መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅከተቆራኘን ወገንተኝነት እንላቀቅ

ከተቆራኘን ወገንተኝነት እንላቀቅ

የሰው ልጅ የራስን ጥቅም የማሳካት ዝንባሌው ሚዛን የደፋ ቢሆንም፣ ቢያንስ ጥቅማችንን የምናሳካበት መንገድ ሌሎችን ሃዘን ላይ የሚጥል መሆን የለበትም። በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም እንዲሉ፣ የአንደኛው ብርሃን ማግኘት የሌላኛውን ሕይወት ካጨለመ የእጃችንን የማንከፍልበት ምክንያት ይኖራል ብለን ራሳችንን አናባብለው።

“ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም” እንዳሉ ከበደ ሚካኤል፣ መልካምነት ከክፋት የተሻለ መሆኑን በተግባር እንፈትነው። በዓለም ዙሪያ ክፉ አድርጎ ደስታው እንደ ጤዛ ተኖ ለዘላለም ያቀረቀረ እንጂ፤ በዘላቂ ደስታ ለዘለለም ቀና ያለ የለም።

መልካም እንሁን። መልካምነት በራሱ ሰላም ነው። ያኔ የደፈረሰው ይጠራል። የራስን ፍላጎት ለማሟላት ነጋ ጠባ እንድንብከነከን በስባሹ ስጋችን ቢያስገድደንም፣ ሌላውን በመጉዳት ያለምነው ዒላማ ግብ ሲመታ ከሚሰማን እርካታ ይልቅ የሌሎችን ክፍተት ብንደፍንላቸው የላቀ እፎይታ እንደሚኖረን እናስተውል።

የእቅዳችን ፍሬያማነት ሌሎችን መጥቀም ቢሳነው እንኳ በራሳችን ላይ እንዲደረግብን የማንፈልገው ነገር በሌሎች ላይ ለማድረግ ባንጣደፍ፣ በዓለም ደረጃ ይቅርና በሰፈርም ጥላቻ ሊፈጠር እንደማይችል አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች። የተጣለብንን አደራ ለመወጣት ከወገንተኝነት አጥብቆ መራቅ ተቀዳሚ የሌለው ተግባር መሆኑንም አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

“ልዩነት ውበት ነው” ብለን ሰብከን ወደተግባር የቀየርነው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ፍካሬያዊ ፍቺውን በተግባር አጥቶ የጡት ነካሾች የስህተት ጉዞ መሆኑ ይግባን። ፌዴራሊዝም ፍካሬ ብቻ የሆነው ሥልጣን ላይ ስንቀመጥ ብሔርተኝነትን የሥልጣን ማስፈጸሚያ ስላደረግነው መሆኑንም ሕሊናችን እንዲያስታውሰን በጥሞና እናዳምጥ።

በአድዋ ላይ ድል ተደርገው በመመለሳቸው ወኔያቸው የሟሸሸው ምዕራባዊያን ድጋሚ ጦራቸውን ቀስረው ቢመጡ እንደማያሸንፉን ስለሚያውቁ፤ በዘር፤ በቋንቋ፤ በሃይማኖት፤ በጎሳ ተሸንሽነን እርስ በእርሳችን እንድንባላ ያሴሩትን እኩይ ተግባር እየፈጸምን መሆኑን እንወቅ።

ሌባ ሀብት ያየበትን እንጂ ባዶ በረት እንደማያንኳኳ ሁሉ፣ ምዕራባዊያኑ በጦርነት ያልተንበረከከች፤ በእምነት የከበረች፤ መልክአ ምድሯ ባልተነካ ሀብት የተመላው ኢትዮጵያ፣ ባደረባቸው ከንቱ ቅናት በራሳቸው ሊያፈርሷት ቢቃትቱም ስላልቻሉ ሕዝቦቿን እርስ በርስ አናክሰው በቀኝ አዙር እራሳችን እንድናፈርሳት ዕቃ ዕቃ ሲጫወቱብን አሜን ብለን መቀበል ይብቃ።

የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ፣ መልካችን ቢለያይም እናት ኢትዮጵያ ያፈራችን አንድ ሕዝብ ነንና በአንድነት መቆሙ የተሻለ መሆኑን አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትሻለች።

መንግሥት በሕዝብ ላይ ችግር ሳይጋረጥ በፊት መፍትሄ የመስጠት ኃላፊነት የተጣለበት ሆኖ ሳለ፤ ሕዝቦች አፋቸውን አውጥተው የድረሱልኝ ሲቃቸውን ሲያሰሙ በሽንገላ መሸኘት መቆም እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

