መነሻ ገጽዜናየእለት ዜናበአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች በተለያየ መንገድ ገብተው የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር...

በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች በተለያየ መንገድ ገብተው የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ዜጎች ምዝገባ ሊካሄድ ነው

ዕረቡ ሐምሌ 6 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች በፈቃድም ይሁን ያለፈቃድ ገብተው በመኖር ላይ የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎችን የመመዝገብ ሥራ ከሐምሌ 11 እስከ 25/2014 ድረስ እንደሚያካሂድ የኢፌዴሪ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በተለያየ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ዜጎችን አስመልክቶ ጥብቅ መልዕክት አስተላልፏል።

በመልዕክቱም፤ በተለያዩ የቪዛ ዓይነቶች ወደ ኢትዮጵያ የገቡና ቪዛቸው የሚፀናበት ጊዜ ያለፈበት፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው የሚፀናበት ጊዜ ያለፈበት፣ ምንም አይነት ቪዛም ሆነ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው እንዲሁም፤ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የስደተኝነት ወይም የጥገኝነት ጠያቂ ዕውቅና አግኝተው በከተማ ስደተኝነት በፈቃድም ይሁን ያለፈቃድ፤ በአዲስ አበባ እና በዙሪያው በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች በሙሉ በተጠቀሱት ቀናት ውስጥ ምዝገባ እንዲያከናውኑ አሳስቧል።

ምዝገባውም ዘወትር ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ዘመትር በሥራ ሰዓትና ቀናት የሚከናወን ሲሆን፤ ተመዝጋቢዎች ማንነታቸውን የሚገልፅ ሕጋዊ ሠነድ /ፓስፖርት፣ የመኖሪያ ፈቃድ፣ የስደተኛ መታወቂያ ወይም የምዝገባ ማረጋገጫ ሰነድ፣ የጉዞ ወይም ሌሎች ተያያዥ ሠነዶችን ይዘው በአካል በመቅረብ እንዲመዘገቡ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የምዝገባ ቦታውም በአዲስ አበባ ከተማ በኹሉም የወረዳ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽ/ቤቶች እና ፒያሳ በሚገኘው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ገላን፣ ዱከም፣ ለገጣፎ፣ ሱሉልታ፣ ቡራዩ፣ ሆለታ፣ ሰበታ እና ቢሾፍቱ ከተማ ወሚገኙ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ፅ/ቤቶች መሆኑንም አገልግሎቱ አስታውቋል።

ከላይ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ባልተመዘገቡ የውጭ አገር ዜጎች ላይ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ያሳሰበ ሲሆን፤ የውጭ ዜጎችን በመቅጠር የሚያሰሩ፣ በቤታቸው ተከራይቶ ወይም በጥገኝነት የሚያኖሩ ግለሰቦችም በተሰጠው ጊዜ ገደብ መመዝገባቸውን እና የምዝገባ ማረጋገጫ መውስዳቸውን እንዲያረጋግጡ ጠይቋል።

የኢፌዴሪ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ መንገድ ገብተው የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ዜጎችን የመመዝገብና የመቆጣጠር ስልጣን በአዋጅ ቁጥር 354/1995 እና ደንብ ቁጥር 114/1997 የተሰጠው ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች