በ2012 ሰማንያ በመቶ የሞባይል ካርድ ሽያጭ ይቆማል

0
1616

ዕቅዱ ሲሳካ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ያህል ወጪ ማስቀረት ይቻላል

ኢትዮ ቴሌኮም በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ የሞባይል ካርድ ሽያጭን ሰማንያ በመቶ እንደሚያስቀር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። በያዝነው ዓመት መጨረሻ ደግሞ ሃምሳ በመቶ የሚሆነው የሞባይል ካርድ ሽያጭ ይቀራል። የሞባይል ካርድ ሽያጭ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ የሚደረገው በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ‹ይሙሉ› የተሰኘው የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ የሞባይል ካርድን ተክቶ አገልግሎት መስጠት ስለሚጀምር ነው።
በዓመት ውስጥ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሞባይል ካርዶች የሚታተሙ ሲሆን፣ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ሃምሳ በመቶ የሚሆነው የአየር ሰዓት ግብይት በ‹ይሙሉ› ሲተካ የሞባይል ካርድን ለማሳተም ይወጣ የነበረውን ወደ ሁለት ቢሊዮን ያህል ብር ማስቀረት ይቻላል ሲሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና የሽያጭ ኃላፊ የሆኑት መሐመድ ሀጂ ተናግረዋል። ይህም በውጪ አገር የሚታተመውን የሞባይል ካርድ ሃምሳ በመቶ ያስቀራል። የዛሬ ዓመት አካባቢ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካርድን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ሐሳብ የቀረበ ቢሆንም በወቅቱ በነበሩ የኢትዮ ቴሌኮም አመራሮች ጋር መስማማት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ይታወሳል። በወቅቱም ባንኩ ለቴሌኮሙ የውጭ ምንዛሬ በቶሎ ባለመፍቀዱ የካርድ እጥረት ለሳምንታት ማጋጠሙ አይዘነጋም።
መሐመድ ምንም እንኳን በ2012 መጨረሻ ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የአየር ሰዐት ግብይት በ‹ይሙሉ› ለመተካት ቢታቀድም ወደፊት ሙሉ በሙሉ የሞባይል ካርድ እንደማይቆምና ከጠቅላላ የአየር ሰዓት ሽያጭ ሀያ በመቶ የሚሆነው በካርድ እንደሚከናወን ገልጸዋል። ይህም በዋናነት በሁለት ምክንያቶች የሆነ ሲሆን አንደኛው የ‹ይሙሉ›ን አገልግሎት ለመተግበር ምቹ ያልሆኑ ቦታዎች ላይ ስርጭቱን ለማዳረስ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የሞባይል ካርድን መጠቀም የተሻለ ምቾት የሚሰጣቸውን ደንበኞች ፍላጎት ለመጠበቅ ሲባል ነው በማለት ተናግረዋል። አገልግሎት አሰጣጡን በተመለከተ ደንበኞች በተንቀሳቃሽ ስልክ አጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ በዩኤስኤስዲና ድረገጽን በመጠቀም አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ። እስካሁን ድረስም ሴፍዌይ፣ ቶሞካና ቃተኛን የመሳሰሉ የንግድ ተቋማት የ‹ይሙሉ›ን አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
የ‹ይሙሉ› አገልግሎትን በባለቤትነት የሚመራው ኢትዮቴሌኮም ሲሆን የገንዘብ ዝውውሩን ለማቀላጠፍ ከተለያዩ የግልና የመንግሥት ባንኮች እንዲሁም ከሄሎ ካሽ ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል። የሄሎ ቤል ሠራተኛ የሆኑት ቴዎድሮስ የ‹ይሙሉ›ን አገልግሎት ከኢትዮቴሌኮም ጋር በመሆን እየሰጡ እንደሆነ ገልጸው ሄሎ ካሽ በዋናነት አገልግሎት የሚሰጠው ለባንኮች እንደሆነና እስከ አሁን ድረስ የሄሎ ካሽ አገልግሎትን የሚጠቀሙት ባንኮች ወጋገን ባንክ፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክና ኢስት አፍሪካ ባንክ እንደሆኑ አክለዋል። በመሆኑም የሄሎ ካሽ አካውንት ያላቸው የባንኩ ደንበኞች የአየር ሰዐት ከኢትዮቴሌኮም አቅማቸው የፈቀደውን የገንዘብ መጠን ያህል ገዝተው መጠቀም ይችላሉ። ቴዎድሮስ ይህ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ላይ ከዋለ ወደ አንድ ወር ገደማ የሚጠጋው ሲሆን፣ አገልግሎቱን የሚጠቀሙ ደንበኞችም የሞሉትን ሒሳብ ዐሥር በመቶ የሚያክል ተጨማሪ የማበረታቻ የአየር ሰዐት እያገኙ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የሞባይል ካርድን ማስቀረት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት የገለጹት ቴዎድሮስ ከነዚህም መካከል የሞባይል ካርድ የሚታተመው በውጪ አገር በመሆኑም በሞባይል ካርድ ፋንታ የሞባይል መተግበሪያን መጠቀም የውጪ ምንዛሬን ያስቀራል ብለዋል። በተጨማሪም የሞባይል ካርድን ወደየቦታው ለማዘዋወር የሚወጣውን ወጪም ያስቀራል የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በአሁኑ ወቅት ከ64 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ተጠቃሚዎች በአገሪቷ ውስጥ ይገኛሉ ከነዚህም መካከል 16 ሚሊዮን የሚሆኑት ኢንተርኔት ይጠቀማሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here