በየወቅቱ እየተጨፈጨፉ ዓመታትን በማስቆጠራቸው የድረሱልኝ ጩኸታቸው የሚያስተጋባው ዜጎች የመንግሥት ጆሮ ሊከፈትላቸው ይገባል። መበልጸግ የሚረጋገጠው የዜጎችን ችግር በመፍታት እንጂ በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሉ በሕዝቡ ችግር ላይ ችግር በመፍጠርና ደም በማፋሰስ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ሰላሟ እንድትመለስ፤ ሕግን ማስከበር በሚመስል ተግባር ንጹሓንን ማሰርና መግደል ይቁም፤ ይህ በማር የተጠቀለለ መርዝ ለሕዝብ ማጉረስ ነውና። ሕዝብ ተግባር ባረጋገጠው መልካም አስተዳዳር እንጂ በመልካም ንግግር ብቻ ነጻነቱን ሊጎናጸፍና እርካታ ሊያገኝ እንደማይችል ይሰመርበት።

ሕይወትን እስከማሳጣት ጫፍ የደረሱ ድርጊቶች ሲከናወኑ ተግባር ላይ የማይውልና ሕግ የሚተላላፉ አካላትን የማይገርዝ ሕግ የተፈጻሚነት ዕድሉ እየሟሸሸ ነውና፣ መስተካከል እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

ኢትዮጵያ ወንጀለኝነታቸው ሳይረጋገጥ ይቅርና ወንጀለኝነታቸው ተጣርቶም ቢሆን ጥፋተኛ ይሰወር የሚል የሕግ ድንጋጌ ባይኖራትም፣ በርካታ ዜጎች ግን ያሉበት አይታወቅም። ሕዝብ በግፍ በሚሰቃይበት አገር ውስጥ ሕጋዊነት አለ የሚል ሽንገላ መቆም እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።

መንግሥት ቆራጥ እርምጃ አለመውሰዱን ተከትሎም ንጹሐን ዜጎች በእምነታቸው፤ በብሔራቸው፤ በቋንቋቸው ምክንያት የሚደርስባቸው ጥቃት እልባት ሳያገኝ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ ችግር ከማንም በላይ የመንግሥትን አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሻ አዲስ ማለዳ ማሳወቅ ትወዳለች።

ሰላም ለማስፍን ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጡ ሰዎች፤ ጋዜጠኞችና ሌሎችን አካላት ወደ እስር ቤት ሲማገዱ ይስተዋላል። ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ሰጥቶ ሐሳብን በነጻ ሲገልጡ ማሸማቀቅ ዴሞክራሲያዊ ናት ከምትባል አገር እንደማይጠበቅ ሊሰመርበት ይገባል። ሰጥቶ መንሳት፤ አይዞህ ብሎ መግፋት ከሕዝብ አስተዳዳሪ አይጠበቅም።

የሕዝብን ነጻነት ለመንፈግ በሥልጣን የተመከተ ፍርድ በመፍረድ ሕዝብን ማታለል ይቁም። ለብሔር ሳይሆን ለአገር የሚጠቅመውን ሥራ እንሥራ። ሕሊናችን በሥልጣን ምርኮ አይውደቅ። ሥልጣናችን ሳይሆን ሕሊናችን እንዲፈርድ እንፍቀድለት። ያኔ ሕሊናም አገርም ሰላሙን አጥቶ አይቅበዘበዝም።

- ይከተሉን -Social Media

ንጹሐንን ወንጅለን ከማሰራችን፤ ለእውነተኛ ድርጊት የኸሰት ፍርድ ከመበየናችን፤ ከሰንም ሆነ ተከስሰን ወደ ፍርድ ቤት ከመቅረባችን በፊት በሕሊናችን ችሎት ፊት ቀድመን እንደምንቆም አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ መልሶ ከኋላ ተከታይ ያደረገንን የትላንት ታሪክ የወደፊት ጉዟችንንም እንዲያደናቅፈው አንፍቀድለት። ትላንት ተፈጠረ በሚባል ክስተት በቦታው ያልነበሩ በርካታ ዜጎች የንዴት መወጫ ሆነው ዛሬያቸው ሲጨልም መፍትሄ በመሆን የድርሻችንን እንወጣ።

ትላንት ጭቆና ደረሰብን የሚሉ አካላት በቦታው ባልነበረ በዛሬው ትውልድ የቂም ቋጠሯቸውን ማወራረድ ርካታ ከመሰላቸው፤ የዛሬው ትውልድ የነገውን እንዲህ የማያደርግበት ምክንያት አይኖርምና አገርን እንደ አገር ለማስቀጠል ይህ ዓይነቱን አሰራር ሳይለመልም ማድረቅ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትሻለች።

ወገንተኝነት ከተላበስን ለምንደግፈውም ሆነ ለምንነቅፈው የማኅበረሰብ ክፍል በነገው ሕይወት ድልድዩ ላይ ድብቅ ጉድጓድ እየቆፈርን መሆኑን ካለፉት ታሪኮች እንማር።

ጉዳትን በጉዳት ለማገገም መጣደፍ ፍጻሜው አገርን ማፍረስ እንጂ አገርን ይገነባል ብሎ ማሰብ የሕልም ሩጫ ስለሚሆን፣ ይህን ድርጊት ማስቆም በቅድሚያ ከመንግሥት ይጠበቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች