ረቡዕ ሰኔ 29 ቀን 2014፤ በሸራተን አዲስ ሆቴል ላሊበላ አዳራሽ ደማቅ ድግስ ተካሂዶ ነበር። ይህም በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለኹለተኛ ጊዜ የተዘጋጀው ‹ክብር ለጥበብ› የተሰኘው መርሃ ግብር ነው። በዚህም መሰናዶ ላይ ከአንጋፋ እስከ ወጣት፣ ከነባር እስከ አዲስ፣ እጅግ በርካታና በበርካታ የጥበብ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሞያዎች ታድመዋል።
ይህ የእውቅና መስጫ መርሃ ግብር፣ ባሳለፍነው ዓመት 2013 ‹ሽልማት ለጥበብ› በሚል መጠሪያ በተካሄደው መሰናዶ፣ የሽልማትና የውድድር ዓይነት ይዘት የነበረው እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታስታውሳለች። ይህም የገንዘብ ሽልማትን ያካተተ ነበር። ዘንድሮ ግን ከዛ ለየት ባለ መልኩ ውድድርም ያልሆነ የገንዘብ ወይም ሌላ ሽልማት የሌለው ይልቁንም የእውቅና መስጠት ዝግጅት ሆኗል።
ይህን ዝግጅት ልዩ የሚያደርገው በመንግሥት የተዘጋጀ ከመሆኑ ባሻገር፣ በተለያዩ ሽልማት ዝግጅቶች ላይ ያልተካተቱ ዘርፎችን ያካተተ መሆኑ ነው። በእለቱም እውቅና ከተሰጣቸው የጥበብ ባለሞያዎች መካከል በኮሜዲ፣ በሰርከስ፣ በውዝዋዜ፣ በፋሽን፣ በሙዚቃ አጫዋችነት (ዲጄ)፣ በቴአትር፣ በሙዚቃ፣ በፊልም እንዲሁም በስዕል ዘር የተሰማሩ ባለሞያዎች ይገኙበታል።
አገር ዐቀፍ ይዘት ያለው ዝግጅቱ፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሠሩና ከተለያዩ ክልሎች የተገኙ የጥበብ ባለሞያዎችንም አመስግኖ እውቅና ሰጥቷል።
አዲስ ማለዳ ዝግጅቱን በሚመለከት ከደራሲት ፀሐይ መላኩ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋ ነበር። ፀሐይ እንዳለችው፣ እንዲህ ያሉ የእውቅና መሰናዶዎች አዳዲስ ባለሞያዎች ጠንክረው እንዲሠሩ የሚያግዝ፣ ነባሮችን ደግሞ የሚያበረታታ ነው።
‹‹እንዲህ ያለው ዝግጅት ሊቀጥል የሚገባ ነው። ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው በአቅሙ፣ በሙያው፣ በዝንባሌው ያገለግላል። ለዛ አገልግሎቱ ደግሞ ዋጋ መስጠት ተገቢ ነው። ያኔ ያ ሰውም ጥረቱ ከተከበረለት የበለጠ ለመሥራት ይነሳሳል። ይህ [እውቅና የመስጠት ዝግጅት] ቀዝቅዞ ነበርና አሁን በማንሰራራቱ ደስ ብሎኛል። ቀጣዩ ትውልድ የሚያየኝና ሥራዬንም የሚያይልኝ አለ ብሎ እንዲሠራ ያደርጋል።›› ስትል ተናግራለች።
በዝግጅቱ ላይ እውቅና ከተሰጣቸው ባለሞያዎች መካከል በየዘርፉ ያሉትን የተወሰኑትን እናውሳ። ኮሜድያን ቤተልሔም ጌታቸው (ቤቲ ዋኖስ)፣ ኮሜድያን ደረጄ ኃይሌ እንዲሁም ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ በኮሜዲ ዘርፍ። አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) እንዲሁም ግርማ ይፍራሸዋ በሙዚቃ ዘርፍ።
በፊልም ዘርፍ ኢላላ ኢብሳ (የሒሩት አባቷ ማን ነው ፊልም አዘጋጅ)፣ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ እንዲሁም ደበበ እሸቱ። በሙዚቃ አጫዋችነት ወይ ዲጄ ዘርፍ ዲጄ ሼሪ እንዲሁም ዲጄ ጆርዳን እና ቤኪ ግዕዝ እውቅና የተሰጣቸው ሆነዋል። በዚሁ ዘርፍ ዳንኤል መላኩ የተባለ ባለሞያም በመድረኩ ተወስቷል። በዲጄነት ሙያ ላይ ተሰማርቶ የነበረው ዳንኤል፤ በ29 ዓመት እድሜው ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው። ለዚህ ወጣት የነበረ ባለሞያም የተዘጋጀውን እውቅና ወላጅ እናቱ ተወክለው ተቀብለዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ፣ አላዛር ሳሙኤል እንዲሁም ደበሽ ተመስገን በቴአትር ዘርፍ እውቅና ያገኙ ናቸው። ከድር አሊ፣ ተመስገን መለሰ እንዲሁም ሀሁ የዳንስ ቡድን በውዝዋዜ፣ በረከት ትዕዛዙ፣ ሰለሞን ታደሰ እንዲሁም ውቤ ዘለቀ (ሰርከስ ጅማ) በሰርከስ ዘርፍ እውቅና ያገኙ ናቸው። ጥበበ ተረፈ፣ ግርማ ወልደሰማያት እና ታምራት ሡልጣን ደግሞ በስዕል ዘርፍ እንዲሁም ዘውዲቱ ከበደ፣ እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ እና ገነት ከበደ ደግሞ በፋሽ ዘርፍ በመድረኩ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ልዩ ተሸላሚዎች ወይም ልዩ እውቅና ተቀባዮች የነበሩ ሲሆን፣ አንጋፋው ድምጻዊ የክብር ዶክተር መሐሙድ አሕመድ፣ የክብር ዶክተር አሊ ቢራ፣ ሳራ አበራ፣ ሳሌም ካሳሁን፣ ፍሬው ቆንጂ፣ መላኩ በላይ (ፈንድቃ) እና ጸጋዬ ደንደና በዚህ ዘርፍ ተካትተዋል።
ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ በመድረኩ የተወሳ ሲሆን፣ ለእርሱም ለሠራቸው ሥራዎች ምስጋና እና እውቅና ተበርክቷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በእለቱ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ የሺሕ ዘመናት ሥልጣኔ እና የአገር በቀል የኪነጥበብና የሥነ ጥበብ እውቀት ባለቤት መሆኗን አውስተዋል። ይህን ብዝኀ ሀብት ተከትሎም በርካታ የጥበብ ባለሞያዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። እንዲህ ጊዜ መጠበቅ ሳያስፈልግ ለጥበብ ሰዎች በየጊዜው እውቅና መስጠት ተገቢና ትክክል መሆኑን አንስተው፤ ያም ሆኖ እንዲህ ያሉ መሰናዶዎች በቋሚነት የመቀጠላቸውን ጥቅምም ጠቅሰዋል። እውቅና ለተሰጣው የጥበብ ባለሞያዎች ሁሉም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስላልፈዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014


