቀሱትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የምርመራ ቡድን በማዋቀር የማጣራት ሥራ መሥራቱን ጠቅሶ ግኝቶቹን በማስተባበል ዝርዝር ምላሽ ስለመስጠቱም ኮሚሽኑ ገልጿል። ችግሮቹ በአፋጣኝ እንዲቀረፉ እና በእስረኞች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ የፖሊስ አባላት ተጠያቂ እንዲሆኑም ጠይቋል።

ኮሚሽኑ በተጨማሪ በሶማሌ ክልል የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ የተወሰነ መሻሻል የታየባቸው ቦታዎች ቢኖሩም፤ አሁንም ብዙ ማሻሻያዎች የሚስፈልጋቸው ጉዳዮችና ቦታዎች መኖራቸውን ተናግሯል።

ኮሚሽኑ መጋቢት 13 ቀን 2013 በጅግጅጋ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች ያደረገውን ፈጣን ክትትል ጨምሮ በተደጋጋሚ ጊዜያት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎችን እና ማረሚያ ቤቶችን በመጎብኘት፣ የእስረኞችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ ክትትል አድርጓል።

ከእስረኞች እና የፖሊስ መምሪያዎች እንዲሁም የማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች እና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የክልሉ የሕግ አስከባሪ እና የአስተዳደር አካላት ጋር ተወያይቷል።

በክትትሉ ከተጎበኙት ቦታዎች በተለይም በጅግጅጋ ከተማ ካውንስል ፖሊስ መምሪያ በተለምዶ ሃቫና ተብሎ በሚታወቀው የተጠርጣሪዎች ማቆያ እና በ04 ቀበሌ አቅራቢያ የሚገኘው የካውንስሉ ማቆያ፤ የተጠርጣሪዎች አያያዝ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ እንዳገኘው የገለፀ ሲሆን፣ እንዲሻሻሉም አስጠንቅቋል።

በእስረኞች ላይ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አሳሳቢ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በተደጋጋሚ የሚያሳውቁ ቢሆንም፣ በእስረኞች ላይ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና አያያዝን በተመለከተ አሳሳቢነቱ አሁንም ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ዘየደ ገብረፃዲቅ ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት፣ ጉባኤው የሠራተኛ እጥረት በመኖሩ ሳቢያ በኢትዮጵያ በሚገኙ በሁሉም ማረሚያ ቤቶች ተንቀሳቅሷል ማለት አይቻልም። ሆኖም በአዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ቦታዎች በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በመንቀሳቀስ ታራሚዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመታዘብ ችሏል ብለዋል።

በዚህም መንገድ ጉባኤው እስረኞች በወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የቀሩ እንዲሁም ፍርድ ቤት መቅረብ ቢችሉም፣ ውሳኔ ያላገኙ እስረኞችን እና በፍርድ ቤት የእስራት ውሳኔ ተበይኖባቸው ያሉ እስረኞች ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ለመታዘብ መቻሉን አስረድተዋል።

ምክትል ሊቀመንበሩ አክለውም፣ ለአብነት ጉባኤው በተያዘው ዓመት ፖሊስ ጣቢያዎችን በጎበኘባቸው ወቅት በእስራት ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ሌሎች ግለሰቦችም ጭምር የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ጉድለት እንዳለበት መታየቱን ጠቅሰዋል። ጉድለቶች እንዲስተካከሉም ለፖሊስ ጣቢያዎች እና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በማሳወቅ ረገድ ያለበትን ኃላፊነት ተወጥቷል ባይ ናቸው።

ምክትል ሊቀመንበሩ አስከትለውም፣ ድንገተኛ ፍተሻ በተደረገ ወቅት አላግባብ ታስረው የነበሩ ሰዎች እንዳጋጠማቸው እና ጉባኤው የታሰሩበትን ሁኔታ ሲጠይቅ፣ ፖሊስ ጣቢያዎች በማድበስበስ አጥጋቢ ምላሽ ሳይሰጡ እስረኞችን የሚለቁበት ሁኔታ አለ ብለዋል።

ጉባኤው የዚህ ዓይነት ድርጊቶች እንዲስተካከሉ በተደጋጋሚ እየወተወተ እንደሚገኝ እና በቀጣይም ከሚያደርጋቸው ድንገተኛ ፍተሻ በተጨማሪ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

ምክትል ሊቀመንበሩ አክለውም፣ ጉባኤው በፍርድ ቤቶች ፍርድ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችንም በጎበኘበት ወቅት አንዳንድ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉ አረጋግጠናል ይላሉ።

ከዚህ አንፃር በማረሚያ ቤቶች ከምግብ ጥራት እና አቅርቦት፣ የሕክምና አገልግሎት አለማግኘት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች እንዳሉ ጉባኤው አረጋግጧል። ክፍተቶች እንዲስተካከሉም ለማረሚያ ቤቶች እና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አሳውቋል።

ጉባዔው በቀጣይ የሠራተኞችን ኃይል በማስተካከል፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ውሳኔ ያላገኙ እና የእስራት ጊዜ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤቶች እና በፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ ሰዎችን አያያዝ እና ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ የሚሠራቸውን ሥራዎች አጎልብቶ እንደሚያስቀጥል ምክትል ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪ፣ በእስረኞች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈፀም ከሚያደርጋቸው ጥረቶች ጎን ለጎን ለማኅበረሰቡ፣ ለመንግሥት እና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በማሳወቅ በትኩረት እንደሚሠሩ ምክትል ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።

የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 18 መሠረት ማንኛውም ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ በሕግ አካላት ተይዞ ሊታሰር የሚችልበት እድል አለ ይላሉ። በሕገ መንግሥቱ መሠረትም የተጠርጣሪዎችን የሰብዓዊ ክብርና መብት መጠበቅ፣ የአካላዊም ሆነ የደኅንነት ነፃነት እንዲጠበቅም ይደነግጋል።

በፖሊስ በኩል ተጠርጣሪዎች ከተያዙ በኋላ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ እና ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ፍርድ ቤቱ በዋስትና እንዲለቀቁ ከወሰነ ፖሊስ ትዕዛዙን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ባለሙያው ጠቁመዋል።

ነገር ግን ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ የሚፈቅድላቸውን ግለሰቦች ፖሊስ ትዕዛዙን ሲጥስ እየታየ እና ለተጨማሪ ማጣሪያ እንዲሁም ይግባኝ እጠይቃለሁ በማለት እስረኞችን የማይለቅበት ሁኔታ እንዳለ አስረድተዋል።

በተጨማሪም፣ ፖሊስ በፍርድ ቤት በኩል ለተጨማሪ ምርመራ በሚል 14 ቀናት የምርመራ ቀናት የሚፈቀድለት ሂደት እንዳለ እና በዚህም ጊዜ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ ፍርድ ቤት እየቀረበ ያጠናቀቀውን እንዲያቀርብ እንዲሁም ያላጠናቀቀውን የደረሰበትን ሁኔታ ማሳወቅ እንዳለበት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ ፍርደኛ ሆነው በማረሚያ ቤት ያሉ እስረኞቹን አያያዝ አስመልክቶ አቅም በፈቀደ መጠን የማኅበራዊ፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የሕክምና አገልግሎት፣ የሥነ ልቦና፣ የምክር አገልግሎት እና ሌሎች አገልግሎቶችን ጭምር ተገቢው ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ሕጉ ይደነግጋል።

እስረኞች በሕግ ጥላ ስር ሆነው ዛቻ፣ ስድብ እና ማስፈራሪያ እንዳይደርስባቸው እና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲሁም ክብራቸው እንደተጠበቀ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ረገድ ማረሚያ ቤቶች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ባለሙያው ይገልፃሉ።

በተጨማሪ፣ ፍርድ ቤት የወሰነባቸውን የእስር ጊዜ ከማጠናቀቅ ጎን ለጎን የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ባለው የአሰራር መመሪያ መሠረት የአመክሮ ጊዜያቸውን የመቀነስ እና እስረኞች የእስር ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ኅብረተሰቡ የሚቀላቀሉበት መብታቸው ሊከበር ይገባል ብለዋል።

ነገር ግን፣ በተቃራኒው ከላይ የተጠቀሱ የእስረኞች መብት ሳይጠበቁ የሚቀሩበት ሁኔታ አለ። ከዚህም ባሻገር፣ የአጃቢ ፖሊስና የተሽከርካሪ እጥረት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በምክንያትነት በማንሳት እስረኞች በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ከሚገኘው ክሊኒክ አቅም በላይ የሆኑ ሕክምና አገልግሎት የማያገኙበት እና መብታቸውም ሳይከበርላቸው የሚቀርበት እድል እንዳለ አመልክተዋል።

ይህ አይነቱ አሠራር ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው የሚሉት ባለሙያው፣ ማረሚያ ቤቶች ሥነልቦናዊና ሰብዓዊ ክብራቸውን በመጠበቅ ረገድ እንዲሁም የታራሚን አቅምና ብቃት በመገንባት ረገድ ኃላፊነትን እንዲወጡ ባለሙያው ጠይቀዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here